Recently Posted News
  15ኛው ሳምንት እና አብይ ክስተተቹ አስር ጎሎች ተቆጥረው አምስቱን የውጭ አገር ተጫዋቾች አስቆጥረዋል15ኛው ሳምንት እና አብይ ክስተተቹ አስር ጎሎች ተቆጥረው
ሚያዚያ 15, 2008

15ኛው ሳምንት እና አብይ ክስተተቹ

አስር ጎሎች ተቆጥረው አምስቱን የውጭ አገር ተጫዋቾች አስቆጥረዋል

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሀሙስ እና ዓርብ ከቀትር በኋላ በተካሄዱ ሰባት ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል መሪው መሪነቱን ግርጌውም የበታችነቱን ያጠናከሩበትን ውጤት አስመዝግበዋል። ዳሽን ቢራ በዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ጎሎችን ሲያስቆጥር ቡና በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ በፍጹም ቅጣት ምት ማሸነፍ ችሏል። ሲዳማ ቡና በፈረሰኞቹ የሚወሰድበትን የበላይነት ማስመለስ ሳይችል ቀርቷል። በ15ኛው ሳምንት የተካሄዱትን ጨዋታዎች አብይ ክስተቶች ከዚህ በታች ቃኝተናቸዋል።

የጎል ብዛት

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚተችባቸው በርካታ ችግሮች መካከል የአጥቂዎቹ ጎል አምክንነት አንዱ ነው። ይህ የሊጉ ድክመትም በብሔራዊ ቡድኑ ላይ ተንጸባርቆ ብሔራዊ ቡድናችን ሲገባበት እንጂ ሲያገባ ማየት እንግዳ ሆኗል። ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄዱ ሰባት ጨዋታዎች በስድስቱ ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን አንድ ጨዋታ ብቻ ያለ ጎል አቻ ተጠናቋል። በስድስቱ ጨዋታዎች አስር ጎሎች ተቆጥረዋል። ከተቆጠሩ አስር ጎሎች መካከል ደግሞ አምስቱ ኢትዮጵያዊያን ባልሆኑ ተጫዋቾች የተቆጠሩ ናቸው። ይህም ማለት ግማሹን ኢትዮጵያዊያን ያልሆኑ ተጫዋቾች አስቆጥረዋል ማለት ነው። ሌላው አስገራሚው ነጥብ ደግሞ አስሩም ጎሎች የተቆጠሩት በኢትዮጵያዊያን ግብ ጠባቂዎች መረባቸውን በሚያስጠብቁ ክለቦች ላይ ነው።

በውጭ አገር ተጫዋቾች  ከተቆጠሩ አምስቱ ጎሎች መካከል የዳሽን ቢራው ቶጓዊ አጥቂ ኤዶም ሶስቱን ሲያስቆጥር የኢትዮጵያ ቡናው ያቡን ዊሊያም እና የንግድ ባንኩ ፍሊፕ ዳውዝ ያስቆጠሯቸው ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ካስቆጠሯቸው አምስት ጎሎች መካከል ደግሞ አራቱ አጥቂዎች ሲሆኑ ማለትም ሳላዲን ሰይድ ሲዳማ ቡና ላይ፣ ታፈሰ ተስፋዬ በቀድሞ ክለቡ ኤሌክትሪክ ላይ፣ ደስታ ዮሃንስ ድሬዳዋ ላይ እና ይተሻ ግዛው ሆሳዕና ሀድያ ላይ ያስቆጠሩት። አጥቂ ሳይሆን ጎል ያስቆጠረ ብቸኛው ተጫዋች አስቻለው ግርማ ብቻ ነው።

ዳኝነት እና ሊጉ

በአንድ ወቅት የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አምበል ዳዊት እስጢፋኖስ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “ለሊጉ ውበት መጥፋት የዳኞች ብቃት ተጠያቂ ሊሆን ይችላል?” ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ ዳዊት የሰጠውን ምላሽ ማስታወስ አስፈልጎታል። በወቅቱ ዳዊት የመለሰው መልስ “ለጨዋታዎቹ መበላሸትም ሆነ ለሊጉ ውበት መጥፋት ብቸኛ ተጠያቂው ዳኛ ነው ባይባልም አብላጫውን ድርሻ የሚወስዱት ግን ዳኞች ናቸው” ብሎ ነበር።

በ15ኛው ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብርም ከታዩት ክስተቶች መካከል የዳኞች ብቃት አለመሻሻል ነው ማለት ይቻላል። አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የተካሄዱትን ሶስት ጨዋታዎች በማንሳት የተመለከትነውን ለማስታወስ ያህል ከዚህ በታች ያሉትን የዳኝነት ስህተቶች እናገኛለን።

ኢትዮጵያ ቡና እና መከላከያ ባካሄዱት ጨዋታ የዕለቱ ዳኛ የቡናው ተከላካይ ወንድይፍራው ጌታሁን ሜዳው ባለው እርጥበት ምክንያት ተንሸራቶ ሲወድቅ ኳስ በእጁ በመንካቱ ዳኛው ይህን ታሳቢ ሳያደርጉ ተጫዋቹን በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል። የወንድይፍራው በቀይ ካርድ መሰናበት ተገቢ አለመሆኑን ቆይተው የተረዱ ይመስላል በመከላከያ ላይ በርካታ በደሎችን በመፈጸም ለማካካስ ሲጥሩ ጨዋታውን ይበልጥ አበላሽተውት አመሹ።

ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከነማ ሲጫወቱ ደግሞ ጨዋታውን የመሩት ዳኛ የኤሌክትሪኩ አጥቂ ፒተር ንዋድኬ በራሱ ጥረት ያስቆጠረውን ጎል ከጨዋታ ውጭ አቋቋም የነበረ ተጫዋች አለ ብለው ጎሉን ሽረውበታል። በጎሏ መሻር ምክንያትም ኤሌክትሪክ ተሸናፊ ሲሆን ትልቅ ዋጋም ለመክፈል ተገድዷል።

ሌላውና በርካታ ስህተቶችን ሲሰሩ ያመሹት ዳኛ ደግሞ ትናንት ዓርብ አመሻሹ ላይ ንግድ ባንክንና ደደቢትን ያጫወቱት ዳኛ ናቸው። የመሃል ዳኛው ከረዳቶቻቸው ጋር መናበብ ባለመቻላቸው ከጨዋታ ውጭ አቋቋምንና ከመስመር ወጥቶ የእጅ የሚወረወር ኳስ ለየትኛው ቡድን እንደሆነ መለየት ተስኗቸው በአንድ ክስተት ሁለት ሶስት ውሳኔ ሲያሳልፉ ታይተዋል። ከዚህ በላይ ደግሞ የደደቢቱ ተከላካይ ስዩም ተስፋዬ በግልጽ በእጁ ኳስ ቢነካም ንግድ ባንክ ፍጹም ቅጣት ምት እንዳያገኝ ከልክለውታል። ተጠልፎ የወደቀው ተጫዋችና አስመስሎ የወደቀውን ተጫዋች መለየት ተስኗቸውም ለተበዳዩ የማስጠንቀቂያ ካርድ ሲሰጡም ተመልክተናል።

ከላይ የተጠቀሱትን የዳኝነት ስህተቶች ያነሳነው ጨዋታዎቹን በአካል ስለተመለከትን እንጂ በክልል ስታዲየም በተካሄዱ ጨዋታዎችም ተመሳሳዩ ስህተት እንደተፈጸመ ከየአካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። የዳኞች ማህበርም ከዚህ በኋላ በዳኞች ላይ በሚሰጠው አስተያየትና በሚተላለፈው ውሳኔ ብቻ ከመሰብሰብ የአባላቱን ብቃት ለማሳደግ የራሱን የቤት ስራ ሊሰራ ይገባል እንላለን።

ለግንዛቤዎ

የሊጉን ደረጃ ፈረሰኞቹ 33 ነጥብ ይዘው ሲመሩት አዳማ ከነማ በ27 እና ደደቢት በ25 ይከተላሉ። ወላይታ ድቻ፣ ሀዋሳ ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል። ሀድያ ሆሳዕና በስድስት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አርባ ምንጭ ከነማ፣ ዳሽን ቢራ እና ኤሌክትሪክ በእኩል 16 ነጥብ ከ11 እስከ 13ኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል። 

የከፍተኛ ጎል አግቢነቱን ደረጃ ታፈሰ ተስፋዬ ከአዳማ ከነማ በአስር ጎል ሲመራ የፈረሰኞቹ አዳነ ግርማ እና የኢትዮጵያ ቡናው ያቡን ዊሊያም እኩል ስምንት ጎሎችን ይዘው ይከተላሉ።

 ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!