Recently Posted News
  በአህጉራዊ ውድድሮች የክለቦቻችን የመጀመሪያ ጨዋታ ቅኝት
ጥር 06, 2008

በይርጋ አበበ

በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ስር ከሚካሄዱ ውድድሮች መካከል የክለቦች የቻምፒዮስን ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድሮች ይገኙበታል። ለ2016 የአህጉሩ ውድድሮች የሚሳተፉ ክለቦችን ለመለየት በተካሄደው የቅድመ ማጣሪያ ውድድርም ባሳለፍናቸው ሁለት ቀናት የአገራችን ሁለት ክለቦች በሜዳቸው ተጋጣሚዎቻቸውን አስተናግደዋል። መከላከያ በግብጹ አል ማቃሳ የሶስት ለአንድ ሽንፈት ሲገጥመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ቀድሞ እንደተተነበየው ተጋጣሚው የነበረውን የሲሸልሱን ቅዱስ ሚካኤልን ሶስት ለባዶ አሸንፎ ሸኝቶታል። የሁለቱን ክለቦቻችንን ጨዋታ በተመለከተ መጠነኛ ዘገባ ከዚህ በታች ቀርቧል።

የአገሪቱን እግር ኳስ አመላካች የሆነው የመከላከያ እና አል ማቃሳ ጨዋታ


መከላከያ እግር ኳስ ክለብ ከግብጹ የወቅቱ ጠንካራ ክለብ አል ማቃሳ ጋር ያካሄደውን ጨዋታ ሙሉ በሙሉ የጨዋታ ብልጫ ተወስዶበት ሶስት ለባዶ ተሸንፏ። የገብረመድህን ሀይሌ ቡድን በተለይ የአጥቂ መስመሩ ለጎል የቀረቡ ኳሶችን በቀላሉ ከማምከኑም በላይ የተከላካይ መስመሩ በቀላሉ የሚሰበር መሆን ለእንግዳው ቡድን አጨዋወት ምቾት ፈጥሮለት ታይቷል።

ሙሉዓለም ጥላሁን የተሻለ በተንቀሳቀሰበት የመከላከያ ቡድን ውስጥ በተለይ ባዬ ገዛኸኝ እና ምንይል ወንድሙ ያገኟቸውን የጎል እድሎች በቀላሉ ማምከናቸው መከላከያ በመልሱ ጨዋታ ነገሮች እንዲከብዱበት አድርጎታል።

የተከላካይ መስመሩም ቢሆን ለተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎች መንገድ ጠቋሚ እንጂ ባለጋራን የመመከት አቅም ያለው አልመስል ብሎ ታይቷል። የመሃል ሜዳውም ቢሆን በተለይ ከእረፍት በፊት በነበረው ክፍለ ጊዜ በሀይሉ ግርማ እና አንጋፋው ሚኬኤል ደስታ ለተጋጣሚዎቻቸው አመቺ ጨዋታን ሲጫወቱ የታዩ ሲሆን ተቀይሮ የገባው ሳሙኤል ደምሴ የመሀል ሜዳውን የበላይነት ወደ መከላከያ ለመመለስ ያደረገው ጥረት መልካም ሆኖ ታይቷል።

በአጠቃላይ ግን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የአገራቱን እግር ኳስ ደረጃ ምን ያህል ልዩነት እንዳለ በግልጽ ያመላከተ ነበር ማለት ይቻላል። ብሔራዊ ቡድን የክለቦች ነጸብራቅ መሆኑ የሚታወቅ እንደሆነው ሁሉ በቀጣይ ብሔራዊ ቡድናችን ከግብጽ አቻው ጋር ቢገናኝ ምን ያህል የጨዋታ ብልጫ ሊወሰድበት እንደሚችል አመላካች ነበር ማለት ይቻላል። ምክንያቱም አልማቃሳ በግብጥ ሊግ ከጠንካራዎቹ አል አህሊ ዛማሊክና ፔትሮሊየም ጄት ጋር የሚስተካከል የቡድን ጥራት የለውም እየተባለ የሚነገርለት ክለብ ሲሆን በግብጽ ብሔራዊ ቡድን ውስጥም ከሁለት እና ከሶስት የዘለሉ ተጫዋቾችን ማስተዋጻት አይችልም። ያም ሆኖ ግን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የተጫዋቾች የአካል ብቃት እና የመጫወት ፍላጎት እንዲሁም የአሸናፊነት ስነ ልቦና ልዩነት በግልጽ የታየ ነበር።

ቀጣይ ጉዞውን ያሳመረው እና ለሌላ ታላቅ ግዳጅ የተዘጋጀው ቅዱስ ጊዮርጊስ

በአፍሪካ የክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ለመወዳደር ከሲሼልሱ ቅዱስ ሚካኤል ጋር በአንጋፋው አዲስ አበባ ስታዲየም የተጫወተው አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በአዳነ ግርማ በሀይሉ አሰፋ እና በቅርቡ ክለቡን በተቀላቀለው ጋናዊ አጥቂው አማካኝነት ባስቆጠራቸው ሶስት ጎሎች አሸንፏል። ቀደም ብሎ እንደተገመተውም ፈረሰኞቹ የሲሼልሱን ቡድን ከተቻለ በሰፊ የጎል ልዩነት ካልሆነ ደግሞ በደርሶ መልስ አጠቃላይ ውጤት አሸንፈው ማለፍ እንደሚችሉ ሲነገር ቆይቶ ነበር። በጨዋታው የታየውም ፈረሰኞቹ የሲሼልሱን ክለብ በቀላሉ ሲጋልቡት ታይተዋል።

አሁን የፈረሰኞቹ ፈተና የሚሆነው ከዚህ ቀጥሎ ያለው ተጋጣሚያቸው ሁኔታ ነው። ይህ ማለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጣይ ተጋጣሚ ያለፈው ዓመት የቻምፒዮንስ ሊጉ ባለ ድል የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው ቴፒ ማዜቤ ነው። ማዜምቤ የጠንካራ ተጫዋቾች ስብስብ ያለው ክለብ እንደመሆኑ የፈረሰኞቹ ቀጣይ እና ትልቁ ፈተና ሆኖ የሚቀርበውም ይሄው ቡድን ይሆናል እንጂ ከሲሼልሱ ቅዱስ ሚካኤል ጋር ስለሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ የሚያሳስባቸው አይመስልም።

ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!