Recently Posted News
  በዳግሚያ ትንሳዔ የሚካሄደው ታላቁ ሸገር ደርቢ እና የቅርብ ሩቅ ታሪክ
ሚያዚያ 29, 2008

ክፍል አንድ

በይርጋ አበበ

የፊታችን እሁድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ታዋህዶ እምነት ተከታዮች እለቱ የዳግሚያ ትንሳኤ በዓል ነው። በመሆኑም እለቱን የተቀደሰ ይሉታል። በዚሁ ዕለት ደግሞ ታሪካዊው እና ዕድሜ ጠገቡ አዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ አስር ሰዓት ላይ ሌላ ቅዱስ ጦርነት ያካሂዳል። የዚህ ቅዱስ ጦርነት ተፋላሚዎች ደግሞ የበርካታ ክለብ ደጋፊ ባለቤት የሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለቦች ናቸው። ሁለቱ ክለቦች በሜዳ ላይ እነ ከሜዳ ውጭ የሚፈጥሯቸው አተካሮዎች ለአዲስ አበባ እና ለፌዴራል ፖሊስ አባላት ትልቅ የቤት ስራ ሲሆኑ ለዓመታት ከእንቅልፉ መንቃት ላልቻለው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ ትልቅ የገቢ ምንጭ ናቸው። እነዚህ ቡድኖች ከነገ በስቲያ የሚያደርጉትን ጨዋታ ከማካሄዳቸው በፊት ስለ ሁለቱ ክለበፐች የቅርብ ሩቅ ግንኙነቶችና ተያያዥ ታሪኮችን ከዚህ በታች አቅርበናቸዋል። ለአንባቢያን ደግሞ የማሸነፉም ዕድል እንዲገምቱ ዕድሉን አበርክተንላቸዋል።

ለሁለቱም ክለቦች የተጫወቱ ተጫዋቾች

በዓለማች እንዳሉት ታላላቅ ደርቢዎች ሁሉ በአገራችንም እንደ እግር ኳሳችን የኋልዮሽ እድገት የራሳችን ታላቅ ደርቢ የምንለው የሁለቱን ክለቦች ፍልሚያ ነው። ቡናም ሆነ ጊዮርጊስ አንደኛው በሌላኛው ላይ ፖለቲካዊም ሆነ ሀይማኖታዊና የብሔር ልዩነት የማይታይባቸው ክለቦች ናቸው። ሆኖም ግን ሁለቱም አንዱ የሌላኛው ባላንጣ እንጂ ወዳጅ ሆኖ አያውቅም። ይህን ባላንጣነታቸው የፈጠረው ደግሞ የመደብ የሀይማኖት ወይም የነገድ ልዩነት ሳይሆን ኳስ ብቻ ነው። የእግር ኳስ ባላንጣነት በኳስ ብቻ መፈጠሩ ጤነኝነት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ምክንያቱም በሁለቱም ክለቦች ውስጥ የመደብ ልዩነት የሌለ ሲሆን ክለቦቹ ህብረ ብሔራዊም ናቸው። በሀይማኖትም ቢሆን ለቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ለኢትዮጵያ ቡና አገሪቱ ውስጥ የሚከበሩ ሁሉም ሀይማኖቶችን የሚከተሉ ተጫዋቾችና አመራሮች ያላቸው ክለቦች ናቸው። ለዚህ ነው የሁለቱ ክለቦች ባላንጣነት በእግር ኳስ ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑ ጤነኝነት ነው ያልነው።

ከላይ ስለ ክለቦቹ ባላንጣነት ከተነጋገርን የትኞቹ ተጫዋቾች ናቸው ለሁለቱም ክለቦች ተጫውተው ያለፉት የሚለውን ጥያቄ ከዚህ በታች ለማንሳት እንሞክራለን። በዚህ ርዕስ ላይ አጭር ጽሁፍ መጻፍ ከባድ ቢሆንም የቅርብ ጊዜያቱን ብቻ ለማንሳት እንገደዳለን።

አሰግድ ተስፋዬ

Asegid Tesfaye


አሰግድ ተስፋዬ የቡና ደጋፊዎች በሙሉ ልባቸው የሚወዱትና የሚያከብሩት አጥቂ ነው። መሮጥ የማይወደውና ጉልበተኛው የድሬዳዋ ተወላጁ አሰግድ ተስፋዬ ከትውልድ መንደሩ ወጥቶ ለብሔራዊ ኩራት ከመሆኑ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከተው የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ነው። በአስራት ኃይሌ መልማይነት ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው አሰግድ ተስፋዬ ከፈረሰኞቹ ጋር እኩል መጋለብ ባለመቻሉ በመድን ኢትዮጵያ በኩል አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ ቡና መግባት ችሏል። በቡና ውስጥም የራሱን ታሪካዊ አሻራ ማሳረፍ የቻለ ሲሆን እስካሁንም ድረስ በክለቡ ደጋፊዎች ከልብ የሚወደድ ተጫዋች ነው።

ታዲዮስ ጌታቸው

Tadios Getachew


አሁን ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው ግዙፉ ግብ ጠባቂ በፈረሰኞቹ ደጋፊዎች የሚወደድ ቢሆንም ቡናማዎቹ ግን ስሙን መጥራት አይፈልጉም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደያስ አዱኛን ማስፈረሙን ተከትሎ ለቡና አሳልፎ የሰጠው ታዲዮስ ለሁለት ዓመታት ለመጫወት ከተስማማ በኋላ አንዱን ዓመት እንኳ በቅጡ ሳይደፍን ነበር ወደ አሜሪካ የሄደው። ይህ ደግሞ ለቡናማዎቹ ትልቅ ክህደት ነው። ለዚህም ነው የሚጠሉት።በሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች የተለያዬ ስሜት የሚያስተናግደው ታዲዮስ ጌታቸው በሁለቱም ክለብ ማሊያ ከተጫወቱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።

አንተነህ አላምረው
ጉልበትን ከድፍረት ጋር ቀላቅሎ የሚጫወተው አንተነህ አላምረው በርካታ አሰልጣኞች የሚወዱት ተጫዋች ነው። ይህ አማካይ ተከላካይ በአገር ቤት ተዘዋውሮ ከተጫወተባቸው ክለቦች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ይገኙበታል። የ1997 ዓ.ም የሴካፋ ዋንጫ ኢትዮጵያ ዋንጫውን ስታነሳ ኮከብ የነበረው አማካይ ተከላካዩ በሁለቱም ክለቦች ተጫውቶ ስኬታማ እና ተወዳጅ መሆን የቻለ ተጫዋች ነው።ነው።

ምንያህል ተሾመ
Menyahil Teshome

የቡና ደጋፊዎች የሚሰድቡኝ ስለሚወዱኝ ነው ብሎ ለመገናኛ ብዙሃን የተናገረው የኳስ አርቲስቱ ምንያህል ተሾመ በቡና ክለብ ውስጥ አሻራውን ያሳረፈ ኮከብ ነው። በእግር ኳስ ዘመኑ በትልቅ ደረጃ ለሶስት ክለቦች ብቻ የተጫወተው ምንያህል ተሾመ ከኢትዮጵያ ቡና ከወጣ በኋላ ማረፊያውን ደደቢት አድርጎ ለሁለት ዓመታት ብቻ ከቆየ በኋላ ወደ ፈረሰኞቹ ካምፕ የተዘዋወረው የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ ነበር። ምንያህል ተሾመ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና ጋር ካነሳ በኋላ በደደቢት እና በፈረሰኞቹም ተዘዋውሮ ዋንጫውን ማንሳት ችሏል። ይህ ኳስ አቀጣጣይ ተጫዋች በደጋፊዎች መካከል ለሚነሳ ብሽሽቅም ጥሩ ማቀጣጠያ ነው ማለት ይቻላል።<

አሸናፊ ግርማ
Ashenaf Girma

የአሸናፊ ግርማ የእግር ኳስ ታሪክ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ቀጭኑ ልጅ ከድሬዳዋ ከነማ በኋላ በመብራትኃይል በኩል አድርጎ ቡናማዎቹን ከተቀላቀለ በኋላ ሜዳ ላይ በሚያሳየው ክህሎት የተማረኩት የቡና ደጋፊዎች በልጁ ፍቅር ለመውደቅ ረጅም ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር። ከቡና ጋር ስኬታማ የውድድር ጊዜያትን ያሳለፈው አሸናፊ ግርማ ለባልንጀሮቹ በሚሊሜትር የተመጠኑ ኳሶችን በአጭርም ሆነ በረጅም ማቀበል ተክኖበታል።

ይህ አማካይ ግን በአንድ ወቅት ከቡና ወጥቶ ወደ ጊዮርጊስ ከገባ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ቀድሞ ክለቡ መመለስ ችሏል። ከአንድ ወር ያልበለጠ ጊዜ ከፈረሰኞቹ ጋር ያሳለፈው የድሬደዋ ተወላጁ በቅዱስ ጊዮርጊስ የሚጠብቀውን እንዳላገኘ ባሳተመው መጽሃፉ ላይ አስነብቧል። አሸናፊ አሁኑን የናሽናል ሴሜንት ስራ አስኪያጅ ነው።

ኤሊያስ ማሞ
Anteneh Alamirew

ዳዊት እስጢፋኖስ ከቡና ከለቀቀ በኋላ እና መስዑድ መሀመድ በመደበኛነት መሰለፍ ባለመቻሉ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ፈጣሪ አማካይ ቢኖር ኤሊያስ ማሞ ነው ማለት ይቻላል። የ2008 ዓ.ም የሴካፋ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋቹ ኤሊያስ ማሞ ቡናን የተቀላቀለው የዛሬ ሁለት ዓመት ከንግድ ባንክ ቢሆንም የእግር ኳስ ታሪኩ ግን ከፈረሰኞቹ ጋር የተያያዘ ነው። ከፕሮጀክት አድጎ ለፈረሰኞቹ መሰለፍ የጀመረው ኤሊያስ ማሞ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ጥሩ የሚባል ጊዜ እያሳለፈ ነው። ከኤሊያስ በተጨማሪም ወጣቱ ዮሴፍ ደሙዬ ከፈረሰኞቹ ካምፕ ለቆ በንግድ ባነክ በኩል ወደ ቡና የተዘዋወረ ተጫዋች ነው።

ይቀጥላል!!

ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!