Recently Posted News
  የ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዙር ዳሰሳ ክፍል ሁለት
መጋቢት 13, 2008

በይርጋ አበበ

በትናንትናው ዝግጅታችን የአራት ክለቦችን የግማሽ ዓመት የውድድር ጉዞ አስቃኝተን ነበር። አራቱ ክለቦች በግማሽ ዓመቱ ያደረጓቸውን ጉዞዎች ጠንካራ እና ደካማ ጎናቸውን በመዳሰስ ሙያዊ አስተያየታችንን አቅርበን ነበር። ዛሬ ደግሞ የርዕሰ ጉዳዩን ቀጣይ ክፍል ይዘን የቀረብን ሲሆን በዛሬው ዝግጅታችን ሶስት ክለቦችን የምንዳስስ ይሆናል።

የውድድር ዓመቱ ክስተት ድሬዳዋ ከነማ

የሙአመር ጋዳፊ አገር ሊቢያ ባስተናገደችው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ውድድሩ እንዲያቀና አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የደርሶ መልስ የማጣሪያ ጨዋታ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው መሃመድ ሚግ። ሚጉ ተቀይሮ ገብቶ በግንባሩ ገጭቶ ያስቆጠራት ጎል በኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ አሰልጣኝነት እና በአስራት ኃይሌ አምበልነት የሚመራውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ትሪፖሊ እንዲያቀና ምክንያት ሆነች። ሚግ ትውልድና እድገቱ ድሬዳዋ ነው።

ድሬዳዋ የመሀመድ ሚግ ብቻ ሳይሆን የአሸናፊ ግርማ እና ዮርዳኖስ አባይም የትውልድ ቦታ ነው። አሰግድ ተስፋዬ እትብቱ የተቆረጠውም ሆነ ስምኦን አባይ የተወለደው እዚያው ድሬዳዋ ከተማ ነው። አስራት ኃይሌ የእግር ኳስ እድገቱ የጎመራውም ሆነ መንግስቱ ወርቁ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወት የጀመረው በድሬዳዋ አሸዋማ መሬት ላይ ነው። አጠር እና ምጥን ባለ ቋንቋ ድሬዳዋ የኢትዮጵያ እግር ኳስ መፍለቂያ ከተማ ነች። ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ባነሳችውና እስካሁንም እንደ “መማያ” የምታነሳውን ሶስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ስታነሳ ከቡድኑ ቋሚ 11 ተጫዋቾችና አሰልጣኝ መካከል ስምንቱ የድሬዳዋ ልጆች ነበሩ።

ከላይ የተጠቀሰው የድሬዳዋ ከነማ የእግር ኳስ ታሪክ ወደ መቃብር ወርዶ ደካማ በሚባለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንኳ የሚወክላት ክለብ ሳይኖራት ለአራት ዓመታት ቆይታ ነበር። አሁን ይህ ክስተት የለም። ድሬዳዋ ከነማ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚወክላትን ድሬዳዋ ከነማን ይዛ ወደ ሊጉ ብቅ ብላለች። ውቢቷ እና ሞቃታማዋ ድሬዳ በጠንካራዋ እና ቆራጧ አሰልጣኝ መሰረት ማኔ የሚመራውን ድሬዳዋ ከነማን ይዛ ወደ ሊጉ የቀረበችው ተወካይዋ ቡድን ደግሞ የሊጉ ክስተት ሆኗል።

በአፍሪካ አፈር ብቸኛዋ የከፍተኛ ሊግ ሴት አሰልጣኝ የሆነችዋ መሰረት ማኒ የምትመራው ድሬዳዋ ከነማ በ13 ጨዋታዎች አምስት አሸንፎ፣ በሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ እና በአምስት ጨዋታዎች ተሸንፎ በድምሩ 18 ነጥቦችን በመያዝ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የጸሀይ መውጫው ክለብ በዚህ ዓመት በሊጉ ከተወዳዳሩ የክልል ክለቦች በሙሉ ለየት የሚያደርገው አንድም ጨዋታ በሜዳው አለመሸነፉ ነው። በሜዳው ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፎ በሶስቱ አቻ የተለያየ ሲሆን ከሜዳው ውጭ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ደግሞ ሁለቱን አሸንፎ በአምስቱ ተሸንፏል።

ይህ አኃዝ የሚያመለክተው የምስራቁ ክለብ ከሜዳው ሲወጣ እግሩ እንደቄጤማ የሚንቀጠቀጥ መሆኑን ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በቤቱ የማይደፈር መሆኑን ነው። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ የአሰልጣኘ መሰረት ማኔ ልጆች የተጋጣሚን ቡድን የግብ ክልል በሚገባ ለይተው የሚያውቁ አይመስሉም። በ13 ጨዋታዎች 11 ጎሎችን ብቻ ያስቆጠረው ድሬዳዋ ከነማ በምትኩ 12 ጎል ተቆጥሮበታል።

የክለቡ ትልቁ ድክመቱ የአጥቂ ክፍሉ ሲሆን በቅርቡ ከመከላከያ ድሬዳዋ ከነማን የተቀላቀለው ተከላካዩ ሲሳይ ደምሴ መጎዳቱን ተከትሎ የተከላካይ ክፍሉም ቢሆን የቡድኑ የድክመት ክፍል ነው ማለት ይቻላል። የቡድኑ ጥንካሬ ደግሞ ያለፈው ዓመት የብሔራዊ ሊጉን ኮከብ ተጫዋች ይሁን እንደሻውን የያዘው የአማካይ ክፍሉ ሲሆን ለዚህ ቦታ ጠንካራ መሆን በተለይ ከኢትዮጵያ ቡና ተገፍተው የሄዱት ዳዊት እስጢፋኖስ እና ዮናስ ገረመው አስተዋጽኦ ይጠቀሳል።

በአጠቃላይ የድሬዳዋ ከነማ እግር ኳስ ክለብ የግማሽ ዓመት ቆይታ ከተጠበቀው በላይ ብቃት ያሳየ ቢሆንም የቡድኑ ስብስበ ግን ጥራት የሚጎድለው ሆኖ ታይቷል። በተለይ የአጥቂው ክፍል እጅግ የተዳከመ መሆኑ በቀጣይ የግማሽ ዓመት የሊጉ ቆይታ ክለቡን ዋጋ እንዳያስከፍለው ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ መሆኑን ያሳየ ነው።

አሰልጣኝ መሰረት ማኔም ብትሆን ካላት ጠንካራ የስነ ልቦና ዝግጅት እና ቴክኒካል ብቃት በተጓዳኝ በተደጋጋሚ ጊዜ የምትፈጽማቸው ታክቲካል ስህተቶች ታይተዋል። የአሰልጣኟ ታክቲካል ስህተቶች ብዙ ጊዜ ጎልተው የሚታዩት በተጫዋች ቅያሪ ላይ ሲሆን ቡድኑ መመራት ሲጀምር በማነሳሳትና ውጤት ለመቀየር ጥረት በማድረግ በኩልም ድክመቶች ታይተውባታል። ከዚህ በተረፈ ግን አሰልጣኝ መሰረት ማኔ እውነትም “የቡድኑ መሰረት” ነበረች ማለት ይቻላል።

የቡድኑ ኮከቦች ይሁን እንደሻው እና ሄኖክ አዱኛ

 

አዳማ ከነማ ሰይጠበቅ ወጥቶ ሳይጠበቅ የተመለሰ

የዚህ ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ጎል አግቢ፣ በሊጉ ታሪክ ከፍተኛ ጎል ያስቆጠረው፣ በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በፍቅር የሚወደደው እና የበረኛ ጠላቱ አንጋፋው ታፈሰ ተስፋዬ በዚህ ዓመት ከሀዋሳ ከነማ ለቆ አዳማ ከነማን ተቀላቀለ። ለአንድ የውድድር ዓመት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ቆይታ አድርጎ ለክለቡ የረባ ነገር ማድረግ ባይችልም በደጋፊዎች የሚዘመርለት ቤኒናዊው ሻኪሩ አቢጊዮ አዳማ ከነማን ተቀላቀለ። በየሁለት ዓመቱ ከክለብ ክለብ የሚዘዋወረው ሚካኤል ጆርጆ ከዳሽን ቢራ አዳማ ከነማን ተቀላቀለ። ወጣቱ ቡልቻ ሹራ በዚህ ዓመት ለክለቡ ዋናው ቡድን መሰለፍ ጀመረ።

ከላይ የተጠቀሱት አራት አጥቂዎች በዚህ ዓመት ከአዳማ ከነማ ጋር በአዲስ መልክ የተዋዋሉ ሲሆን ከቀደም ብሎ በክለቡ የቆዩ እንደ ታከለ አለማየሁ እና ዮናታን ከበደ አይነት አጥቂዎች በክለቡ ይገኛሉ። በአጠቃላይ ስድስት አጥቂዎችን ይዞ ውድድሩን የጀመረው አዳማ ከነማ የዓመቱን የመክፈቻ ጨዋታ በሜዳው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አካሂዶ በወንድወሰን ሚልኪያስ ሁለት ጎሎች ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ነበር ውድድሩን አሃዱ ብሎ የጀመረው። በቀጣዩ ሳምንትም በሜዳው ኤሌክትሪክን አስተናግዶ ሁለት ለባዶ በማሸነፍ የድል ጉዞውን አጠናክሮ ገፋበት። በሶስተኛው ሳምንት ጨዋታው ለመጀመሪያ ጊዜ ከሜዳው ውጭ ተጫውቶ ታፈሰ ተስፋዬ በቀድሞ ክለቡ ላይ ባስቆጠራት ጎል ኢትዮጵያ ቡናን አንድ ለባዶ ሲመራ ያመሸው የአሸናፊ በቀለ ቡድን በመጨረሻ ጋቶች ፓኖም ባስቆጠራት ጎል ነጥብ ለመጋራት ተገድዷል።

ከሶስተኛው ሳምንት በኋላ በተካታይ ያካሄዳቸውን አራት ጨዋታዎች ማለትም ደደቢትን በሜዳው ሶስት ለሁለት፣ አርባ ምንጭ ከነማን ከሜዳው ውጭ አንድ ለባዶ፣ ዳሽን ቢራን በሜዳው ሁለት ለአንድ እና ሀዋሳ ከነማን ከሜዳው ውጭ ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ቀጥሎ የቆየ ቢሆንም በሊጉ ስምንተኛ ሳምንት በሜዳው ከሲዳማ ቡና ጋር አንድ እኩል ተለያየ። የዓመቱን የመጀመሪያ ሽንፈት ያስተናገደው ደግሞ በዘጠንኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሲሆን እሱም ወደ ድሬዳዋ ተጉዞ በድሬዳዋ ከነማ ሁለት ለባዶ በመሸነፍ ነው። በአጠቃላይ ክለቡ በ13 ጨዋታዎች በአራት ተሸንፎ፣ በሁለት ነጥብ ተጋርቶ በቀሪዎቹ ሰባቱን በማሸነፍ የነጥብ ድምሩን 23 በማድረስ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

አዳማ ከነማ በድሬዳዋ ከነማ ከተሸነፈ በኋላ ካካሄዳቸው አራት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ አሸንፎ በሶስቱ የተሸነፈ ሲሆን ለተከታታይ ሽንፈቱ ተጠያቂ የተደረገው አንዳንድ የክለቡ ደጋፊዎች ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር በፈጠሩት ግጭት ምክንያት አሰልጣኙ ስራቸውን ተረጋግተው እንዳይሰሩ ስላደረጋቸው ነው ተብሎ ሊነገር ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ኮከብ ሆኖ የቀረበው ታፈሰ ተስፋዬ በተደጋጋሚ የደረሱበት ጉዳቶችና ወጣቱ ታከለ ዓለማየሁ ደግሞ ሳይጠበቅ ብቃቱ ወርዶ መገኘቱ ሌላ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።

የቡድኑ ኮከቦች ታፈሰ ተስፋዬ እና ወንድወሰን ሚልክያስ

ሀዋሳ ከነማ ተጠብቆ የቀረው ቡድን

ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በማንሳቱ የሚታወቀው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከሱዳኑ ኤል ሃሊ ሻንዲ ጋር የነበረውን ቆይታ ካጠናቀቀ በኋላ ወደ አገሩ ሲመለስ ማረፊያው ኢትዮጵያ ቡና ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ውበቱ ግን ሃዋሳ ከነማን ሊያሰለጥን ተስማማ። ክለቡን በተረከበበት ዓመትም ቡድኑ የመውረድ ስጋት ፊቱ ላይ ተደቅኖ የነበረ ቢሆንም በአሰልጣኙ ልዩ ብቃትና በተጫዋቾች ተነሳሽነት ሀዋሳ ከነማ ከሊጉ ሳይወርድ ቀረ።

በዚህ ዓመትም ሃዋሳ ከነማ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ የውድድር ዓመቱን ዝግጅቱን ቀድሞ የጀመረ ሲሆን በርካታ የክለቡ ደጋፊዎችና የስፖርት ቤተሰቦች ሀዋሳ ከነማን በዓመቱ መጨረሻ ከዋንጫው ጋር እንደሚገናኝ ተስፋ ጥለውበት ነበር። በተለይ በሀዋሳው ሴንትራል ሆቴል ስፖንሰርነት የተዘጋጀው “ሴንትራል ሀዋሳ ሲቲ ካፕ”ን በበላይነት ማጠናቀቁ የክለቡን ዝግጅት ጠንካራነት አመላካች ነበር።

ፕሪሚየር ሊጉ ሲጀመር ሀዋሳ ከነማ በተከታታይ የሚያካሂዳቸው አራት ጨዋታዎች በሴንትራል ሲቲ ካፑ ያገኛቸውን ክለቦች መሆኑ እና እነዛ ክለቦችም ማለትም ሲዳማ ቡና፣ ድሬዳዋ ከነማ፣ ወላይታ ድቻ እና ሀድያ ሆሳዕና ወቅታዊ ብቃታቸውም ሆነ የቡድን ስብስባቸው ከሀዋሳ ከነማ ያነሰ በመሆኑ ከአራቱ ጨዋታዎች ዳጎስ ያለ ነጥብ ይሰበስባል ተብሎም ተጠብቆ ነበር። የሆነው ግን ተቃራኒው ነበር። በአራቱ ጨዋታዎች ክለቡ መሰብሰብ የቻለው አምስት ነጥብ ብቻ ሆነ።

የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን በሊጉ ካከናወናቸው 13 ጨዋታዎች መካከል በመከላከያ፣ በደደቢት፣ በአዳማ ከነማ፣ በኤሌክትሪክ እና በወላይታ ድቻ ሽንፈትን አስታገደ። ከሲዳማ ቡና፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከድሬዳዋ ከነማ እና ከዳሽን ቢራ ጋር ነጥብ መጋራት የቻለ ሲሆን ሳይጠበቅ ቅዱስ ጊዮርጊስንና ኢትዮጵያ ቡናን በሜዳው ማሸነፍ ችሏል። በዚህ ዓመት ሊጉን የተቀላቀለውን ሀድያ ሆሳዕናን እና ወጥ አቋም ማሳየት የማይችለውን አርባ ምንጭ ከነማንም አሸንፏል። በአጠቃላይ አራት ጨዋታዎችን አሸንፎ፣ በአራት አቻ ተለያይቶ እና በአምስት ጨዋታዎች ተሸንፎ ነጥቡን 16 በማድረስ አምስት የግብ እዳ ይዞ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የሀዋሳ ከነማ የግማሽ ዓመት የውድድር ጉዞ የታሰበውን ያህል አለመሆኑን ቀደም ባሉት ሳምንታት ሰፋ ያለ ዘገባ አቅርበን ነበር። በወቅቱ ባቀረብነው ዘገባ የክለቡን ውጤት አልባ ጉዞ ምክንያቶች ጠቅሰን ዘግበን ስለነበረ በዚህ ዝግጅታችን ማለት የምንፈልገው ነገር አይኖርም። አንድ ነጥብ ብቻ እናንሳ። ሀዋሳ ከነማ በአገሪቱ አሉ ከሚባሉ በእጣት ከሚቆጠሩ ብቃት ያላቸው አሰልጣች አንዱን የያዘ፣ እንደ ሀይማኖት ወርቁ እና ፍርዳውቅ ሲሳይ አይነት ወጣቶችንና እንደ ሙሉጌታ ምህረትና ታፈሰ ሰለሞን አይነት የተረጋጉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን የያዘ፣ ለክለባቸው ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይሉ ድጋፋቸውን የሚሰጡ ደጋፊዎች ያሉት እና በክልሉ በተለይም በከተማዋ በሀዋሳ በርካታ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣት ተጫዋቾች የሚገኙበት ክለብ ነው። ይህ ክለብ ከዚህ ዓመት ውድድር ድል በዘለለ ከላይ የተጠቀሱትን መልካም አጋጣሚዎች ለመጠቀም ግን ቆም ብሎ የሚያስብበት የማሰላሰያ ጊዜው አሁን ይመስለናል።

የቡድኑ ኮከቦች ታፈሰ ሰለሞን ብቻ

ይቀጥላል!!

ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!