Recently Posted News
  የ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዙር ዳሰሳ
መጋቢት 10, 2008

በይርጋ አበበ

ለዓመታት የሊጉም ሆነ የአገሪቱ እግር ኳስ እድገት ተወዳሽ የነበረውን ሙገር ሲሚንቶንና በመጣበት እግሩ ሳይውል ሳያድር የተመለሰውን ወልድያ ከነማን አሰናብቶ በምትካቸው ደካማውን ሆሳዕና ሀድያን እና አስገራሚውን ቡድን ድሬዳዋ ከነማን ተቀብሎ ውድድሩን የጀመረው የ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አንደኛው ዙር መርሃ ግብር ተጠናቋል። በእርግጥ ያለፈው ዓመት ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዳሽን ቢራ እና ከመከላከያ የሚያካሂዳቸው ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀራሉ። ከሁለቱ ጨዋታዎች በስተቀር ፕሪሚየር ሊጉ 89 ጨዋታዎችን አስተናግዷል። በእነዚህ 89 ጨዋታዎች የትኞቹ ክለቦች ከተጠበቀው በታች ሆኑ? የትኞቹስ ሳይጠበቁ አስገራሚ አቋም አሳዩ? የትኛው ተጫዋችስ የተሻለ ነበር? ተጠብቆ የጠፋውስ ማንኛው ነው? ከአሰልጣኞች መካከል የትኛው በሚፈልገው መልኩ ቡድኑን ገንብቷል? የትኛውስ ደክሞ ታየ? የሚሉትንና ሌሎች ተያያዥ ነጥቦችን በማንሳት የ14ቱንም ክለቦች የግማሽ ዓመት ጉዞ እንዳስሳለን።

ማስታወሻ፦ የክለቦቹ ቅደም ተከተል ካለፈው ዓመት ሻምፒዮን በመነሳት ነው የተመረጡት።

ቅዱስ ጊዮርጊስ  7 ፡ 2 ፡ 2

በዚህ የውድድር ዓመት ሶስት የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎችን ያካሄደውና ለአራተኛው ጨዋታ ዛሬ ማለዳ ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሉሙምባሼ ያቀናው ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ 11 ጨዋታዎችን አካሂዷል። ፈረሰኞቹ በዚህ ዓመት ካካሄዷቸው 11 የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ሰባቱን በማሸነፍ ከየትኛውም ክለብ በላይ ብዙ ጨዋታዎችን ያሸነፉ ክለብ ያደርጋቸዋል። እዚህ ላይ ይህ አኃዝ ፈረሰኞቹ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ሰለሚቀራቸው በተሰራ ስሌት እንጂ ሰባት ጨዋታ ያሸነፈ ሌላ ክለብ አለ።

ሊጉ ሲጀመር ወደ አዳማ ያቀኑት ፈረሰኞቹ በአዳማ ከነማው ወንድወሰን ሚልክያስ ሁለት ጎሎች ሁለት ለባዶ በመሸነፍ ነበር የዓመቱን ውድድራቸውን የጀመሩት። በጨዋታው ብሪያን አሙኒ ያገባት ጎል የተሻረበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም እንኳ በጎሏ መሻር ተቃውሞውን ቢያሰማም ለሽንፈቱ ግን ምክንያት አድርጎ አላቀረበም ነበር። በሁለተኛው ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ጨዋታቸው በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲዳማ ቡናን አስተናግደው አምስት ለአንድ በሆነ ሰፊ የጎል ልዩነት በማሸነፍ ወደ አሸናፊነታቸው ተመለሱ።

በአጠቃላይ ፈረሰኞቹ ያሸነፏቸው ሰባት ጨዋታዎች የሚከተሉት ናቸው። በሲዳማ ቡና አንድ ብለው የነጥብ አካውንታቸውን የከፈቱት ፈረሰኞቹ በተከታታይ ሶስት ጨዋታዎችን ማለትም ከሲዳማ ቡና በተጨማሪ ኤሌክትሪክንና ድሬዳዋ ከነማን በተመሳሳይ አንድ ለባዶ ያሸነፉ ሲሆን በሊጉ አምስተኛ ሳምንተ ጨዋታቸው ከዘወትር ተቀናቃኛቸው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ባዶ ለባዶ በመለያየት የማሸነፍ ግስጋሴያቸው የተገታ ቢሆንም በተከታዮቹ አራት ሳምንታት አንድም ጎል ሳይቆጠርባቸው ሆሳዕና ሀድያን እና ደደቢትን በተመሳሳይ ሁለት ለባዶ፣ ወላይታ ድቻን ሶስት ለባዶ እና አርባ ምንጭ ከነማን አንድ ለባዶ ማሸነፍ ችለዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የግማሽ ዓመቱን ሁለተኛ ነጥብ ተጋርቶነ የወጣበትን ጨዋታ ያካሄደው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ባዶ ለባዶ የተለያዩበት ጨዋታ ነው። በ11ኛው ጨዋታቸው ደግሞ ወደ ሀዋሳ አቅንተው የዓመቱን ሁለተኛ የሽንፈት ጽዋቸውን ተጎንጭተው ተመልሰዋል ሁለት ለአንድ በመሸነፍ።

በአጠቃላይ ፈረሰኞቹ ሰባት አሸንፈው፣ ሁለት አቻ ተለያይተው እና ሁለት ጊዜ ተሸንፈው የነጥብ ድምራቸውን 23 አድርሰዋል። ኮከቡ አጥቂያቸው አዳነ ግርማ ሰባት ጎሎችን ሲያስቆጥርላቸው ጠንካራው የተከላካይ ክፍሉ እና ምርጡ በረኛቸው ማስተናገድ የቻሉት የጎል ብዛት ደግሞ አምስት ጎሎችን ብቻ ነው። ይህም ከየትኛውም የሊጉ ተፎካካሪ ክለብ በላይ ጨዋታዎችን በማሸነፍና ዝቅተኛ ጎል የተቆጠረበት ክለብ ያደርጋቸዋል።

የቡድኑ ኮከቦች አዳነ ግርማ እና ሮበርት ኦዶንካራ

ደደቢት 7 ፡ 4 ፡ 2

13 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ያካሄዱት ሰማያዊ ለባሾቹ ደደቢቶች ሰባት ጨዋታዎችን አሸንፈው በአራት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራትና ሁለት ጊዜ ብቻ በመሸነፍ የነጥብ ድምራቸውን 25 በማድረስ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ከሚቀሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለት ነጥብ ልቀው የሊጉን መሪነት ተቆጣጥረውታል።

ከ13 የሊጉ ጨዋታቸው በአምስቱ መረባቸውን ያላስደፈሩት ሰማያዊ ለባሾቹ ጎል ሳያስቆጥሩ የወጡበት ጨዋታ ደግሞ አንድ ብቻ ነው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ባዶ ለባዶ ሲለያዩ። ሰማያዊዮቹን ከሊጉ ክለቦች ለየት ከሚያደርጓቸው አብይ ክስተቶች መካከል አንዱም በ12 ጨዋታዎች ጎል ያስቆጠሩ ብቸኛ ክለብ መሆናቸው ነው። የብሔራዊ ቡድኑን አምበል ስዩም ተስፋዬን እና ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነትን የያዙት ደደቢቶች ሽንፈት ያስተናገዱት በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በአዳማ ከነማ ብቻ ነው። በእነዚህ ሁለት ጨዋታዎችም ፈረሰኞቹ ሁለት ለባዶ የስምጥ ሸለቆው አዳማ ከነማ ደግሞ ሶስት ለሁለት ነው ያሸነፋቸው።

ደደቢት ነጥብ ተጋርቶ የወጣባቸው ጨዋታዎች ሶስቱን አዲስ አበባ ላይ ሲሆን ማለትም ከንግድ ባንክ ጋር ባዶ ለባዶ፣ ከአርባ ምንጭ ከነማ ጋር አንድ እኩል እና ከኤሌክትሪክ ጋር ሁለት ለሁለት የተለያየባቸው ናቸው። ቀሪው አንድ ጨዋታ ይርጋለም ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር ሁለት እኩል የተለያየበት ነው። ከአዲስ አበባ ውጭ አራት ጨዋታዎችን ብቻ ያካሄዱት የ2005 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮናዎች ከአራቱ ጨዋታዎች ሁለቱን ማለትም ዳሽን ቢራን ጎንደር ላይ አንድ ለባዶ እና ሆሳዕና ሀድያን ሆሳዕና ላይ ሶስት ለአንድ አንፈዋል። እነዚህ ሁለት ክለቦች ደግሞ በአሁኑ ወቅት የሊጉን ግርጌ ተከታትለው የያዙ ክለቦች ናቸው።

የቡድኑ ኮከቦች ሳሙኤል ሳኑሚ እና ስዩም ተስፋዬ

ኢትዮጵያ ቡና 12 ፡ 14

የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት የሆነውና የአዲስ አበባ ስታዲየም ውበት የሚባለው ኢትዮጵያ ቡና በዚህ ዓመት አልሆንልህ ብሎታል። በውድድሩ ግማሽ ዓመት ካካሄዳቸው 13 ጨዋታዎች 12 ጎሎችን ብቻ አስቆጥሮ 14 ደግሞ ተቆጥሮበታል። ሊጉን በዚህ ዓመት የተቀላቀለው እና የደረጃውን ግርጌ የያዘው ሆሳዕና ሀድያ እንኳ ከቡና በተሻለ ጎል ያስቆጠረ ክለብ ነው።

በ40 ዓመት የክለቡ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ አገር አሰልጣኝ በመቅጠርና በርካታ ነባር ተጫዋቾቹን አሰናብቶ በምትካቸው በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ይዞ ወደ ውድድር የገባው ኢትዮጵያ ቡና በ13 የሊግ ጨዋታዎች ስድስት ጊዜ ተሸንፏል። ከአዳማ ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አዲስ አበባ ላይ ነጥብ ሲጋራ ከሜዳው ውጭ ደግሞ ድሬዳዋ ላይ ከመሰረት ማኔ ቡድን ጋር ነጥብ ተጋርቶ ተመልሷል። ማሸነፍ የቻለው አራት ጨዋታዎችን ብቻ ሲሆን አራቱንም ጨዋታዎች ያሸነፈው አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ነው። ንግድ ባንክን አንድ ለባዶ፣ ኤሌክትሪክን ሁለት ለአንድ፣ ዳሽን ቢራን ሁለት ለባዶ እና ሆሳዕና ሀድያን ሁለት ለአንድ ነው ማሸነፍ የቻለው።

የድራጋን ፖፓዲች ስብስብ 12 ጎሎችን ብቻ ያስቆጠረ ሲሆን ከእነዚህ ጎለሎች መካከል ግማሹን ያስቆጠረው ያቡን ዊሊያም ነው። ሁለቱን ተከላካዩ አብዱል ከሪም መሃመድ ሲያስቆጥር ቀሪዎቹን አራት ጎሎች አራት ተጫዋቾች ናቸው ያስቆጠሩለት። ሜዳ ላይ በጨዋታ ውበትም ሆነ ነጥብ መሰብሰብ ያልተሳካለት ኢትዮጵያ ቡና በ15 ነጥብና ሁለት የጎል እዳ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ይህም ቡናማዎቹ በቀሪው የውድድር ዘመን ከፍተኛ ስራ የሚጠብቃቸው መሆኑን አመላካች ነው።

የቡድኑ ኮከብ አብዱልከሪም መሀመድ እና ኤልያስ ማሞ


አነስተኛ በጀት፣ ማራኪ ጨዋታ እና ውጤት መገለጫው የሆነው ወላይታ ድቻ

ይህን የደቡብ ኢትዮጵያ ክለብ ሳስብ ሁለት መላምቶች ወደ አዕምሮዬ ይመጣሉ።  የመጀመሪያው “ምነው የአገሪቱ እግር ኳስ ክለቦች ራሳቸውን በወጣቶችና ተስፈኛ ተጫዋቾች ቢገነቡ?” የሚል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ “ውለታ የማያውቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ የሙገር ሲሚንቶን እጣ ፈንታ ለወላይታ ድቻ እንዳይሰጠው” ስል እሰጋለሁ። ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ቡና “አትችልም” ተብሎ የተሰናበተውን ባዬ ገዛኸኝን ጨምሮ እንደ አላዛር ፋሲካ፣ አዲሱ ተስፋዬ፣ ብሩክ ቃልቦሬ፣ አሸናፊ ይታየውና እሸቱ መና አይነት በርካታ ወጣቶችን ለታላቅነት ያበቃው የመሳይ ተፈሪ ቡድን ወላይታ ድቻ በዚህ ዓመት ካካሄዳቸው 13 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች 20 ነጥቦችን መሰብሰብ በመቻሉ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ስድስት ጨዋታዎችን አሸንፎ፣ ሁለት አቻ ወጥቶና አምስት ጊዜ ደግሞ የተሸነፈው ወላይታ ድቻ፤ በሜዳው በድሬዳዋ ከነማ አንድ ለባዶ፣ ከሜዳው ውጭ ደግሞ ወራጅ ቀጠና ላይ ባለው ሆሳዕና ሀድያ የአምስት ለአንድ እና በፈረሰኞቹ የደረሰበት የሶስት ለባዶ ሽንፈት የቡድኑን ስነ ልቦና በእጅጉ የጎዳ ነበር። ሶስቱንም ጨዋታዎች የተሸነፈው በተከታታይ መሆኑ ደግሞ ክስተቱን ከባድ ያደርገዋል። ሆኖም ቀደም ብሎ አርባ ምንጭ ከነማን፣ ሀዋሳ ከነማን እና ዳሽን ቢራን አንድ ለባዶ በሆነ ተመሳሳይ ውጤት ማሸነፉ እና ከጊዮርጊስ ሽንፈት በኋላም አዲስ አበባ ላይ መከላከያን በአላዛር ፋሲካ ጎሎች ሁለት ለአንድ፣ በሜዳው አዳማ ከነማን ሁለት ለባዶ እና ኢትዮጵያ ቡናን ሁለት ለአንድ በማሸነፉ የቡድኑን ስነ ልቦና ማንሰራራት አስችሎታል።

በአጠቃላይ በ13 ጨዋታዎች 13 ጎሎችን ያስቆጠረው ወላይታ ድቻ በሶስት ጨዋታዎች ጎል አላስቆጠረም። የተቆጠረበት የጎል ብዛት ደግሞ 16 ደርሷል።

የቡድኑ ኮከቦች አላዛር ፋሲካ እና በዛብህ መለዮ

ይቀጥላል!!

ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name [66 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [66 days ago.]
 arachni_text

arachni_name) [66 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [66 days ago.]
 arachni_text)

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!