Recently Posted News
  የ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዳሰሳ
መጋቢት 21, 2008

2008 . የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዳሰሳ

በይርጋ አበበ

ባለፉት ሁለት ቀናት የዘንድሮውን የፕሪሚየር ሊግ ውድድር የግማሽ ዓመት ጉዞ በተመለከተ ሙያዊ ምልከታችንን ማቅረባችን ይታወሳል። በምልከታዊ ዳሰሳችንም የሰባት ክለቦችን የግማሽ ዓመት ጉዞ የዳሰስን ሲሆን በዚህ ክፍል ደግሞ የቀሪዎቹን ክለቦች ጉዞ የምንመለከት ይሆናል።

ማትረፍ ያልቻለው ባንኩ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚወዳደደሩ ጠንካራ እና ማራኪ የኳስ ፍሰትን ከሚያሳዩ ክለቦች አንዱ የጸጋዬ ኪዳነማሪያም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው ወይም ነበር። ባንክ ያለፈው ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ሻምፒዮን ከመሆኑ በዘለለ ግን የዋንጫ ጆሮን መጨበጥም ሆነ የድል አክሊልን ለመድፋት ያልታደለ ክለብ ነው እየተባለ ይታማል። ክለቡ በዚህ የውድድር ዓመትም 13 ጨዋታዎችን አካሂዶ ስምንት ጊዜ ነጥብ በመጣል የሚስተካከለው አልተገኘም።

ነጥብ ተጋርቶ በወጣባቸው ስምንት ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር የቻለው በአራቱ ብቻ ሲሆን በቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች ደግሞ ጎል ሳያስቆጥር ነው የተለያየው። ያለፈው የውድድር ዓመት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ኮከብ ጎል አግቢ ሆነው ያጠናቀቁትን ፍሊፕ ዳውዝን እና ቢኒያም አሰፋን የያዘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከደደቢት፣ ሀዋሳ ከነማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ጋር ባዶ ለባዶ የተለያየ ሲሆን በኢትዮጵያ ቡና እና በድሬዳዋ ከነማ ደግሞ አንድ ለባዶ በሆነ ተመሳሳይ ውጤት ተሸንፏል። በዚህ ዓመት ከ13ቱ ጨዋታዎች በስድቱ ጎል ሳያስቆጥር መውጣቱ የክለቡን የአጥቂ መስመር ብቃት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ሆኗል።

ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ በወጣባቸው ሶስት ጨዋታዎችም ቢሆን ማስቆጠር የቻለው አምስት ጎሎችን ብቻ ሲሆን እነሱም ዳሽን ቢራን እና ሆሳዕና ሀድያን አንድ ለባዶ በሆነ ተመሳሳይ ውጤት እና አዳማ ከነማን አዳማ ላይ ሶስት ለሁለት ያሸነፈበት ነው። በአጠቃላይ በ13 ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለውም አስር ጎሎችን ብቻ ነው። ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ላይ የአሁኑ የክለቡ አጥቂዎች ፍሊፕ ዳውዝ እና ቢኒያም አሰፋ እያንዳንዳቸው 10 እና 11 ጎሎችን አስቆጥረው የነበረ መሆኑ ሲታሰብ በዚህ ዓመት የተጫዋቾቹ ብቃት ተቀዛቅዟል ወይም ሌላ ችግር አለ ብሎ መውሰድ ይቻላል።

በሌላ በኩል የጸጋዬ ኪዳነማሪያም ስብስብ በ13 ጨዋታዎች ዘጠኝ ጎሎችን ብቻ ያስተናገደ መሆኑ ሲታይ ደግሞ የቡድኑ ተከላካይ ክፍል ከኮከቡ ግብ ጠባቂ ኤማኑኤል ፌቦ ጋር ጠንካራ ጥምረት የፈጠረ መሆኑን አመለካች ሊሆን ይችላል። የጸጋዬ ኪዳነማሪያም እና የሲሳይ ከበደ ስብስብ የኋላ መስመሩን ያጠናከረውን ያህል በፊት በኩል ተጠናክሮ መቅረብ ችሎ ቢሆን ወይም አጥቂዎቹ እንደቀድሟቸው ግብ አነፍናፊነታቸው ባይቀንስ ኖሮ የውድድር ዓመቱ ሲጀመር “ዓላማችን ዋንጫውን ማንሳት ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡትን የአሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያምን አስተያየት እውነት ሆኖ ለማየት ተስፋ ይኖረው ነበር። ሆኖም ግን ሁለቱም አጥቂዎች በስማቸው አንድም ጎል ሳያስመዘግቡ የውድድር ዓመቱ ተጋመሰ። ቡድኑም በዓመቱ አትራፊ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ማትረፍ ሳይችል ቀጠለ። ትርፍ ሲባል የሜዳ ላይ ውጤቱን ብቻ ነው።

ሌላው በዚህ ዓመት የንግድ ባንክ ድክመት ሆኖ የታየው አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም ቀደም ብሎ ከሚታወቅበት በተለየ መልኩ ለተመልካች ማራኪ የኳስ ፍሰት የሚጫወት ቡድን ይዞ አለመቅረቡ ነው። ቡድኑ ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት የተጋጣሚን ቡድን የግብ ክልል ደጋግሞ ከመጎብኘት ይልቅ ኳስን ወደመጣችበት የሚጠልዝና በራሱ የግብ ክልል ላይ ተወስኖ የሚውል ቡድን ሆኖ ታይቷል። በተለይ ተጋጣሚውን መምራት ሲጀምር የሚያሳየው አጨዋወት አሰልችነቱን የከፋ ያደርገዋል። በሁለተኛው የውድድር አጋማሽ የተሻለውን ንግድ ባንክን ይዞ እንደሚቀርብ ግን የቡድኑ ስብስብ አመላካች ነው።

የቡድኑ ኮከቦች ፍቅረየሱስ ብርሃኑ እና ኤማኑኤል ፌቦ

የሚቆራረጠው ኤሌክትሪክ

የዛሬን አያርገውና በ1990ዎቹ መጀመሪያ የአገሪቱ ሀያል እና ጠንካራ ክለብ ነበረ። የሊጉን ዋንጫ ሁለት ጊዜ በማንሳት ታሪካዊ የሆነው ኤሌክትሪክ ወይም በቀድሞ ስሙ መብራት ኃይል በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኖ የውድድር ዓመቱን ያጠናቀቀው ዮርዳኖስ አባይ እስካሁንም ያልተደፈረ ሪከርዱን ያስመዘገበው ማለትም በአንድ የውድድር ዓመት 24 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለው በኤሌክትሪክ ማሊያ ነው። የአሁኑ የኢትዮጵያ ቡናው አምበል መስዑድ መሀመድ እና የዚህ ዓመት የሊጉ ኮከብ ጎል አግቢ ታፈሰ ተስፋዬ ተጫውተው ያለፉትም ሆነ እነ አንዋር ሲራጅ፣ ኤሊያስ ጁዋር እና ስምኦን አባይ በዚሁ ክለብ ማሊያ ነግሰው ያለፉ ኮከቦች ናቸው።

አሁን ግን ዘመኑም ሆነ ክለቡ ሌላ ናቸው። ዘመኑ ወደፊት ሲገሰግስ ክለቡ ግን እንደባለቤቱ ኤሌክትሪክ ወጥ ሆኖ ከመጓዝ ይልቅ መቆራረጥ መለያው ሆኗል። በዚህ ዓመትም ይሄው ወጣ ገባ አቋሙን ይዞ ቀጥሏል። ሜዳ ላይ ከሚያስመዘግበው ውጤት መክፋት በዘለለ በዲስፕሊን ግድፈትም ከፍተኛ ቅጣት የተጣለበት ክለብ ሊሆን ችሏል። ጎንደር ላይ ከዳሽን ቢራ ጋር ባደረገውና አንድ ለባዶ ተሸንፎ በተመለሰበት ጨዋታ ላይ በተነሳ አምባጓሮ አሰልጣኙ ብርሃኑ ባዬ እና አምበሉ አዲሱ ነጋሽ ለከፍተኛ ቅጣት ተዳርገውበታል።

ወደ ጨዋታው ስንመለስ በዚህ ዓመት ኤሌክትሪክ 13 ጨዋታ ተጫውቶ 13 ጎሎች ተቆጥረውበት በምትኩ 12 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። በአራት ጨዋታዎች ሙሉ ሶስት ነጥብ ያገኘ ሲሆን ያሸነፋቸው ቡድኖች መከላከያን እና ሆሳዕና ሀድያን በተመሳሳይ አንድ ለባዶ፣ ሀዋሳ ከነማን ሁለት ለአንድ እና አርባ ምንጭ ከነማን ሁለት ለባዶ ናቸው።

ከወላይታ ድቻ፣ ደደቢት፣ ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ የተጋራው ኤሌክትሪክ በድሬዳዋ ከነማ፣ ዳሽን ቢራ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከነማ ደግሞ ሽንፈት ያስተናገደባቸው ጨዋታዎች ናቸው።

ለተደጋጋሚ የቡድኑ ሽንፈት ዳኛን ተጠያቂ በማድረግ ውንጀላውን ለመገናኛ ብዙሃን ተናግሮ የነበረው ኤሌክትሪክ በአሁኑ ወቅት በ16 ነጥብና አንድ የጎል እዳ ዘጠንኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ሆኖም እንደ ፍጹም ገብረማሪያም እና ፒተር ንዋድኬ አይነት አጥቂዎችን የያዘው ቡድን በዚህ ወቅት መገኘት የነበረበት ከደረጃው አጋማሽ በላይ ነበር።

ኤሌክትሪክ ወጥ ላልሆነ አቋሙ ምክንያቱ የቡድኑ ስብስብ ነው። ቡድኑ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊያደርገው የሚችል የተጫዋቾች ስብስብ የሌለው መሆኑን ለማወቅ ብዙ መጓዝ አያስፈልግም። በአንድ ወይም በሁለት ጨዋታ ብቻ ወደ ስታዲየም ለሚታደም ሰው የቡድኑ ጥልቀት የሳሳ መሆኑን መረዳት አይከብደውም። ለዚህም ነው የቡድኑ ኮከቦች ብሎ ለይቶ ተጫዋቾችን ለማውጣት የተቸገርነው።

በማራኪ አጨዋወቱ የቀጠለው መከላከያ

መከላከያ እግር ኳስ ክለብ ባለፉት አራት ዓመታት ከሌሎች ክለቦች ለየት ባለ መልኩ የተረጋጋ የቡድን ስብስብ ያለው ክለብ ነው። በርካታ ተጫዋቾቹ በአንድ ክለብ ውስጥ ለረጅም ጊዜ አብረው የቆዩ ተጫዋቾች ሲሆኑ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌም ቢሆን በቡድኑ ተረጋግቶ ስራውን ሲሰራ የቆየ አሰልጣኘ ነው ማለት ይቻላል። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ቡድኑ ተግባብተው የሚጫወቱ ተጫዋቾችን መያዝ የቻለው።

ማራኪ የኳስ ቁጥጥር እና ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ የሚያደርጉ ተጫዋቾችን የያዘው አረንጓዴው ጦር በዚህ ዓመት በተለየ መልኩ የቡድኑ አጨዋወት ወደ ፊት ያመዘነ ሆኖ ታይቷል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው መከላከያ በ12 ጨዋታዎች 11 ጎሎችን ብቻ ያስቆጠረ መሆኑ የቡድኑን አጥቂ ክፍል ድክመት አለበት ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ቡድኑ ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን በማድረግ ከሌሎች ክለቦች ብልጫ የያዘ ክለብ ነው ማለት ይቻላል።

በመከላከያ ክለብ ውስጥ እንደ ባዬ ገዛኸኝ አይነት ታታሪ እና እንደ ምንይሉ ወንድሙ አይነት በቴክኒኩ የተካኑ ወጣት ተጫዋቾችን የያዘ ሲሆን፣ “ኳስን በአእምሮው ይጫወታል” የሚባለው መሀመድ ናስር እና ድካም የማያውቀው ሙሉዓለም ጥላሁን ከጉዳት ነጻ ሆነው መጫወት ቢችሉ ኖሮ ክለቡ በሊጉ አስፈሪ የአጥቂ ስብስብ ያለው ክለብ ያደርገው ነበር። ሆኖም አራቱም ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ጊዜ ለጉዳት መዳረጋቸው የአጥቂ ክፍሉ የታሰበውን ያህል ጎል እንዳያስቆጥር አድርጎታል።

አገሩን ወክሎ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ተወዳድሮ በጊዜ የተሰናበተው መከላከያ በ12 ጨዋታዎች አራት አሸንፎ፣ አራት አቻ ተለያይቶ በአራቱ ደግሞ ተሸንፏል። መከላከያን ከሌሎች ክለቦች ለየት የሚያደርገው አሸንፎ በወጣባቸው አራቱም ጨዋታዎች ጎል ያልተቆጠረበት መሆኑ ነው። ሁለቱን ጨዋታዎች ማለትም ኢትዮጵያ ቡናን እና አዳማ ከነማን አንድ ለባዶ ያሸነፈ ሲሆን ድሬዳዋ ከነማን ሁለት ለባዶ እንዲሁም ሀዋሳ ከነማን ሶስት ለባዶ ነው ያሸነፈው። አራቱንም ጨዋታዎች ያሸነፈው አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ብቻ መሆኑ ደግሞ ክስተቱን ለየት ያደርገዋል።

ነጥብ ተጋርቶ ከወጣባቸው አራት ጨዋታዎች መካከል ደግሞ በሶስቱ ጎል ሳያስቆጥር ባዶ ለባዶ ሲለያይ ከአርባ ምንጭ ከነማ ጋር ብቻ አንድ እኩል ተለያይቷል። ከመከላከያ ጋር ያለ ጎል አቻ የተለዩ ክለቦች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሆሳዕና ሀድያ እና ዳሽን ቢራ ናቸው። ከዳሽን ቢራ ጋር ባዶ ለባዶ የተለያየበት ጨዋታ ደግሞ መከላከያ ከአዲስ አበባ ውጭ ያስመዘገበው ብቸኛው ነጥብ ነው። ምክንያቱም መከላከያ በመጀመሪያው ዙር የሊጉ መርሃ ግብር ከአዲስ አበባ ውጭ የተጫወተው ሁለት ጊዜ ብቻ በመሆኑ እና አንዱን ጨዋታ በሲዳማ ቡና አንድ ለባዶ የተሸነፈ በመሆኑ ነው። 

በሲዳማ ቡና እና በኤሌክትሪክ በተመሳሳይ አንድ ለባዶ የተሸነፈው የገብረመድህን ሀይሌ ቡድን በወላይታ ድቻ ሁለት ለአንድ እና በደደቢት ደግሞ ሶስት ለሁለት ተሸንፏል። በአጠቃላይ 11 ጎሎችን ያስቆጠረው መከላከያ በምትኩ ስምንት ጎሎች ተቆጥረውበታል። በ16 ነጥብ እና በሶስት ንጹህ ጎልም የሊጉን ስምንተኛ ደረጃ መያዝ ችሏል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋርም ተስተካካይ ጨዋታ ይኖረዋል።

የቡድኑ ኮከቦች ከሌሎች ክለቦች በተለየ መከላከያ በርካታ ኮከቦችን ማስመዝገብ የሚችል ቡድን ነው። ተከላካዮቹ አዲሱ ተስፋዬ እና ቴዎድሮስ በቀለ፣ ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ፣ አማካይ ተከላካዩ በሀይሉ ግርማ እና አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ ይቀጥላል!!

 


ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!