Recently Posted News
  ሃዋሳ ከነማ ወዴት እያመራ ነው?
የካቲት 10, 2008

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ጊዜ ማንሳት ችሏል፤ አዳነ ግርማን እና ሽመልስ በቀለን አይነት ኮከቦችን ለብሔራዊ ቡድንና ለአገሪቱ እግር ኳስ አስተዋውቋል፤ ከምንም በላይ ደግሞ እንደ ሙሉጌታ ምህረት አይነት ሁሉ በኩሉ የሆነ ተጫዋችን ማፍራት የቻለ ክለብ ነው ሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ። ይህ ሀሳብ ስለ ሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ጥንካሬ እና በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ ካስተዋጻው ህልቆ መሳፍርት ውለታው እጅግ ትንሹን ብቻ የተጠቀምኩበት ሀሳብ ነው።

በአንድ ክረምት የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት 10 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ አሰባሰበ። ያን ያህል ገንዘብ ወጭ የተደረገበት ቡድን ግን በዓመቱ አጋማሽ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ወራጅ ቀጠናውን በቅርብ ርቀት መከታተል ጀመረ። ለውጤቱ መጥፋት ተጠያቂ ናቸው የተባሉትን አሰልጣኙን ታረቀኝ አሰፋን አሰናብቶ በምትካቸው ውጤታማውን ውበቱ አባተን ቀጠረ። በወቅቱም የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ በመጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም “ውበቱ አባተ ለሀዋሳ ከነማ መልህቅ ይሆነው ይሆን?” በሚል ርዕስ በርካታ ስነ አመክንዮዎችን ጠቅሰዶ አንድ አርቲክል አስነበበ። የጸሀፊው እምነት ተሳክቶም ክለቡ ከወራጅ ስጋት ወጥቶ የውድድር ዓመቱን ጨረሰ።

ይህ የውድድር ዓመት ከመጀመሩ በፊት ደግሞ ክለቡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አድርጎት በማያውቀው መልኩ በርካታ ተጫዋቾችን ከታችኛው ቡድን ወደ ዋናው ቡድን በማሳደግ የውድድር ዓመቱን ጀመረ። በዚህ ወቅትም በርካታ የሀዋሳ ከነማ ተወላጆችና ነዋሪዎች በቡድናቸው ላይ እምነትን ማሳደር ጀመሩ። እምነት ለማሳደር ያስቻላቸው ምክንያት ሁለት ሲሆን በዋናነት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሚፈልገው መልኩ ቡድኑን በመገንባቱ ውጤት ያመጣልናል የሚለው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ክለቡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተጫዋቾች ዝውውር ምክንያት በርካታ ገንዘብ አባክኗል ተብሎ ይታማ ስለነበረ በዚህ ዓመት ግን የቡድኑ ተስፋዎችን ወደ ዋናው ቡድን በማሳደጉ ዋናውን ቡድን የተቀላቀሉት ወጣቶች ለክለባቸው ትልቅ ስራ ይሰራሉ በሚል ተስፋ ነበር። ነገር ግን የደጋፊዎች ተስፋ ጉም ሆኖ አልጨበጥ ያለው ገና የውድድር ዓመቱ ከመጀመሩ ነው። ቡድኑ አስር ጊዜ ተጫዋውቶ በ900 ደቂቃዎች ማሸነፍ የቻለው ሁለቱን ብቻ ማለትም 20 ፐርሰንት ብቻ ሲሆን በሶስቱ አቻ ወጥቶ በአምስቱ በመሸነፍ የወራጅ ቀጠናውን ከሆሳዕና ሀድያ ጋር እግር ለእግር እየተከተለ መምራቱን ተያያዘው። ለመሆኑ ሀዋሳ ከነማ ወዴት እያመራ ነው? የሚል ጥያቄ ለማንሳት የተገደድነውም በዚህ ምክንያት ነው።

የቡድኑ የውድቀት ቁልቁለት ምክንያት አንድ የጎል መስመሩን ማየት ያልቻለው አጥቂው ክፍል

ዋና አሰልጣኙ ውበቱ አባተም ሆነ በርካታ የቡድኑ ደጋፊዎችና ተጫዋቾች ከቡድኑ ውቀት ምክንያት ነው ብለው የሚያምኑት ክለቡ በአጥቂወች ድርቅ መመታቱን ነው። በደረጃ ሰንጠረዡ 13ኛ ላይ የተቀመጠውና ስምንት የጎል እዳ የተሸከመው ሀዋሳ ከነማ በዚህ የውድድር ዓመት ከአጥቂዎቹ ማግኘት ከነበረበት የጎል ብዛት ውስጥ 1/4ኛውን እንዳለገኘ ይታመናል። በዚህ የተነሳም በአንድ ወቅት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አጥቂዎቻቸውን ሰብስበው ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ለክለቡ ቅርበት ያላቸው የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ምንጮች ገልጸውልን ነበር።

በክለቡ ውስጥ አራት ነባር እና ሁለት ወጣት የፊት መስመር ተጫዋቾች ቢኖሩም በአስር ጨዋታ አንድ ጎል እንኳ ማግባት ያልቻሉ አጥቂዎች በቡድኑ ውስጥ አሉ። በስማቸው ጎል ማስቆጠር የቻሉት ተጫዋቾች ሁለት ሲሆኑ አንዱ ማለትም በረከት ይሳቅ በፍጹም ቅጣት ምት እና ወጣቱ ፍርድአወቅ ሲሳይ ደግሞ አንድ ጎል አግብቷል። ቀሪዎቹ አጥቂዎች ማለትመ ገብረ ሚካኤል ያዕቆብ፣ ጉዳት ላይ ያለው ተመስገን ተክሌ፣ መስቀሌ መንግስቱ እና እስራኤል እሸቱ ከጎል ጋር ያልተገናኙ ተጫዋቾች ናቸው። ይህ ደግሞ ለቡድኑ ውድቀት ዋና ተጠያቂ ባይሆን እንኳ አንዱ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ምክንያቱም ከሀዋሳ ከነማ ያነሰ ጎል በዚህ ዓመት ያስቆጠረ ክለብ የለምና ነው። የደረጃውን ግርጌ የተቆጣጠረውና በዚህ ዓመት ሊጉን የተቀላቀለው ሆሳና ሀድያ እንኳ ከሀዋሳ ከነማ የተሻለ ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ምክንያት ሁለት የተከላካይ ክፍሉ ወንፊትነት


መቋጠር የማይችለው የተከላካይ ክፍሉ ሌላው የሀዋሳ ከነማ የውድቀት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። ሀዋሳ ከነማ ከሆሳዕና ሀድያ፣ ደደቢትና መከላከያ ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች በድምሩ ዘጠኝ ጎሎች ተቆጥረውበታል። በእነዚህ ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ ሶስት ተጫዋቾች ማለትም የሆሳዕና ሀድያው ዱላ ሙላቱ፣ የመከላከያው ባዬ ገዛኸኝ እና የደደቢቱ ዳዊት ፈቃዱ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ጎሎችን አስቆጥረውበታል። አንድ ተጫዋች በአንድ በቡድን ላይ በአንድ ጨዋታ ሁለት ጎል ማግባት ከቻለ ይህ የተከላካዮች የስነ ልቦና እና የዝግጁነት ችግር ለመሆኑ የእግር ኳሱ ሊሂቃን ይናገራሉ።

አጥቂው ክፍል በአንድ ጨዋታ በአማካይ 0.35 ጎሎችን ብቻ በሚያስቆጥር ቡድን ውስጥ ተከላካይ ክፍሉ በአንድ ተጫዋች ብቻ በየ ጨዋታው ሁለት ጎሎች የሚቆጠርበት ከሆነ ቦታው ችግር አለበት ማለት ነው። ከላይ ከተጠቀሱት ሶስት ጨዋታዎች መካከል ከመከላከያ እና ከደደቢት ጋር የተካሄዱትን ጨዋታዎች ለአብነት አንስተን ለማየት ብንሞክር የመከላከያው ባዬ 16 ደቂቃ ሲቀር ተቀይሮ ገብቶ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው በተከላካዮቹ ሙጂብ እና አንዲሳለም ስህተቶች ያገኛቸውን ሁለት ኳሶች ተጠቅሞ ሲሆን የደደቢቱ ዳዊት ደግሞ የግርማ በቀለንና የሙጂብ ቃሲምን ስህተቶች ተጠቅሞ ያገኛቸውን ኳሶች ነው ያገባቸው። በተለይ ትናንት ከደደቢት ጋር በተካሄደው ጨዋታ ደደቢቶች የማዘን ያህል ጎሎችን ሳቱለት እንጂ ሀዋሳ ከነማ ከሶስት ለባዶም በባሰ የጎል ብዛት ተሸንፎ ይመለስ ነበር። ምክንያቱም የተከላካይ ክፍሉ ለተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎች መንገድ መሪ እንጂ መንገድ ዘጊ መሆን አልቻለምና ነው።

ምክንያት ሶስት ጉዳት


በዚህ ዓመት የሀዋሳ ከነማን ያህል በተጫዋቾች ጉዳት የተጎዳ ቡድን አለ ማለት ይከብዳል። ታላላቆቹ ጊዮርጊስና ደደቢትም የተጫዋቾች ጉዳት የደረሰባቸው ቢሆንም በውጤታቸው ላይ ቀውስ ሊፈጠርባቸው አልቻለም። የሀዋሳ ከነማን የተጫዋቾች ጉዳት የከፋ ያደረገው ክለቡ በተመሳሳይ ወቅት በተመሳሳይ ቦታ የሚጫወቱ ተጫዋቾቹ መጎዳታቸው ነው።

ለዚህ ደግሞ ሙሉጌታ ምህረት እና ሀይማኖት ወርቁ ከአማካይ ክፍሉ፣ ተመስገን ተክሌ እና በረከት ይሳቅ ከአጥቂ ክፍሉ እንዲሁም ተከላካይ ክፍሉ በተመሳሳይ ወቅት ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ይህም በቡድኑ ውጤት ላይ ያሳረፈው አሉታዊ ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።

ጉዳት በእግር ኳስ ስፖርት ውስጥ ያለ የነበረ እና የሚኖር አንዱ የስፖርቱ አካል ቢሆንም ሀዋሳ ከነማ ግን በጉዳት ምክንያት ውጤቱ ላይ ጉዳት ሊደርስበት የቻለው ለምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል። የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ እንደሚያምነው ግን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በቡድኑ የጉዳት አቴንዳንስ ሲበዛ የቀሪዎቹን ተጫዋቾች ስነ ልቦና እና የማሸነፍ ፍላጎት በማነሳሳት በኩል የወሰደው እርምጃ ያለ አይመስልም ቢኖርም ሜዳ ላይ አልታየም።

ምክንያት አራት ዳኛ

የአገሪቱ እግር ኳስ በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ የሚያጣጥር በሽተኛ ይመስላል። ይህን እግር ኳስ ደግሞ ከሞት ለመታደግ ሳይሆን ወደ ሞት መንደር ለማድረስ የሚተባበሩ በርካታ ገፊ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ የእግር ኳሱ ገፊ አካላት መካከል ደግሞ አንዱ ዳኞች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። እንደ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ አይነት የወቅቱ ኮከብ ዳኞች ያሉትን ያህል በርካቶች ግን ሙያው ከሚጠይቀው ችሎታ እና ስነ ምግባር ውጭ ሲሆኑ ይታያል። የስነ ምግባሩን ጉዳይ ወደ ጎን ትተን የችሎታ ማነሱን ብንመለከት እንኳ በዚህ ዓመት ብቻ ቅዱስ ጊዮርጊስ የገባ ጎል ተሽሮበት በአዳማ ከነማ ሁለት ለባዶ ተሸንፏል፣ ኢትዮጵያ ቡና በእጅ የተነካ ኳስ ፍጹም ቅጣት ምት ሊያገኝ ሲገባው ዳኛው ዝምታን በመምረጣቸው ቡና ሊሸነፍ ችሏል፣ ኤሌክትሪክ ባልተገባ የዳኝነት ውሳኔ ፍጹም ቀጣት ምት ተከልክሎ ተጫዋቹ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶበታል። እነዚህ ለአብነት የተነሱ የዚህ ዓመት ጉልህ ስህተቶች እንጂ ሌሎች የሉም ማለት አይደለም።

ሀዋሳ ከነማም በዚህ ዓመት ካካሄዳቸው ጨዋታዎች መካከል በዳኝነት በደል ከደረሰባቸው ክለቦች አንዱ ሲሆን በተለይ ትናንት ከደደቢት ጋር ሲጫወት የተቆጠረበት የመጀመሪያ ጎል ከጨዋታ ውጭ አቋቋም ላይ የነበረውን የደደቢትን ተጫዋች ኳስ እንዳነካ ጥረት ባደረገው ተከላካይ ምክንያት ነው። የደደቢቱ ተጫዋች ከጨዋታ ውጭ መሆኑን የመስመር ዳኛው ባለማየታቸው ጎሉ የተቆጠረበት ሀዋሳ ከነማ ራሱን ከጸጸት ለመመለስ ቢሞክርም ሌሎች ጎሎች ሊቆጠሩበት ችለዋል። በሌሎች ጨዋታዎች ተመሳሳይ የዳኝነት ችግሮች የደረሱበት የውበቱ አባተ ቡድን በዚህ ዓመት ላስመዘገበው እጅግ በጣም ደካማ ውጤት ዳኝነትን እንደ ምክንያት ቢያነሳ ውሃ ሊቋጥርለት ይችላል። ይህ ሲባል ግን በዳኛ ውሳኔ ሀዋሳ ከነማ ተሸነፈ ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ የራስን እከክ ሌላ ላይ ማላከክ ይሆናል።

መደምደሚያ

ሀዋሳ ከነማ በአስር ጨዋታዎች ማግኘት ከነበረበት 30 ነጥብ 1/3ኛውን እንኳ ማግኘት አለመቻሉ ግልጽ ነው። ከወራጅ ቀጠናው ውስጥ ለሳምንታት መቀመጡም የታወቀ እውነታ ነው። እነዚህ እውነታዎች በቡድኑ ላይ በደጋፊው በአመራሩ እና በአሰልጣኙ ላይ ስለ ልቦናዊ ጫና መፍጠራቸው ግልጽ ነው። ጥያቄው ክለቡ እንዴት ከውድቀት ይነሳ? የሚለው ይሆናል።

ውድቀት ለትንሳዔ ትምህርት ይሆናል ይባላል። ይህ አባባል ትክክል የሚሆነው በመውደቁ ለሚጸጸትና ለመነሳት ራሱን ለሚያነሳሳ ነው። ሀዋሳ ከነማ ውድቀት ላይ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም አሰልጣኝ ውበቱ ኣበተ እና ስብስቡ በሙሉ ከአመራሩ እና ከደጋፊው ጋር ቁጭ ብለው በመነጋገር መፍትሔ ላይ ሊደርሱ ይገባል። ይህ በጠረጴዛ ዙሪያ ዒደረግ የሚገባው ውይይት ትኩረቱን ማድረግ ያለበት በችግሮች እና በችግር አፈታቶች ዙሪያ እንጂ በመወቃቀስና በመወነጃጀል ላይ ሊሆን አይገባውም። ምክንያቱም እንደ ባለሙያም ሆነ እንደተመልካች የሀዋሳ ከነማው ውድቀት ስመለከተው ለቡድኑ ውጤት መጽፋት ከላይ ያስቀመጥኳቸው ምክንያቶች እነዳሉ ሆነው ለእነዚህ ምክንያቶች መፈጠር ደግሞ የሁሉም ድርሻ ሆኖ ነው ያገኘሁት።

ፕሪሚየር ሊጉ ሊጠናቀቅ 16 ጨዋታዎች ይቀሩታል። ዘጠኝ ጨዋታ ተጫውቶ ሊጉን የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሀዋሳ ከነማ በመካከላቸው ያለው የነጥብ ልዩነት 12 ብቻ ነው። ይህ አኃዝ ደግሞ በሂሳብ ስሌት የላይኛው የታችኛውን አሳንሶ የሚያሳይበት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም አራት ጨዋታዎችን በተከታታይ ያሸነፈ ቡድን ሊያስመዘበው የሚችለው ውጤት ስለሆነ። የሀዋሳ ከነማ ባለቤቶችና ይመለከተናል የሚሉ አካላትም ቁጭ ብለው ከተወያዩ እና በችግሮች ላይ መፍትሔ ማስቀመጥ ከቻሉ በቀሪዎቹ 16 ጨዋታዎች ማግኘት ከሚችሉት 48 ነጥብ ውስጥ አብላጫውን ነጥብ መሰብሰብ ከቻሉ በደረጃው አጋማሽ ላይ ሆነው ማጠናቀቅ ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ ያለፈው ዓመት የቡድኑ ተሞክሮ አንዱ ማሳያ ነው። ቡድኑ ከወራጅ ቀጠና ወጥቶ የከረመው በ13 ጨዋታዎች ብቻ በሰበሰበው ነጥብ ሲሆን በዚህ ዓመት ግን ቢያንስ የሶስት ጨዋታዎች አድቫንቴጅ እጁ ላይ አለለት።

ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!