Recently Posted News
  ዋልያዎቹን ከዮሐንስ በኋላ ማን ይመራቸዋል?
ሚያዚያ 21, 2008

በይርጋ አበበ

የአቶ ጁነዲን ባሻ እና ተክለወይን ካቢኔ አሰልጣኘ ዮሃንስ ሳህሌን ከእነረዳቶቹ አሰናብቷል። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት ዋልያዎቹ አሰልጣኝ አልባ ናቸው። ከ40 ቀናት በኋላ ደግሞ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኬሴቶ ብሔራዊ ቡድን ጋር ይጫወታሉ።በእነዚህ አጭር ቀናት ውስጥም ፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ አሰልጣኝ እንደሚቀጥር ይጠበቃል። ለመሆኑ ዋልያዎቹን በቋሚነት የትኛው አሰልጣኝ ቢመራቸው የተሻለ ውጤት ሊያስመዘግቡ ይችላሉ ለሚለው ጥያቄ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ከዚህ በታች ካሉት አሰልጣኞች አንዳቸው ቢሆኑ ይበጃል የሚል ድምዳሜ ደርሷል። አንባቢያን ደግሞ ሀሳባቸውን ከእነ ምክንያታቸው ቢያቀርቡ እናስተናግዳለን ምክንያቱም ይህ የአገር ጥሪ ነው።

አስራት ኃይሌ
Asrat Haile


የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስና ህንጻ ኮንስትራክሽን አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ የህይወት ዘመኑን ሙሉ ያሳለፈው ከእግር ኳስ ጋር በተያያዘ ነው። አስራት ከድሬዳዋ እስከ አዲስ አበባ ባሉ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን በተለይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ጋር እጅግ ስኬታማ የተጫዋችነት ዘመን አሳልፏል። ጠንካራ እና ፍርሃት ሲያልፍ የማይነካው አስራት ሀይሌ በተጫዋችነት ዘመኑ በተለይ ብሔራዊ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ለአፍሪካ ዋንጫ ያሳለፈ ተጫዋች ነበር።

አስራት በአሰልጣኝነት ዘመኑም በርካታ ክለቦችን አሰልጥኖ ከዋንጫ ጋር ያስተዋወቀ አሰልጣኝ ነው። እሱ እያሰለጠነው የዋንጫ ጆሮ ያልጨበጠ ክለብ የለም። በተለይ ከፈረሰኞቹ ጋር ባሳለፋቸው ጊዜያት ስምንት ጊዜ ከዋንጫ ጋር የተገናኘ ሲሆን በግሉም በተደጋጋሚ ጊዜ የኮከብነት ክብርን የተጎናጸፈ አሰልጣኝ ነው።

አስራት በብሔራዊ በቡድን አሰልጣኝነቱ በወር 1350 ብር እየተከፈለው ለስድስት ጊዜያት ብሔራዊ ቡድኑን አሰልጥኗል። በእነዚህ ጊዜያትም ሁለት የሴካፋ ዋንጫዎችን በሁለት ወር ዝግጅት ማንሳት ችሏል። በ2008 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ቡድኑ ከጫፍ ደርሶ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ድክመት ምክንያት ቡድኑ በእር በእርስ ጦርነት እየታመሰች በነበረችው ላይቤሪያ እንዲጫወት በመደረጉ ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድሉ ያመለጠው አሰልጣኝ ነው። በወቅቱም ጨዋታው በገለልተኛ ሜዳ እንዲካሄድ ፌዴሬሽኑ ለካፍ ደብዳቤ እንዲጽፍ ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ገልጿል።

የአሰልጣኙ ድክመት

አስራት ሀይሌን በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ከሚያነሱበት ድክመት መካከል ነገሮችን እንዳመጣጣቸው ፊት ለፊት የሚጋፈጥ መሆኑ አንዱ ነው። ይህም የአሰልጣኙን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አነስተኛ እንዲሆን ያደርገዋል ተብሎ ይተቻል። ሌላው የአሰልጣኙ ድክመት የሚባለው የሚገነባቸው ቡኖች ሀይልንና ፍጥነትን እንጂ ማራኪ የኳስ ቅብብልን መሰረት ያደረገ አይደለም እየተባለ ነው።

ሰውነት ቢሻው
Sewnet Bishaw


በክለብ እግር ኳስ እና በብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ የተለያየ ገጽታ ያለው አሰልጣኝ ቢኖር አቶ ሰውነት ቢሻው ናቸው። በቅርቡ የካፍ ኢንስትራክተር ዮሆኑት ሰውነት ቢሻው በክለብ እግር ኳስ ዘመናቸው ስኬታማ እንዳልነበሩ ማሳያቸው ትራንስ ኢትዮጵያ የቀድሞው መብራት ሀይል እና ኒያላ የተባሉ ክለቦችን እያሰለጠኑ ወደ ታችኛው ሊግ ማውረዳቸው ነው። እንዲሁም ሊጠቀስ የሚችል የዋንጫ ጆሮም ያልጨበጡ መሆናቸው ያስተቻቸዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ አሰልጣኙ ብሔራዊ ቡድኑን በመሩባቸው ጊዜያት ስኬታማ መሆን ችለዋል። አንደ የሴካፋ ዋንጫን በዋና አሰልጣኝነት ማንሳት የቻሉት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ሁለት ጊዜ ደግሞ የአስራት ሀይሌ ምክትል ሆነው የሴካፋ ዋንጫን ማንሳት ችለዋል።

የአሰልጣኙ ትልቁ ስኬት ተደርጎ የሚነሳላቸው በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ብሔራዊ ቡድኑ የሱዳን አቻውን በደርሶ መልስ አምስት እኩል ተለያይቶ ከሜዳው ውጭ ባገባ በሚለ ህግ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፋቸው ነው። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ብሔራዊ ቡድኑ ከመጨረሻዎቹ አስር የአፍሪካ ቡድኖች አንዱ ማድረጋቸው ይጠቀሳል።

የአሰልጣኙ ድክመት

አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከሚነሱባቸው ድክመቶች መካከል ታላላቅ ቡድኖችን የማሸነፍ ሪከርዳቸው ፍጹም ደካማ መሆኑ ነው። ብሔራዊ ቡድኑን እየመሩ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከአፍሪካ ምርጥ አስር ቡድኖች አንዱ ሲያደርጉትም ከቦትስዋና እና ከሴንትራል አፍሪካ ጋር ተጫውተው ሲሆን የደቡብ አፍሪካን ብሔራዊ  ቡድንም ሲያሸንፉ ቡድኑ ብቃቱ ወርዶ ስለነበረ ነው። ለአፍሪካ ዋንጫ በደረሱበት ወቅትም ከቤኒን እና ሱዳን ጋር በደርሶ መልስ ሲጫወቱ የቡድኖቹ ጥንካሬ እምብዛም ነበር።

ሌላው የአሰልጣኙ ድክመት የሚባለው ቡድናቸውን ወጥ የሆነ አሰላለፍ የሌላቸው መሆኑ ነው። ለአብነት ያህልም በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ብሔራዊ ቡድኑ ባካሄዳቸው ሶስት ጨዋታዎች አራት ግብ ጠባቂዎችን የተጠቀሙ ሲሆን ሶስቱንም ጨዋታዎች በቋሚነት የተሰለፈው ብቸኛ ተጫዋች ሳላዲን ሰይድ ብቻ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የአሰልጣኙ ስብስብ በተደጋጋሚ ጊዜ የዲሲፕሊን ግድፈት ይታይበት ነበር። በአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ቀይ ካርዶችን የተመለከተው ቡድናቸው በውጤትም በአጨዋወትም ሆነ በዲሲፕሊን ሲታይ በውድድሩ ከተሳተፉት ቡድኖች በሙሉ ዝቅተኛ ውጤት ይዞ የተመለሰ ቡድነ ነበር።

ስዩም ከበደ
Seyum Kebede


እግር ኳስን ጠንቅቆ ያውቃል ይባልለታል። የሴቶች ብሓራዊ ቡድን እና የወጣት ብሔራዊ ቡድን በመምራት ብቃቱን ማሳየት ችሏል። በየመን በቆየባቸው ጊዜያትም ስኬታማ ያደረገውን ውጤት አመዝግቦ ነው። የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ምክትል ሆኖም ብሔራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ የቻለ ሲሆን ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጋር በታክቲክና በቴክኒክ አሰላለፍ ላይ ባለመግባባት ራሱን ከኃላፊነት ካገለለ በኋላም የስዩም ሚና ምን ያህል ወሳኝ እንደነበረ አሳይቷል ሲሉ የሚናገሩለት አሉ። ምክንያቱም አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከስዩም ጋር ከተለያዩ በኋላ ቡድናቸው ወደ ታች እንጂ ወደ ላይ ሲወጣ አለመታየቱ ነው።

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ተወካይ የሆነውን አዲስ አበባ ከነማን ከተቀበለ በኋላ ባካሄዳቸው ጨዋታዎችም እጅግ ስኬታማ የሆነ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። ከኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ ፍሬዎች አንዱ የሆነው ጎልማሳው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድንን በሚገባ መምራትና ኳስን የሚወዱ ተጫዋቾችን ለይቶ ያውቃል ይባልለታል።

የአሰልጣኙ ድክመት

ስዩም ከበደ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ያለው ግንኙነት መልካም የሚባል ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ በስራው ላይ ጣልቃ እንዲገቡ ይፈቅዳል ይባላል። ይህ ደግሞ ስራውን ሊያበላሽበት እንደሚችል ግልጽ ነው። ከዚህ በተረፈ ደግሞ ስዩም የሚመራው ቡድን የሚጨነቀው ለኳስ ውበት እንጂ ለውጤት አይደለም ተብሎ ይተቻል።

ውበቱ አባተ
Webetu Abate


አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የእግር ኳስ ሊቅ ከሚባሉ የአገር ውስጥ አሰልጣኞች መካከል አንዱ ነው ይባላል። በይበልጥ የሚጠቀስለ ውጤቱ ኢትዮጵያ ቡናን ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ ያስቻለበት ብቃቱ ሲሆን ከአገር ውጭ ደግሞ ከአልሃሊ ሻንዲ ዳር ባሳለፋቸው ሁለት ዓመታት ያስመዘገበው ጥሩ ውጤት ነው።

አሰልጣኙ ከሱዳኑ ሻንዲ ጋር ስኬታማ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ወደ አገሩ ተመልሶም ከሀዋሳ ከነማ ጋር ውጤ ውረድ የበዛበት ህይወት እያሳለፈ ይገኛል። ሀዋሳ ከነማ ባለፈው ዓመት ከመውረድ ስጋት የዳነው በውበቱ አባተ መሪነት ነበር። ቡድኑ በዚህ ዓመት ከተስፋ ቡድኑ እና ከታዳጊ ቡድኑ ያሳደጋቸውን ተጫዋቾች እና የተወሰኑ አዳዲስ ተጫዋቾችን ይዞ ፕሪሚየር ሊጉን ቢጀምርም ከተጠበቀው በታች ሆኖ ተገኝቷል። ለዋንጫው ሲጠበቅ ሳይታሰብ ራሱን ከወራጅ ቀጠናው ውስጥ የተገኘው ሀዋሳ ከነማ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ውጤታማ እየሆነ ይገኛል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሚመራው ቡድን ሁሉ ስኬታማ ጊዜያትን እያሳለፈ መሆኑ በርካቶች ለብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ግምታቸውን ከሰጧቸው አሰልጣኞች አንዱ ነው። አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ብሔራዊ ቡድኑን በሚመሩበት ወቅት የእሳቸው ምክትል ሊሆን እንደሚችል ሰፊ ግምት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ሳይታሰብ ሌላ ሰው ቦታውን እንዲይዝ ተደረገ። አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ብሔራዊ ቡድኑን ለማሰልጠን ከመማማቱ በፊት የቅድመ ግምቱን አግኝተው ከነበሩት አሰልጣኞች አንዱ ውበቱ አባተ ነበር።

የአሰልጣኙ ድክመት

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ካለው ጠንካራ ጎን በተጓዳኝ ቡድኑን ወጥ በሆነ መንገድ አለመምራቱ ይነሳል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ተጫዋቾችን የሚይዝበት መንገድ ቡድኑን የሚከፋፍል ነው ተብሎ ይተቻል።

ጸጋዬ ኪዳነ ማሪያም
Tsegaye Kidanemariam


በተጫዋችነት ዘመኑ ማራኪ ጨዋታን ይጫወት እንደነበረ የሚያወሱት አስተያየት ሰጪዎች ጸጋዬ ኪዳነማሪያም አገሪቱ ካፈራቻቸው ኮከብ አሰልጣኞች አንዱ ነው ይላሉ። ከሀረር ከነማ እና ከኢትዮጵያ ቡና ክለቦች ጋር ሆኖ ማራኪ ኳስ የሚጫወት ቡድን እነደገነባ የሚነገርለት ጸጋዬ ኪዳነማሪያም አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የብሔራዊ ቡድን ስራውን ከመያዙ በፊት ቡድኑን ለማሰልጠን እድል ከነበራቸው አሰልጣኞች አንዱ ነበር። በሁለተኛ ደረጃም የተመረጠው እሱ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ ጋር ተረጋግቶ እየሰራ የሚገኘው ጸጋዬ ኪዳነማሪያም ብሔራዊ ቡድኑን ቢያሰለጥን ለተመልካች አዝናኝ እግር ኳስን ያስኮመኩማል ተብሎ ይጠበቃል። ይህን ደግሞ በክልብ ፉትቦሉም አሳይቷል።

የአሰልጣኙ ድክመት

የአሰልጣኙ ትልቁ ድክመቱ የሚባለው በአሰልጣኝነት የዋንጫ ጆሮ ለመጨበጥ አለመታደሉ ነው። ቡድን እየመራ ዋንጫ አነሳ ተብሎ ሊጠቀስለት የሚችለው ቢኖር የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ነው። አገሪቱ ውስጥ የአጥቂ እና የግብ ጠባቂ ችግር እንዳለ በግልጽ እየታየ ባለበት በዚህ ወቅት አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም ብሔራዊ  ቡድኑን እንዲያሰለጥን እድሉን ቢያገኝ ምናልባት ስኬታማ ላይሆን ይችላል እየተባለ ይታማል።

ከእነዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሁለቱ አብርሃሞች አብርሃም ተክለኃይማኖት እና አብርሃም መብራቱ እንዲሁም ገብረመድህን ሀይሌም እድሉን እንደሚያገኙ ተስፋ የተጣለባቸው ናቸው።

ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
eliyas mukerem [663 days ago.]
 በመጀመሪያ።የዩሐንስ ሳሕሌ በዚን ሳአት መባረር አግባብ አይደለም ሌላው የብሔራዊ ቡዳናችን ውድቀት ዩሐንስ ምንም አያስጠይቀውም።ሌላው።ብሔራዊ ቡድናችን።አሑን የተዘረዘሩት።ኮቾች ቀርቶ።የባርሴሎና ሙሉ መጥቶ ቢኢዘው።የሚመጣ።ለውጥ የለም።ምክንያት።ባለንበት።ዘመን።ፉትቦል የደረሰበት ደረጃለመድረስ ወይም ተፎካካሪ ለመሖን እግርኩአስ ከሚፈልጋቻው ፋሲሊቲዎች።መሰረታዊ ነገሮች።100%እስካሑን።እኛ ያለን 3%ብቻነው።እነሱም።ደጋፊ።ተጫዋች።ያልተገራ።እናም።ኩአስ።ቆዳው።እና።97%ሳሰራ።ዩሐንስ።ምን።

Asrat Nigusse Berhane [662 days ago.]
 ማንም መጣ ማንም ተባረረ የኢ/ያ እግር ኳስ ለማሳደግ የሚፈልግ አካል ወይም ዜጋ ማድረግ ካለበት ከታች ማለትም ከታዳጊ፤ ለወደፊቱ የሚሆኑ ልጆች ተመርጠው ቢበቁልን፡፡ አሁን አስራ ስምንት አመት የሞላቸው እገሌ ይችላል እየተባለ መምረጥ ለአገር ውስጥ ክለቦች ካልሆነ ለኢ/ያ ብሔራዊ ቡድን ተወዳዳሪ ሆነው ሊቀርቡ አይችሉም፡፡ ልክ ዳሽን ቢራ ከአርስናል ጋር የጀመረው በጎ ስራ በአገር ደረጃ ተሰርቶበት አመርቂ ውጤት ለወደፊቱ ይመጣል ብየ አምናለሁ፡፡ በዚህ በጣም እርግጠኛ ነኝ እንዲሁም አሰልጣኞቻችን እገለ ኢንስትራክተር ነው እገሌ አይደለም ከማለት አልፎ ከላይ በገለፅኩት መንገድ በቁ ባለሙያዎች ፤ከታች እውቃታቸውን አሳድገው የመጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ እና ብቁ እንዲሆኑ ብዙ መስራት ከመንግሰትም ሆነ እግር ኳሱ ከሚመለከታቸው አካላት ፤ ባለሀብቶች ብዙ ይጠበቃል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ግን ለምን ፔፕ ጋርድዮላ ወይም ጆሴፍ ሞሪንሆ ወይም አርሴን ቬንገር አይቀጠርም፡፡ ምንም ለውጥ አይመጣም፡፡ እኔ የምለው ግን ልክ አንዱ ከአርሴናል የመጣ የስልጠና ክፍል ባለደርባ ከዳሽን ቢራ ጋር የሰሩት ዶክሜንተሪ ፍልም ተመልክቼ ነበር እና ባልሳሳት ያኔ ሲናገር "ልጆቹ ችሎታ አላቸው፤ ትንሽ በመናገር፤ ብዙ ኳስ እንዲጫወቱ አድርጉ ነበር ያለው" ሙሉ በሙሉ ሀሳቡን እደግፈዋለሁ፡፡ ኢ/ያ ኢ/ሔር ይባርክ!!

Asrat Nigusse Berhane [662 days ago.]
 ማንም መጣ ማንም ተባረረ የኢ/ያ እግር ኳስ ለማሳደግ የሚፈልግ አካል ወይም ዜጋ ማድረግ ካለበት ከታች ማለትም ከታዳጊ፤ ለወደፊቱ የሚሆኑ ልጆች ተመርጠው ቢበቁልን፡፡ አሁን አስራ ስምንት አመት የሞላቸው እገሌ ይችላል እየተባለ መምረጥ ለአገር ውስጥ ክለቦች ካልሆነ ለኢ/ያ ብሔራዊ ቡድን ተወዳዳሪ ሆነው ሊቀርቡ አይችሉም፡፡ ልክ ዳሽን ቢራ ከአርስናል ጋር የጀመረው በጎ ስራ በአገር ደረጃ ተሰርቶበት አመርቂ ውጤት ለወደፊቱ ይመጣል ብየ አምናለሁ፡፡ በዚህ በጣም እርግጠኛ ነኝ እንዲሁም አሰልጣኞቻችን እገለ ኢንስትራክተር ነው እገሌ አይደለም ከማለት አልፎ ከላይ በገለፅኩት መንገድ በቁ ባለሙያዎች ፤ከታች እውቃታቸውን አሳድገው የመጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ እና ብቁ እንዲሆኑ ብዙ መስራት ከመንግሰትም ሆነ እግር ኳሱ ከሚመለከታቸው አካላት ፤ ባለሀብቶች ብዙ ይጠበቃል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ግን ለምን ፔፕ ጋርድዮላ ወይም ጆሴፍ ሞሪንሆ ወይም አርሴን ቬንገር አይቀጠርም፡፡ ምንም ለውጥ አይመጣም፡፡ እኔ የምለው ግን ልክ አንዱ ከአርሴናል የመጣ የስልጠና ክፍል ባለደርባ ከዳሽን ቢራ ጋር የሰሩት ዶክሜንተሪ ፍልም ተመልክቼ ነበር እና ባልሳሳት ያኔ ሲናገር ልጆቹ ችሎታ አላቸው፤ ትንሽ በመናገር፤ ብዙ ኳስ እንዲጫወቱ አድርጉ ነበር ያለው ሙሉ በሙሉ ሀሳቡን እደግፈዋለሁ፡፡ ኢ/ያ ኢ/ሔር ይባርክ!!

ዶሮኩስ [650 days ago.]
 ስዩም ከበደን እድል ለግሱት እስኪ፥ ይታይ። ከውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርተው ውጤታቸው ያልተዩትን ከመኮልኮል ሠርቶ ውጤት ያመጣውን ለምን ኣይሞርኩም። እኔ ብጠየቅ «ስዩም ከበዴን» በኣስር ጣቶቼ እመርጣለሁ በኣሁኑ ግዜ።

ዶሮኩስ [650 days ago.]
 ስዩም ከበደን እድል ለግሱት እስኪ፥ ይታይ። ከውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርተው ውጤታቸው ያልተዩትን ከመኮልኮል ሠርቶ ውጤት ያመጣውን ለምን ኣይሞርኩም። እኔ ብጠየቅ «ስዩም ከበዴን» በኣስር ጣቶቼ እመርጣለሁ በኣሁኑ ግዜ።

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!