Recently Posted News
  ፈረሰኞቹ የባህር ዳር ስታዲየምን ሪከድ አስጠብቀዋል
መጋቢት 05, 2008

በይርጋ አበበ

ወደ አንድ ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ወጭ የሆነበት ግዙፍ ስታዲየም ነው የባህር ዳር ሁለገብ ስታዲየም። ይህ ስታዲየም ግንባታው ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ የተለያዩ ኢንተርናሽናል ውድድሮችን ማካሄድ ጀምሯል። ስታዲየሙ ለኢንተርናሽናል ውድድር ክፍት ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደው ጨዋታ ደደቢትን ከሲሼልሱ ኮት ዲኦር ክለብ ጋር ሲሆን የእለቱንም ሆነ ለስታዲየሙ የመጀመሪያ የሆነችውን ጎል ያስቆጠረው የደደቢቱ ስዩም ተስፋዬ ሲሆን ጨዋታው የተጠናቀቀውም በደደቢት ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ነበር።

ይህ ስታዲየም ታዲያ ከደደቢት ጨዋታ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን አንድ ጊዜ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ሁለት ጊዜ ያስተናገደ ሲሆን በሴካፋ ውድድርም ስድስት ጨዋታዎችን አስተናግዷል። የሴካፋውን ትተን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የአገሪቱ ክለቦች በዚያ ስታዲየም ተጫውተው ያስመዘገቡትን ውጤት በተመለከተ አንድ ሁለት ነጥቦችን እናነሳለን።

ኢትዮጵያዊያን የማይሸነፉበት ስታዲየም

በንዑስ ርዕሱ እንደተገለጸው በባህር ዳሩ ግዙፍ ስታዲየም የአገሪቱ ብሔራዊ ቡድንም ሆነ ዋልያዎቹ በድምሩ አራት ጊዜ ጨዋታቸውን አድርገው አንድም ጊዜ አልተሸነፉም። ዋልያዎቹ ሌሴቶን እና ኬኒያን በተመሳሳይ ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ያሸነፉ ሲሆን ደደቢትም የተጠቀሰውን ክለብ ሁለት ለአንድ ማሸነፉን ገልጸን ነበር። በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ ፈረሰኞቹ ከዓመት በፊት ያደረጉትን ጨዋታ አንድ እኩል ተለያይተው በስታዲየሙ ኢትዮጵያዊያን ቡድኖች ሳይሸነፉ የተጓዙበትን ሪከርድ አስጠብቀው ነበር።

በዚህ ዓመት የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል በድምቀት በማክበር ላይ የሚገኘው ግዙፉ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በግዙፉ የባህር ዳር ስታዲየም የወቅቱን የአፍሪካ ሃያል ክለብ ቲፒ ማዜምቤን አስተናግዶ ሁለት እኩል መውጣት ችሏል። በዚህ ውጤት መሰረትም የባህር ዳርን ስታዲየም ሪከርድ አስጠብቆ መውጣት አስችሎታል።

በሌላ በኩል ደግሞ ፈረሰኞቹ ያስመዘገቡት ውጤት በተጠቀሰው ስታዲየም ሳያሸንፉ መጓዛቸውን አስቀጥለውታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በባህር ዳሩ ብሔራዊ ሁለገብ ስታዲየም በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ሁለት ጨዋታዎችን አካሂደው ሁለቱንም በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ ችለዋል። ይህ ውጤትም ፈረሰኞቹ ባህር ዳር ላይ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው ያልተመለሱበትን ሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታቸው ሆኗል። ለፈረሰኞቹ በሀይሉ አሰፋ እና አዳነ ግርማ ጎሎቹን ሲያስቆጥሩ ለቲፒ ማዜምቤ ደግሞ አስቻለው ታመነ በራሱ ላይ እና የቲፒ ማዜምቤው 19 ቁጥር ዳንኤል አድጂኔ አስቆጥረውለታል።

የጨዋታው መዘርዝር

ፈረሰኞቹ እና ኮሮኮዳይሎቹ ከዚህ በፊት በ1958 ዓ.ም ማለትም የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር በተጀመረ በሁለተኛው ዓመት ነበር። በወቅቱ ሁለቱ ቡድኖች አዲስ አበባ ላይ በፈረሰኞቹ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ቢያጠናቅቁም ኮንጎ ላይ በተካሄደው ጨዋታ ማዜምቤዎች ሶስት ለአንድ ነበር ያሸነፉት።

የትናንትናው ጨዋታ በባህር ዳር ስታዲየም ሲካሄድ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ደጋፊ በስታዲየም ተገኝቶ ጨዋታውን የተከታተለ ሲሆን በባህር ዳር ከተማም ለጊዮርጊስ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎለት ነበር። ፈረሰኞቹ ቀድሞ ከሚታወቁበት በተለየ መልኩ በኳስ ቁጥጥሩ ላይ ትኩረት አድርገው መጫወታቸውም ተገልጿል። ጨዋታውን የመሩት ደግሞ አራት ሲዋዚላንዳዊያን ዳኞች ሲሆኑ ኮሚሽነር የነበሩት ደግሞ ዚምባቡዌዊው ኦኒያን ፍሊክስ ናቸው።

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሰጡት የክለቡ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች በውጤቱ አለመከፋታቸውን ገልጸዋል። በተለይ የዕለቱን የመጀመሪያ ጎል ያስቆጠረው በሀይሉ አሰፋ “ውጤቱ የተገኘው በስነ ልቦና ዝግጅት” መሆኑን ለሶከር ኢትዮጵያ የገለጸ ሲሆን ምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታ ደግሞ ጨዋታውን የሚያሸንፉበት እድል እጃቸው ላይ እንደነበረ ነገር ግን ሳይጠቀሙበት መቅረታቸውን ለአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከሳምንት በኋላ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ በሉምባሺ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘውና 18 ሺህ ደጋፊዎችን በሚይዘው ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል። ለመልሱ ጨዋታ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸውም የፈረሰኞቹ አሰልጣኞችና ተጫዋቾች ተናግረዋል።

ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!