Recently Posted News
  የኢትዮጵያ ቡና መውረድ እና የወደፊት ጉዞ
የካቲት 11, 2008

በይርጋ አበበ

ክለቡ ሜዳ ላይ ወርዶ ከሜዳ ውጭ ከፍታ ላይ ነው

የዚህን ጽሁፍ መግቢያ በአንድ የክለቡ መዝሙር ለመክፈት እገደዳለሁ። መዝሙሩ የድምጻዊት አስቴር ከበደ ቢሆንም የቡና ደጋፊዎች ለክለባቸው በሚመጥን መልኩ ግጥሙን ቀይረው ያዜሙት ነው። እናም መዝሙሩን በትንሹ ገልጬ ወደ ሀሳቤ እመለሳለሁ።

“ይሁን አይከፋኝም በቡና ብረታ በቡና ብረታ
በእሱ ይካካሳል የሰው አሉባልታ የሰው አሉባልታ
ጉዳት እና ጥቅሙ የእኔ ሆኖ ሳለ የእኔ ሆኖ ሳለ
እንዳማልተው አውቀው ቢተውኝ ምን አለ ቢተውኝ ምን አለ?
ልቤን አሸንፎት አደገኛው ቡና
ስምህን ሳላነሳ ውዬ አድሬ አላውቅም።
ቡና ቡና ቡና ቡና ቡና ቡና
ቃዋ ቃዋ ቃዋ ቃዋ ቃዋ ቃዋ ቃዋ”

ይህ መዝሙር በርካታ የኢትዮጵያ ቡና የልብ ደጋፊዎች በሚቀመጡባቸው ምስማር ተራ ከማን አንሼ እና ቀኝ ጥላ ፎቅ በተደጋጋሚ ያለ ማቋረጥ የሚዜም መዝሙር ነው። ይህ መዝሙር ታማኝ የክለቡ ደጋፊዎች ደጋግመው ይዘምሩት እንጂ ክለቡ ግን ከእለት ወደ እለት ከዓመት ወደ ዓመት በተሸጋገረ ቁጥር የደጋፊውን ቅስም ከመስበር እና በተቀናቃኝ ክለቦች የበላይነቱን አሳልፎ ከመስጠት ወደ ኋላ ሲል አልታየም። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ቡና በዚህን ያህል መጠን እና ባልተጠበቀ ፍጥነት ወደታች ሊምዘገዘግ ቻለ? ብሎ መጠየቅ ደጋፊውንም ሆነ አመራሩንና የቡድኑን አባላት ማስከፋትም ሆነ ማሳዘን ይሆናል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም መሬት ላይ ያለው እውነት ኢትዮጵያ ቡና በአስር ጨዋታ ማግኘት ከነበረበት 30 ነጥብ 11 ብቻ ያገኘ ሲሆን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ12
ነጥብ አንሶ ከደረጃ ሰንጠዡ ግርጌ አካባቢ ተቀምጧል። ይህ ደግሞ በየትኛውም መመዘኛ ክለቡ ሜዳ ላይ የለም ወይም ወርዷል ብሎ መናገር እውነት እንጂ ስህተትነት የለውም። ስለዚህ ቡና ለምን ወደቀ ወይም ወደ ታች ፈጠነ? ብዬ እጠይቅና የራሴንና የስፖርቱን ሳይንስ አስተያየት አካትቼ ከዚህ በታች ጽፌያለሁ።

ሜዳ ላይም መረብ ላይም የሌለው የቡና

 ኳስ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ በአዲስ አበባ ስታዲየም የኢትዮጵያው ተወካይ ቡና ገበያ ከግብጹ ግዙግፍ ክለብ ዛማሌክ ጋር እየተጫወተ ነው። በቡና ገበያ በኩል አማካይ ተከላካዩ አንዋር ያሲን እና አጥቂው አሰግድ ተስፋዬ ጎሎችን አስቆጥረው ካምቦሎጆን ጮቤ አስረገጡ። ዛማሌኮች አንድ ጎል አግብተው ጨዋታውን ወደ መለያ ምት ቢወስዱትምና ጨዋታው በመለያ ምት በዛማሌክ አሸናፊት ተጠናቆ ቡና ገበያ ከውድድሩ ሰናበትም በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ግን ደስታቸው ሳይደበዝዝ ክለባቸውን እያደነቁ ቤታቸው ገቡ። ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ክለባቸው ሜዳ ላይ ያሳየው ማራኪ ጨዋታ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ ክስተት ከተካሄደ 15 ዓመታትን አስቆጥሯል።

በ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከነማ ሲጫወት የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ካታንጋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከቡና ደጋፊዎች መሀል ተቀምጦ ጨዋታውን እየተከታተለ ነው። እንደወትሮው በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ካምቦሎጆ ገብተው ጨዋታውን ባይከታተሉትም ስታዲየም የታደሙት ጥቂት የክለቡ ታማኝ ደጋፊዎች ግን ቡድናቸውን እያበረታቱ ነበር። በመሀል ግን ደጋፊዎቹ በአንድ ድምጽ በክለባቸው ተጫዋቾችና አሰልጣኝ ላይ ቁጣ ያዘሉ ጠንካራ ቃላትን ያወርዱ ጀመር። ምክንያታቸውን ሲናገሩም “እኛ እኮ ስታዲየም የምንመጣው በየዓመቱ ዋንጫ እየበሉ መደርደሪያ ላይ ለመሰብሰብ አይደለም። የእኛ ፍላጎት በቡና ጨዋታ  ተደስቶ መውጣት ነው። ይህን ደግሞ ማግኘት አልቻልንም ወይ አያገባም ወይም አይጫወትም” ሲሉ የቡድናቸውን ድክመት በግልጽ መናገር ጀመሩ።

ክለቡ በዚህ ዓመት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ አገር ዜግነት ያለው አሰልጣኝ ቀጥሮ ውድድሩን ቢጀምርም ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ የተሻሻለ ቡድን ይዞ መቅረብ አልቻለም። ሊጉ ከተጀመረ ገና 10ኛ ሳምነቱ ላይ ቢሆንም ከአሁኑ ከዋንጫ ፉክክር ውጭ መሆኑ ታወቀ። ይባስ ብሎ ደግሞ ክለቡ ቀደም ሲል ከሌሎች ክለቦች ተለይቶ የሚታወቅበት ማራኪ ኳስ ፍሰት የተላበሰ አጨዋወቱ ሜዳ ላይ ጠፋ። አጥቂዎቹ የተጋጣሚ ቡድን የግብ ክልል የትጋ እንዳለ የማያውቁ ሆነው ታዩ። አማካዩ በተለይም ከመስዑድ መሀመድ ኤልያስ ማሞ እና እያሱ ታምሩ ውጭ ያሉት ከቡድናቸው ጋር ተቀናጅተው ከመጫወት ይልቅ ኳስን ወደ መጣችበት የሚጠልዙ እና ውጤት ተኮር አጨዋወትን የሚመርጡ ሆነው ተገኙ። ተከላካይ ክፍሉ ደግሞ የተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎች ሲቀርቡት እግሩ ቄጤማ ይሆናል። ግብ ጠባቂውማ ጭራሽ ኳሷን የጦር ያህል የሚፈራት ይመስል ኳስ ሲመታበት ኳሷ ባልሄደችበት አቅጣጫ ይወድቃል እንጂ መረቡ ላይ ከማረፏ በፊት በጓንቶቹ ለመያዝ ሲሞክር አይታይም። ይህ ሁሉ ድክመት እና ውድቀት የዚህ ዓመት የቡና ጉዞ ነው ኳሱ ሜዳ ላይም በተጋጣሚ መረብ ላይም የሌለችበት የቡና ቡድን።

የሽንፈት እና የውድቀት ምሳሌ?

አርባ ምንጭ ከነማ፣ ሀዋሳ ከነማ እና ሲዳማ ቡና ሶስቱም የደቡብ ክልል ክለቦች ናቸው። ሶስቱ ክለቦች ባለፈው ዓመት እና በዚህ ዓመት ከቡና ጋር ባካሄዷቸው ስድስት ጨዋታዎች በየጨዋታው ከኢትዮጵያ ቡና ላይ ሶስት ሶስት ነጥቦችን ይዘው ሂደዋል። ባለፈው የውድድር ዓመት ሁለተኛ ዙር ላይ ደደቢት ቡናን ሶስት ለባዶ ያሸነፈው ሲሆን በዚህ ዓመትም በመጀመሪያ ዙር መገናኘታቸው ሁለት ለአንድ አሸንፎታል። አራት ክለቦች በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ገጥመውት ሁለቱንም ጨዋታዎች በበላይነት አጠናቀውበታል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ብሎ ለሚጠይቅ አስተዋይ አንባቢ መልሱ ግልጽ እና ግልጽ ነው ተጋጣሚዎቹ ክለቦች የቡናን ውስጣዊ ድክመት ጠንቅቀው አውቀውታል። ለዚህም ነው ክለቡ ከዓመታት በፊት በተጋጣሚ ቡድኖች በተለይም ለክልል ክለቦች አስፈሪ የነበረውን ያህል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለተጋጣሚዎች ቀላል ሆኖ የታየው።

ከ2004 ዓ.ም ወዲህ ባሉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ ቡና ከኢንተርናሽናል ውድድር ውጭ ሆኗል። ከአራት ዓመታት ወዲህ ከኤልያስ ማሞ እና አብዱልከሪም መሃመድ ውጭ በአገሪቱ ደረጃ ኮከብ ሊባል የሚችል ተጫዋች አስፈርሞ አያውቅም። በ2003 የሊጉን ዋንጫ ካነሳ በኋላ አንድ ጊዜ ብቻ ሁለተኛ ወጥቶ ሲያጠናቅቅ ሌሎቹን ጊዜያት ከሶስተኛ በታች ሆኖ ነው ያጠናቀቀው። አንድ ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅም ዋንጫውን ካነሳው ከደደቢት በ21 ነጥብ አንሶ ነው ያጠናቀቀው።

ከ2004 ወዲህ የቡድኑን ኮከቦች ማቆየት አልቻለም። ለአብነት ያህልም አስቻለው ግርማ ቶክ ጄምስ ዳዊት እስጢፋኖስ ታፈሰ ተስፋዬ ምንያህል ተሾመ ጀማል ጣሰው እና ሙላለም ጥላሁን ባለፉት ሶስት እና አራት ዓመታት ክለቡን የለቀቁ የክለቡ ኮከቦች ነበሩ። ባለፉት አራት ዓመታት ክለቡ አምስት አሰልጣኞችን ቀያይሯል። አራቱ አሰልጣኞች ለክለቡ ማበርከት ከነበረባቸው ግማሽ ያህሉን እንኳ ሳይፈጽሙለት ነው ያሰናበታቸው።  እነሱም በ2005 ጸጋዬ ኪዳነማሪያም በ2006 ጳውሎስ ጌታቸው ማንጎ በ2007 ጥላሁን መንገሻ እና አንዋር ያሲን ሲሆኑ በዚህ ዓመት ደግሞ ሰርቢያዊው ድራጋን ፖፓዲች የቡናን ካምፕ የተፈራረቁበት አሰልጣኞች ናቸው። እነዚህን ሁሉ በጥልቀት ከተመለከትን ክለቡ በ2003 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ካነሳ በኋላ በየዓመቱ እየወረደ መሄዱን ነው። ይህ ደግሞ ከላይ የውድቀትና የሽንፈት ምሳሌ ብዬ የጠቀስኩትን ርዕስ ያጠናክርልኛል።

ከሜዳ ውጭ ያለው ቡና

 አንድ ቡና ላኪ በቶን 30 ብር እያዋጣ የሚደጉመው ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከሜዳ ላይ ባለው እንቅስቃሴው ጠንካራ እና ስኬታማ ነው ማለት ይቻላል። ከቀድሞው የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን በተገኘ ሰነድ ለማወቅ እንደተቻለቸው “በአገሪቱ ውስጥ ጠንካራ እና ፕሮፌሽናል የክለብ አደረጃጀል ያለው ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ነው” ሲል ያመለክታል። ይህ ምስክርነት ደግሞ ክለቡ በአደረጃጀት በኩል ጥሩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ አካባቢ በአስር ሚሊዮን ብር ያስገነባው የተጫዋቾች ማደሪካ ካምፕ እና የስፖርት ማዕከል የተጠናቀቀው ባሳለፍነው ወር ነው። በስፖርት ማዕከሉ አቅራቢያ ደግሞ ከ25 ሺህ በላይ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችል ስታዲየም ለመገንባት እንቅስቃሴም ጀምሯል። ገቢውን በማሳደግ በኩል ደግሞ ከተለያዩ ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር በተለይም ከሀበሻ ቢራ ጋር ባደረገው ስምምነት በዓመት 12 ሚሊዮን ብር የማሊያ ላይ ስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ላይ የደረሰ ሲሆን ከሀበሻ ሲሚንቶ ጋር ደግሞ ለጊዜው መጠኑ የማልገልጸው ግን ከፍተኛ እንደሆነ የሚነገር ገንዘብ በስፖንሰር መልክ ያገኛል።

በየዓመቱ ለማካሄድ ባቀደው የቡና ቤተሰብ ሩጫ ላይ እና በየሳምንቱ በሚያቀርበው የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ሌሎች ተጨማሪ ድርጅቶች ክለቡን ስፖንሰር ያደርጉታል።  እነዚህ ሁሉ ክለቡን ከሜዳ ውጭ እያጠናከሩት ያሉ ክስተቶች ቢሆንም ሜዳ ላይ ግን ቡና የለም።

ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
Dani Sanjawe [731 days ago.]
  my prediction:- St.George 5 - 1 Bank [ 2 Goals -Adane Girma ] [ 2 Goals Sala ] [ 1 Goal ጎድዊን ቺካ ]

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!