Recently Posted News
  “የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች፣ የጎንደር ህዝብ እና የዳሽን ቢራው አስራት መገርሳ ክብር ይገባችኋል”
ግንቦት 20, 2008

“ጎንደር ላይ የደረሰብን ችግር ይደርስብናል ብለን አንድም ቀን አስበን አናውቅም ነበር” መቶ ዓለቃ ፈቃደ ማሞ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የቦርድ ሰብሳቢ

“የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የጎንደር ህዝብ እና የዳሽን ቢራው አስራት መገርሳ ክብር ይገባችኋል” አቶ ሰለሞን ታምራት የደጋፊዎች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር

ክፍል አንድ

በይርጋ አበበ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጎንደር ላይ የተገናኙት ዳሽን ቢራ እና ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለቦች በጨዋታው ሁለት እኩል ቢለያዩም ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ በተነሳ ግጭት ጨዋታውም ሆነ ከጨዋታው በኋላ የነበረው የእግር ኳስ ድባብ መልካም አልነበረም። በጨዋታው የመሃል ዳኛው የጆሯቸው አንደኛው ክፍል በድንጋይ በመፈንከቱ ጨዋታው ለ14 ደቂቃዎች ተቋርጦ እንዲቆይ ሲደረግ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላም በርካታ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችና የክለቡ ሰራተኞች በዳሽን ቢራ ደጋፊዎች ተደብድበዋል።

ከተደበደቡት የቡና ደጋፊዎች መካከል አብዛኞቹ ለከባድ ህክምና በእለቱ በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ መጥተው ቤተዛታ እና ሰናይ ሆስፒታል ገብተው እንዲታከሙ ሲደረግ ቀሪዎቹ ደግሞ በጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና በባህር ዳሩ ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይተው ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ተደርጓል። በተለይ አንድ ደጋፊ ቀኝ እግሩ ላይ በደረሰበት ከባድ ጉዳት እግሩ ውስጥ ብረት እንዲገባበት በህክምና ባለሙያዎች ተነግሮት ቀሪውን የህይወት ዘመኑን በብረት ተደግፎ እንዲኖር መዳረጉን የክለቡ ኃላፊዎችና የደጋፊዎች ማህበር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እና የደጋፊዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ታምራትን ጨምሮ ሌሎች የክለቡ ኃላፊዎችና የደጋፊዎች ማህበር አመራሮች በጋራ ትናንት በደሳለኝ ሆቴል በወቅታዊ የደጋፊዎች ጉዳት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተው ነበር። በጋዜጣዊ መግለጫው “ጎንደር ላይ ችግር ይደርስብናል ብለን ለአንድ ቀንም አስበነው አናውቅም ነበር” ሲሉ መናገር የጀመሩት የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ፤ ምክንያታቸውን ሲናገሩም “በመጀመሪያ ደረጃ ጎንደር ከተማ ታሪካዊና ጥንታዊት ከተማ ስትሆን ህዝቧም እንደማንኛውም የአገራችን ህዝብ እንግዳ ተቀባይና ሰው አክባሩ መሆኑ፣ ቢራ ፋብሪካው የክለባችን ስፖንሰር ሆኖ መስራቱ የሚታወስ ሲሆን የራሳቸውን ክለብ ካቋቋሙ በኋላም ቢሆን በተለያየ መንገድ ደጋፊዎቻችንን በፋይናንስ ሲደግፍልን መቆየቱ፣ ክለቡም ቢሆን በመሰረታዊ የእግር ኳስ መርህ ላይ ከእኛ ጋር ተግባብቶ በመስራት የሚታወቅ መሆኑ እና ከምንም በላይ ደግሞ ፋብሪካው ከአርሴናል እግር ኳስ ክለብ ጋር በፈጠረው ግንኙነት የኢትዮጵያን አሰልጣኞች ስልጠና እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ስናስብ ጎንደር ላይ ችግር ይደርስብናል ብለን እንዳናስብ አድርጎናል” ሲሉ ነበር የተናገሩት።

መቶአለቃ ፈቃደ አያይዘውም ከዚህ በፊት ሀዋሳ ላይም ተመሳሳይ ችግር በክለባቸው ደጋፊዎች ላይ እንዳጋጠመ ተናግረዋል። በቅርቡ ኢትዮጵያ ቡና ከአርባምንጭ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ጋር አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ባደረጉት ጨዋታ የስታዲየም በሮች ጨዋታው ሊጀመር ከ30 ደቂቃ ያነሱ ጊዜያት ሲቀሩት መከፈቱ በወቅቱ ቡናን በገቢ ከመጉዳቱም በላይ ደጋፊዎችን ለብጥብጥ ሊዳርግ የሚችል ጥፋት እንደሆነ ጠቁመዋል። “በሮቹ በመዘጋታቸው ምክንያት ወደ ስታዲየም ለመግባት በነበረው ትንቅንቅ ምክንያት የሰው ህይወት ሊያልፍ የሚችል እንደነበረ በመገንዘባችን ሳይከፍሉ እንዲገቡ ወሰንን። በወቅቱ የስታዲየም በሮች ለምን እስከዚያ ሰዓት ድረስ እንዳልተከፈቱ ባደረግነው ማጣራት ከፌዴሬሽኑ የደረሰን መልስ ቲኬት ቆራጮች ስላልገቡ የሚል ነው” ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው ለዚህም ፌዴሬሽኑ የራሱን የቤት ስራ ቀድሞ አለመስራቱ ለዚህ ሁሉ ችግር እንደዳረጋቸው እምነታቸውን ገልጸዋል። በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ስለተፈጠረው ችግር በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በተደረገ ማጣራት የተገኘው መልስ ግን በወቅቱ ቲኬት ቆራጮች ቢገኙም የጸጥታ ሀይሉ ስላልተሟላ እንደሆነ የሚል ነው። መቶ አለቃ ፈቃደ “ለጸጥታ ሀይሉም ሆነ ለቲኬት ቆራጮች በጊዜው አለመገኘት የፌዴሬሽኑ ችግር ነው” ብለዋል።

ከዚህ በተረፈም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለያዩ ጊዜያት ለሚፈጠሩ ችግሮች ወዲያውኑ አስተማሪ ቅጣት አለመወሰኑን የገለጹት የቡናው ፕሬዚዳንት በዚህም ምክንያት ችግሮች እንዲቀጥሉ ማድረጉን ተናግረዋል።

ከመቶአለቃ መግለጫ በኋላ ጎንደር ላይ የነበረውን ሂደት የተለያዩ የክለቡ ኃላፊዎች በዝርዝር ተናግረዋል። በመጀመሪያ መናገር የጀመሩት የቡድኑ መሪ አቶ ሰይፈ ናቸው።  አቶ ሰይፈ ክለባቸው ጎንደር ሲገባ ከተጋጣሚያቸው መልካም አቀባባል እንደተደረገላቸው ገልጸው በቀጣዩ ቀን ግን ልምምድ ለመስራት ሜዳ ሲጠይቁ “ከሰዓት በኋላ ብሔራዊ ሊግ ውድድር ስላለ ሜዳ ልንሰጣችሁ እንቸገራለን ስለዚህ ሌላ ሜዳ ፈልጋችሁ ተለማመዱ” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። ሆኖም በተደጋጋሚ ጥያቄ ለአንድ ሰዓት ሜዳ እንደተፈቀደላቸው ገልጸዋል።

የቡድን መሪው አያይዘውም “በቅድመ ጨዋታ ግንኙነታችን ደግሞ የምንጫወትበትን ማሊያ እንድንለውጥ የሚያስገድድ ሀሳብ ይዘው መቅረባቸው ነው” ያሉት አቶ ሰይፈ ሀሳባቸውን ሲያብራሩ “ዳሽን ቢራ በሜዳው ሲጫወት ለመልበስ ያስመዘገበው ማሊያ ሙሉ አረንጓዴ ቢሆንም ከእኛ ጋር ለመጫወት ግን ሙሉ ቀይ ማሊያ ይዘው ቀረቡ።  የእኛ ማሊያ ደግሞ ከላይ ቡኒ ሆኖ ከታች ቢጫ ስለሆነ ማሊያ ቀይሩ ተብሎ ከዳሽን ቢራ ተነገረን። እኛ ግን አንድ ቡድን በሜዳው ለመጫወት የሚጠቀምበትን ማሊያ በመጀመሪያ ባስመዘገበው እንዲጫወት ይገደዳል የሚለውን ህግ ጠቀስን። ኮሚሽነሩ አቶ ተስፋዬ ኦሜጋ ህጉን ገልጠው ከተመለከቱ በኋላ የዳሽን ሀሳብ ውድቅ እንዲሆን ወሰኑ” ብለዋል።

 የሁለቱ ቡድኖች ውዝግብ በዚህ ብቻ እንዳላበቃ የገለጹት አቶ ሰይፈ “ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ሜዳ የሚያደርሰንን መኪና ማቅረብ ስለሚገባቸው እንዲያቀርቡልን ስንጠይቃቸው ያለን አንድ መኪና ብቻ ስለሆነ የምናደርገው በመጀመሪያ የራሳችንን ቡድን ይዘን መሄድ ነው። እናንተን የምንወስደው ከዚያ በኋላ ነው ብለው ነገሩን። እኛም ግድ የለም መኪና ከሌላችሁ እኛ ተከራይተን እንሄዳለን ብለን ነገርናቸው። ቆይተው ግን መኪናውን ፈቀዱልን” ሲሉ አብራርተዋል። አቶ ሰይፈ ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ እስከ 65ኛው ደቂቃ በሰላም መካሄዱን ገልጸው በ65ኛው ደቂቃ ቡና የአቻነቷን ጎል ካስቆጠረ በኋላ ግን ነገሮች እንደበላሹ ተናግረዋል።

ሌላው ሪፖርት ያቀረቡት የቡና ሰው ደግሞ የክለቡ ሀኪም አቶ ይሳቅ ናቸው። አቶ ይሳቅም ከክለቡ ቡድን መሪ ጋር ተመሳሰሳይ አስተያየት ያቀረቡ ሲሆን በተለይ የእለቱ ዳኛ የደረሰበትን ጉዳት የህክምና እርዳታ እንደሰጡ ገልጸው ጨዋታውን እንዳይቀጥልም ሙያዊ ምክር ነግረውት እንደነበረ ተናግረዋል።  ሆኖም ዳኛው “ግድ የለም ደሙን ካቆምክልኝ ጨዋታውን እጨርሳለሁ” እንዳላቸው ተናግረዋል።  በዚህም ምክንያት ዳኛው የተፈነከተውን ጆሯቸውን በሻሽ አስረው ጨዋታውን እንደመሩ ገልጸው ዳኛውም ከዚያ ክስተት በኋላ በቡና ላይ ዋጋ ያስከፈሉ ውሳኔዎችን እንደወሰኑ ተናግረዋል። ለአብነት ያህልም አምበሉ መስዑድ መሃመድ ተጠልፎ በመውደቁ የሰጡትን ፍጹም ቅጣት ምት እንደገና መሻራቸውንና ለመስዑድም ቢጫ ካርድ እንደሰጡት አቶ ይሳቅም ሆኑ አቶ ሰይፈ ተናግረዋል። በነገራችን ላይ በዚህ ወቅት የክለቡ የቡድን መሪ ግንባራቸውን ሃኪሙ አቶ ይሳቅ ደግሞ ጀርባቸውን በድንጋይ መመታታቸውን ክለቡ ለጋዜጠኞች ባሳየው ፊልም ተመልክተናል።

አቶ ገዛኸኝ ከተሰናበቱ በኋላ የክለቡን ስራ አስኪያጅነት በጊዜያዊነት እየመሩ ያሉት አቶ ተክለወይን በበኩላቸው በክለባቸው ደጋፊዎች ላይ የደረሱትን አደጋዎች መጠን እና ክለቡም በፋይናንስ የደረሰበትን ጉዳት ሪፖርት አቅርበዋል።  37 ወንድ እና 7 ሴት ደጋፊዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የገለጹት አቶ ተክለወይን የተጎዱትን ደጋፊዎችም ክለቡ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ጎንደር፣ ባህር ዳር እና አዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች እንዳሳከመ ገልጸዋል። በተለይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ደጋፊዎች ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ እና ከጎንደር ባህር ዳር ከዚያም አዲስ አበባ የሚያደርስ የአውሮፕላን ቲኬት ክለቡ እንደገዛ ገልጸው ለህክምናም እስከ ትናንት አርብ ድረስ ከ50 ሺህ ብር በላይ ወጭ ማውጣቱን ገልጸዋል። ለትራንስፖርት ደግሞ ወደ 18 ሺህ ብር ወጭ እንዳደረገ ገልጸዋል።

የደጋፊዎች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ታምራት ደግሞ “ጨዋታው ከመካሄዱ ሁለት እና ሶስት ቀናት ቀደም ብለን ከዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ማህበር ጋር በስልክ ግንኙነት በማድረግ ነገሮች በታሰበላቸው መልኩ እንዲካሄዱ ጥረት አድርገናል። ምክንያቱም ደጋፊዎቻችን ወደ ቦታው ሲሄዱ በቦታው ሊደረግላቸው ስለሚገባው የጸጥታ ጉዳይ እና ስለሚያስፈልጋቸው ማንኛውም ሁኔታ እንድንወያይ ነበር ጥረት ያደረግነው። ከእነሱ የተሰጠን መልስም ምንም አይነት ስጋት እንዳይገባን ነበር የተገለጸልን። እኛም ከዚህ ያለውን ነገር አስተካክለን ከጨረስን በኋላ ደጋፊዎቻቸንን በመኪና፣ በአውሮፕላን እና በሞተር ሳይክል ደጋፊዎቻችን ይዘን ሄድን። ጎንደር ስንገባም ከከተማው ነዋሪ ደማቅ አቀባበል ነበር የተደረገልን” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ሰለሞን አክለውም “ጎንደር ከገባን በኋላም የደጋፊ ማህበር አመራሮች ለጨዋታው የተመደቡትን ዋና ኢንስፔክተር ሂደን ስለ ጸጥታው ጉዳይ አነጋገርናቸው። ደጋፊዎቻችንም አንድ ቦታ ሆነው ክለባቸውን እንዲደግፉ እንፈልጋለንና አትቀላቅሏቸው ስንላቸው ስለፈቀዱልን ሁሉም ደጋፊዎቻችን አንድ አይነት ቲኬት ገዝተው እንዲገቡ ስለነገርናቸው አንድ ቦታ ላይ ተቀምጠው ጨዋታውን ተከታትለዋል። ስለጸጥታው ጉዳይ በቂ ሀይል መኖሩን ስንጠይቃቸውም ስጋት አይግባችሁ በቂ ሀይል አለ ብለው ነገሩን። ጨዋታው ከተጀመረ በኋላም ቢሆን ደጋፊዎቻችን በጨዋነት ድጋፋቸውን ቀጥለው ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።  ሆኖም ነገሮች የተበላሹት ከ65ኛው ደቂቃ ጀምሮ መሆኑን ገልጸዋል።

በ65ኛው ደቂቃ ቡና የአቻነት ጎል ካስቆጠረ በኋላ ጎሏ ከጨዋታ ውጭ ናት በሚል ሰበብ የዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ረብሻ መፍጠራቸውን የገለጹት አቶ ሰለሞን “በወቅቱ ደጋፊዎቹ ዳኛው ላይ ጥቃት ሲያደርሱ ኢንስፔክተሩን ሂደን አነጋገርናቸው።  ከዚህ በኋላ ነገሮች እየከፉ ስለሚሄዱ የጸጥታ ሀይላችሁን አጠናክሩት ብለን ጠየቅናቸው። እነሱም በእኛ በኩል ጸጥታ ሀይሉን እናጠናክራለን እናንተም ደጋፊዎቻችሁን ሂዱና ስትደግፉ የምታሰሙትን መዝሙር ማለትም “ዳሽን ይወርዳል ፋሲል ይመጣል የሚለውን” እንዲያስተካክሉ ንገሯቸው ብለው ነገሩን። እኛም እንደተባለው አደረግን። እነሱ ግን እንደገቡልን ቃል ማድረግ አልቻሉም” ብለዋል። የዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች በቡና ደጋፊዎች ላይ ድንጋይ እየወረወሩ ሲመቷቸው የጸጥታ ሀይሉ የማረጋጋት ስራ እንዳልሰራ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል። ጉዳዩ በቀላሉ ሊበርድ ባለመቻሉም ጥይት መተኮሱን አስታውሰው ከምሽቱ 1፡00 ሲሆን የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ከሜዳ መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ይቀጥላል!!

      


ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!