Recently Posted News
  የሊጉ ሁለተኛ ዙር የመጀመረያ ሳምንት ውሎ
ሚያዚያ 10, 2008

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር በየምክንያቱና ሰበባሰበቡ ሲቋረጥ ቆይቶ በመጨረሻ መጋቢት አጋማሽ ላይ መጠናቀቁ ይታወሳል። ሁለተኛው ዙር መርሃ ግብር ደግሞ ባሳለፍነው ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮጵያ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ተጀምሯል። በዚ ጨዋታም ስፍር ቁጥር የሌለው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ስታዲየም ታድሞ ቡድኑን ከማበረታታቱም በላይ በክለቡ አመራሮች ላይ ቁጣውንና ተቃውሞውን ሲያሰማ አምሽቷል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ሜዳ ላይ ጥሩ ያልነበሩት ሁለቱ ቡድኖች ሙሉውን 90 ደቂቃ ባዶ ለባዶ ሊያጠናቅቁ ሲሉ የቡናው አጥቂ ሳዲቅ ሴቾ በእጅ የወረወራትን ኳስ የቀድሞው የቡና ተከላካይ ቶክ ጀምስ በእጁ በመንካቱ ፍጹም ቅጣት ምት ቡና አግኝቶ በያቡን ዊሊያም አማካኝነት ሙሉ ሶስት ነጥብ ያገኘበትን ጎል አስቆጥሯል። ያቡንም በዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ ሰባት ከፍ በማድረግ ከኮከብ ጎል አግቢዎቹ ጋር ያለውን ርቀት ማጥበብ አስችሎታል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ግንኙነታቸው ጨዋታው በተጀመረ በ28ኛው ሰከንድ ያቡን ዊሊያም ባስቆጠራት ጎል ቡና አሸናፊ የነበረ ሲሆን በቅዳሜ ምሽቱ ጨዋታቸው ደግሞ በጨዋታው መጠናቀቂያ ሰዓት ያቡን በድጋሚ የጸጋዬ ኪዳነማሪያምን ቡድን ሶስት ነጥብ የቀማበትን ውጤት አስመዝግቧል።

ከቡና እና ንግድ ባንክ ጨዋታ ውጭ ያሉት ቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ትናንት እሁድ በአዲስ አበባ ስታዲየም እና በተለያዩ የክልል ከተየሞች የተካሄዱ ሲሆን ከስድስቱ ጨዋታዎች ሁለቱ ማለትም አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከነማ እና ሆሳዕና ላይ ሀድያ ሆሳዕና ከአርባ ምንጭ ከነማ ያደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ አንድ እኩል የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ናቸው።

ድሬዳዋ ከዳሽን ቢራ

ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ያቀናው የአማራ ክልሉ ተወካይ ዳሽን ቢራ በመሰረት ማኔው ድሬዳዋ ከነማ ሶስት ለአንድ በሆነ ሰፊ ውጤት ተሸንፎ ተመልሷል። ድሬዳዋ ከነማ ሙሉ ሶስት ነጥብ ያገኙናቸውን ሶስት ጎሎች ያስቆጠሯቸው የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ዮርዳኖስ አባይ አንድ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ሁለት ናቸው። አንጋፋው ዮርዳኖስ አባይ የትውልድ ከተማውን ለብ በተቀላቀለ የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታው ላይ ጎል ማስቆጠር ሲችል ዳዊት እስጢፋኖስ በበኩሉ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ከተጓዘ በኋላ ትናንት የመጀመሪያ ጎሎችን አስቆጥሯል። ለዳሽን ቢራ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ኤዶም ነው። ድሬዳዋ ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን 21 በማድረስ አምስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ተሸናፊው ዳሽን ቢራ በበኩሉ ከስድስት የጎል እዳ ጋር 13 ነጥብ ብቻ ይዞ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሲዳማ ቡና ከሀዋሳ ከነማ

ሁለቱ የሲዳማ ዞን ክለቦች ትናንት ምሽት በሲዳማ ቡና ሜዳ ይርጋለም ላይ ተገናኝተው እንግዳው ቡድን ሁለት ለአንድ አሸንፎ ተመልሷል። የውበቱ አባተ ስብስብ አጀማመሩ የከፋ ቢሆንም የመጀመሪያው ዙር ውድድር ሊጠናቀቅ ሳምንታት ሲቀሩት ጀምሮ ግን ወደ ወጥ አቋሙ መመለስ ጀምሯል። መጀመሪያው ዙር ሜዳው ላይ ሂዶ ነጥብ ያስጣለውን ሲዳማ ቡናንም ትናንት ወደ ሲዳማ ቡና ሜዳ ሂዶ በፍርዳወቅ ሲሳይና ግርማ በቀለ ሁለት ጎሎች አሸንፎ ተመልሷል። የሲዳማ ቡናን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው ደግሞ አንዷለም ንጉሴ አቤጋ ነው።

ሀዋሳ ከነማ ተቀናቃኙን ጎረቤቱን ሲዳማ ቡናን በማሸነፉ ነጥቡን አስተካክሎ በጎል ክፍያ ብቻ ተበልጦ ምንተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሲዳማ ቡና በበኩሉ ሀዋሳ ከነማን በአንድ የጎል ክፍያ በልጦ 19 ነጥብና ሶስት የጎል እዳ ብቻ ኖሮበት ሰባተኛ ደረጃ ላይ ነው።  

ወላይታ ድቻ ከደደቢት

ደደቢትን ቦዲቲ ላይ ያስተናገደው ወላይታ ድቻ አንድ ለባዶ አሸንፎ ሸኝቶታል። ሙሉ ሶስት ነጥብ ያስገኘችዋን ብቸኛ የወላይታ ድቻ ጎል ጸጋዬ ብርሃኑ ነው ያስቆጠረው። ወላይታ ድቻ የትናንት ውጤቱን ተከትሎ ነጥቡን 23 በማድረስ አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል ደደቢት ቢሸነፍም ሁለተኛነቱን አላስጠነቀም።

መከላከያ ከኤሌክትሪክ

ሁለቱ ቡድኖች አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ባደረጉት ጨዋታ ጥበበኛው ፍሬው ሰለሞን እና ማራኪ ወርቁ ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች የገብረመድኅን ሀይሌ ቡድን ሙሉ ሶስት ነጥበ ይዞ መውጣት ችሏል። በመጀመሪያው ዙር ጨዋታቸው ኤለክትሪክ አንድ ለባዶ አሸንፎ የነበረ ሲሆን በትናንቱ ጨዋታ ግን መከላከያ ከፍጹም የጨዋታ ብልጫ ጋር ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ መውጣት ችሏል።

በመከላከያ እና ኤሌክትሪክ ጨዋታ ሌላው ክስተት ሆኖ የታየው የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች የተነሳሽነትና የመጫወት ፍላጎታቸው ወርዶ እንዲሁም ብቃታቸውም ከሚጠበቀው በታች ሆኖ መገኘቱ ነው። ለወትሮው በማራኪ የኳ ቅብብል ጨዋታቸው የሚታወቁት ኮረንረቲዎቹ በትናንትናው ጨዋታ ግን ፍጹም እግራቸው የተሳሰረ እና ለመጫወትም ፍላጎት የሌላቸው መሰለው ነበር የታዩት። ይህ እንቅስቃሴያቸው የት ድረስ እንደሚያደርሳቸው ባይታወቅም ክለቡ ግን ራሱን ሊፈትሽ እንደሚገባው ያመላከተ ጨዋታ ነበር ማለት ይቻላል። መከላከያ በ19 ነጥብና ሶስት ተጨማሪ ጎል ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ኤሌክትሪክ 16 ነጥብ ይዞ በሶስት የጎል እዳ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧለ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከነማ

የሳምነቱ ተጠባቂ ጨዋታ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የተካሄደው በሳምነቱ የመጨረሻ የውድድር መርሃ ግብር ነበር። የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የተባለው ይህ ጨዋታ ሁለት ወንድማማቾችን በተቃራኒ ጎራ ያሰለፈ ነበር። መሃሪ መና ከፈረሰኞቹ ጋር እሸቱ መና ደግሞ ከስምጥ ሸለቆው ክለብ ጋር። አንዳቸው ግራኝ ሌላኛቸው ደግሞ የቀኝ መስመር ተጫዋች መሆናቸውን ተከትሎም ሁለቱም አንዱ አንዱን ለማለፍ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲታገሉ ታይተዋል።

ወደ ጨዋታው ስንመለስ ብዙም ማራኪ ባልነበረውና ለተመልካች አዝናኝነት ባልታየበት ይህ ጨዋታ የአዳማ ከነማው ጫላ ድሪባ በጭንቅላቱ ገጭቶ በማስቆጠር አዳማን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ አዳነ ግርማ በግሩም ሁኔታ የሞከራትን ኳስ የአዳማው ግብ ጠባቂ ጆሴፍ ፔንዛ ሲተፋ በቅርብ ርቀት የነበረው የፈረሰኞቹ አማካይ ተከላካይ ምንተስኖት አዳነ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹን አቻ ማድረግ ቻለ። ከጎሏ መቆጠር በኋላ ፈረሰኞቹ ለማሸነፍ አዳማ ደግሞ ነጥቡን አስጠብቆ ለመውጣት ባደረጉት ትንቅንቅ ጨዋታው ወዳልተፈለገ አቅጣጫ አመራ። አዳማ ሰዓት በማባከን ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ጎል ለማግባት በከፍተኛ ጉጉት ላይ ሆነው ያካሄዱትን ጨዋታ ለአራት የአዳጋ ከነማ ተጫዋቾችና ለሁለት ፈረሰኞች ቢጫ ካርድ የዳረገ ሲሆን የአዳማው ግብ ጠባቂ ጆሴፍ ፒንዛ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሊሰናበት ግድ ብሎታል።

በዚህ ጨዋታ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን የዘን እንመለሳለን። በተለይ የፈረሰኞቹ ደጋፊዎች ያሳዩት በነበረው ያልተገባ ባህሪ እና ስታዲየም ውስጥ በደረሰው የሰው አካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያዎችነ ይዘን እንመለሳለን።

በሌላ የሳምነቱ ጨዋታ ሆሳዕና ሀድያ በሜዳው ከአርባ ምን ከነማ ጋር ያደረገውን ጨዋታ አንድ እኩል ተለያይቷል። ለሆሳዕና ቢኒያም ገመቹ ሲያስቆጥር ለአርባ ምንጭ ከነማ ደግሞ ተሸመ ታደሰ አስቆጥሯል። ሆሳዕና ነጥቡን ስድስት አድርሶ 14ኛ ላይ ባለበት ሲረጋ አርባ ምንጭ ደግሞ በ15 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በአጠቃላይ የመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ በ15 ጎሎች ታጅቦ ተጠናቋል። ጎል ያልተቆጠረበት ጨዋታ የለም ጎል ያላስድቆጠሩ ክለቦች ደግሞ ሶስት ብቻ ናቸው። ጎል ያላስቆጠሩት ክለቦች በሙሉ የአዲስ አበባ ክለቦች ሲሆኑ እነሱም ኤሌክትሪክ፣ ንግድ ባንክ እና ደደቢት ናቸው።

ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!