Recently Posted News
  በዳግሚያ ትንሳዔ የሚካሄደው ታላቁ ሸገር ደርቢ እና የቅርብ ሩቅ ታሪክ
ሚያዚያ 30, 2008

ክፍል ሁለት

በትናንትናው ዝግጅታችን ስለፈረሰኞቹ እና ቡናማዎቹ ጨዋታ መጠነኛ ዳሰሳ አቅርበን ነበር። ከትናንት የቀጠለውን ክፍል ደግሞ እነሆ 

የሁለቱ የቅርብ ጊዜያት ግንኙነት

ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ስኬታማው ክለብ ነው። ሊጉን ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ከተቀላቀለ በኋላ ለ12 ጊዜያት ዋንጫውን ማንሳት ችሏል። በሊጉ የሚወዳደሩ ክለቦች በሙሉ ያላገኙትን የዋንጫ ብዛት የአሁኑ የፈረሰኞቹ አምበል ደጉ ደበበ ራሱ ብቻውን ስምንት ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ችሏል። ቡና በበኩሉ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

ሁለቱ ክለቦች ነገ ከመገናኘታቸው በፊት ከዚህ ቀደም ከተገናኙባቸው ግጥጥሞሽ መካከል ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ያሉትን ብቻ ለማየት እንሞክራለን። በ2003 ዓ.ም ውበቱ አባተ የሚያሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና በፈረሰኞቹ መረብ ላይ ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ጎሎችን አስቆጥሮ በምትኩም ሁለት ገብቶበታል። በአጠቃላይ የመጀመሪያ ግንኙነታቸውን ሁለት እኩል አጠናቀው በሁለተኛው ደግሞ ባዶ ለባዶ ተለያይተዋል።

በ2004 ዓ.ም ፈረሰኞቹ የበላይነታቸውን የያዙበት ዓመት ነው። የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በፈረሰኞቹ ሁለት ለባዶ አሸናፊነት ያጠነቀቁ ሲሆን የመልሱን ጨዋታ ደግሞ በድጋሚ ፈረሰኞቹ ሶስት ለባዶ አሸንፈዋል። በዚህም በውድድር ዓመቱ ፈረሰኞቹ ካስመዘገቧቸው ነጥቦች መካከል ስድስቱ የወሰዱት ከቡና ነው። የሊጉን ዋንጫ ደደቢት ባነሳበት በ2005 ዓ.ም ደግሞ በመጀመሪያው ዙር ባዶ ለባዶ የተለያዩት ሁለቱ ክለቦች በሁለተኛው ዙር ግን ሙሉዓለም ጥላሁን ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል በምክትል አሰልጣኙ ካሊድ መሃመድ የሚሰለጥነው ቡና አሸናፊ መሆን ችሏል።

ዋንጫውን በደደቢት ከተቀማ ከአንድ ዓመት በኋላ ክብሩን ያስመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስም በ2006 ዓ.ም ኢትዮጵያ ቡናን ሁለት ለባዶ እና ሁለት ለአንድ ማሸነፍ ችሏል። ባለፈው ዓመት ደግሞ የመጀመሪያው ዙር ላይ አስቻለው ግርማ አስቆጥሮ ቡና ሶስት ነጥብ ሲያገኝ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ብሪያን አሙኒ እና በሀይሉ አሰፋ ሁለት ጎሎችን አስቆጥረው ፈረሰኞቹ ማሸነፍ ቻሉ። በዚህ ዓመት የመጀመሪያው ዙር አምስተኛው ሳመንት ላይ ተገናኝተው ባዶ ለባዶ ተለያይተዋል። ነገስ?
የፈረሰኞቹ ወሳኝ ተጫዋቾች በ36 ነጥብ ሊጉን የመመመራው ቀዱስ ጊዮርጊስ ለሰበሰበው ነጥብ የቡድኑ አባላት እንደ ቡድን የሰሩት ስራ ከፍተኛ ቢሆንም በተለየ መልኩ ግን የተወሰኑ ተጫዋቾች ሊነሱ ይችላሉ። ከእነዚህ መካከል ለዓመታት አልደፈር ያለው የፈረሰኞቹ በር ሲሆን የበሩ ጠባቂ ደግሞ ሮበርት ኦዶንካራ ነው። ዩጋንዳዊው ግዙፍ ግብ ጠባቂ ለአገር ውስጥ ውድድር ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እንኳን ጠንካራው ቲፒ ማዜምቤ አልበገረውም ማለት ይቻላል። ስለዚህ በዚህ ዓመትም ቅዱስ ጊዮርጊስ ላደረገው ስኬታማ የውድድር ዓመት የዚህ ግዙፍ ግብ ጠባቂ ሚና ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል። በነገው ጨዋታም በፈረሰኞቹ በኩል ከሚጠበቁት አንዱ ኦዶንካራ እንደሚሆን አያጠራጥርም።

ከደደቢት ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው በዚህ ዓመት ቢሆንም እያሳየ ያለው ብቃት ግን ለረጅም ዓመታት በክለቡ እንደቆየ ነው። ተከላካዩ አስቻለው ታመነ በዚህ ዓመት ከፈረሰኞቹ ጋር ስኬታማ ጊዜያትን እያሳለፈ ሲሆን በነገው ጨዋታም ቢሆን ድሮውንም አይናፋር የሆነውን የቡናዎችን የአጥቂ መስመር በሚገባ ሊቆጣጠር ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው የውድድር ዓመት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው መሃሪ መና በዚያው ዓመት ያሳየው ብቃት የወረደ ነበር። ቦታውንም ወጣቱ ዘካሪያስ ቱጂ የግሉ አድርጎት ነበር። በዚህ ዓመት ግን መሃሪ መና ተስሎ ቀርቧል። ረጅሙ ተከላካይ ያለ ኳስ ቀርፋፋ ቢሆንም ከአጥቂ ጋር አንድ ለአንድ ሲገናኝና ኳስ እግሩ ስር ስትገባ ወደፊት ሲገፋ ለተጋጣሚ ቡድን አስቸጋሪ ነው።

ተስፋዬ አለባቸው እና ምንተስኖት አዳነ በመሀል ሜዳ ላይ የሚኖራቸው ተጽእኖ ከፍተኛ ቢሆንም ለነገው ጨዋታ ግን ከሁለቱ አማካይ ተከላካዮች ይልቅ ጥበበኛው በሀይሉ አሰፋ በፈረሰኞቹ በኩል ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ አንጋፋው አጥቂ አዳነ ግርማ እና አዲሱ አጣማሪው ሳላዲን ሰይድም ተጠባቂዎች ናቸው።

በቡናማዎቹ በኩል ተጠባቂ ተጫዋቾች

ከዓሊ ረዲ በኋላ ሁነኛ የጎል ክልል ጠባቂ ማግኘት አልችል ብሎ ሲሰቃይ የኖረው ኢትዮጵያ ቡና በዚህ ዓመት አስተማማኝ ግብ ጠባቂ አግኝቷል ማለት ይቻላል። የቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪስተን ሄሱ ባለፉት አራት ጨዋታዎች መረቡን ማስደፈር አልቻለም። ግብ ጠባቂው በጉዳት በቆየባቸው ወራት መረቡን ማንም እንደፈለገ ሲመላለስበት የቆየው ኢትዮጵያ ቡና ከሀሪስተን መመለስ በኋላ ግን ይበልጥ ተጠናክሯል። ለዚህም ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሽንፈት ያልደረሰበት ሲሆን የተቆጠሩበት ጎሎችም ውስን ናቸው። ይህ ግዙፍ ግብ ጠባቂ በነገው ጨዋታ በቡና በኩል የሚጠበቅ ነው።

ከሲዳማ ቡና በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው አብዱልከሪም መሀመድ በክለቡ ደጋፊዎች ለመወደድ ጊዜ የወሰደበት አይመስልም። ከቀኝ መስመር ተከላካይነት በተጨመሪ በግራ በኩል እንዲከላከል ሲደረግም ሆነ የአማካይ ተከላካይነቱን ሚና ሲሰጠው በሚገባ መወጣት የሚችለው ቀዩ ልጅ የቡና ወሳኝ ተጫዋች ነው። አብዱል ከሪም ከመከላከሉ በዘለለ ኳስን ውበት ሰጥቶ የሚጫወት ሲሆን ጎል አካባቢ ሲደርስ ደግሞ ርህራሄ አያውቅም። በነገው ጨዋታ ከቡና በኩል ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ ነው።

ያለፈውን የውድድር ዓመት በብሔራዊ ሊጉ ቢቆይም ድሬዳዋ ላይ በድራጋን ፖፓዲች አይን መግባት ቻለ። ለቡና ከፈረመ በኋላም በክለቡ የኋላ መስመር ላይ እያሳየ ያለው ብቃት ለብሔራዊ ቡድን እንዲመረጥ አስችሎታል። ወንድይፍራው ጌታሁን ወይም ቦልተና ከሁለት ጨዋታ ቅጣት በኋላ ነገ ወደ ጨዋታ ሲመለስ አስፈሪ ለሆነው የፈረሰኞቹ አጥቂ ክፍል ትክክለኛ መልስ ይሆናል። የክለቡ ወሳኝ ተጫዋችም ነው።

ዕድሜው ቢገፋም ቡናን ገፍቶ መሄድ የፈለገ አይመስልም አምበሉ መስዑድ መሃመድ። በርካቶች በአመለ መልካምነቱ የሚያነሱት መስዑድ እድሜው የቱንም ያህል ቢገፋም እየቆየ እንደ ወይን ጠጅ በሚጣፍጥ ችሎታው አሁንም ቡናን እያገለገለ ይገኛል። ቡድን በመምራትም ሆነ ኳስን አደራጅቶ በመጫወት በኩል እንከን የማይወጣለት መስዑድ በነገው ጨዋታ ድረራጋን ፖፓዲች የመሰለፍ እድሉን የሚሰጡት ከሆነ ከጋቶች በተሻለ ለቡድነኑ ወሳኝ አገልግሎት መስጠት ይችላል።

በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያ ቡናን ሊለቅ ይችላል ተብሎ የሚገመተው ኤሊያስ ማሞ ሌላው በቡና በኩል ከሚጠበቁ ተጫዋቾች አንዱ ነው። ኳስን ተቆጣጥሮ ሲጫወት ለተመልካች አዝናኝ የሆነው አጭሩ ልጅ በነገው ጨዋታም ለቀድሞ ክለቡ ፈታኝ እንደሚሆን አያጠራጥርም። በአንድ አጥቂ ላይ ጥገኛ ለሆነውና ያው አጥቂውም በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ የማይሰለፍለት ቡና ጎሎችን ለማግኘት በኤሊያስ ላይ ጥገኛ ቢሆን አይገርምም። ምክንያቱም ቡና በዚህ ዓመት ካስቆጠራቸው የሊግ ጎሎች መካከል 75 በመቶ ያህሉን ያገኘው ከያቡን ዊሊያም ነው። ዊሊያም ደግሞ ነገ አይሰለፍም። ስለዚህ የነገው የቡና የጎል አምሮት ሊቆረጥ የሚችለው ያለ ማቋረጥ ኳስን በሚያንከባልለው በኤሊያስ ማሞ ላይ ነው። 

ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!