Recently Posted News
  ቅዱስ ጊዮርጊስ ለ13ኛ ጊዜ ሻምፒዮን ሆነ
ሰኔ 15, 2008

በይርጋ አበበ

የፈረሰኞቹ ድል እና ከድሉ ጀርባ ያሉ እውነታዎች

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደ አዲስ በ1990 ዓ.ም መካሄድ ሲጀምር ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የአንደኛ ዲቪዚዮን ተወዳዳሪ ነበር። በወቅቱ አስራት ሀይሌ እያሰለጠነው የአንደኛ ዲቪዚዮን የዋንጫ ባለቤት ሲሆን ስንታየሁ ጌታቸው ወይም ቆጬ ኮከብ ጎል አግቢ ሲሆን ፋሲል ተካልኝ ደግሞ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጦ ነበር። ቡድኑን ለስኬት ተጫዋቾቹን ደግመሞ ለድል ያበቃው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ደግሞ የውድድሩ ኮከብ አሰልጣኝነት ክብርን ተቀዳጅቷል። ይህን ሁሉ ስኬት ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ላይ ሲጎናጸፍ በፕሪሚየር ሊጉ ደግሞ የቀድሞው መብራት ኃይል የአሁኑ ኤሌክትሪክ የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ባለድል የሆነበት ዓመት ነበር።

ከላይ የተጠቀሰው ታሪክ የተፈጸመው ከዛሬ 18 ዓመት በፊት ነው። ዛሬ ነገሮች ሁሉ ተቀይረዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ የአንደኛ ዲቪዚዮን ተወዳዳሪ ሳይሆን የፕሪሚየር ሊጉ አንደኛ ክለብ ነው። ኤሌክትሪክ ደግሞ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ህም ሆኖበት ወደ ታችኛው ሊግ ላለመውረድ እጁ የገባውን ሰርዶ የሙጥኝ ብሎ መያዝ የዓመት ከዓመት ይትባህሉ አድርጎታል።

ፕሪሚየር ሊጉ መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ 19ኛ ጊዜው ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በ18ቱ ተሳትፎ በአምስቱ ብቻ ዋንጫውን ሲያጣ 13 ጊዜ 13 ክለቦችን አስከትሎ የውድድር ዓመቱን አጠናቋል። ዘንድሮ እየተካሄደ ባለውና በውዝግብ ታጅቦ ለመጠናቀቅ በተቃረበው ፕሪሚየር ሊግ ከታዩ አብይ ክስተቶች መካከል ከእግር ኳሱ አዝናኝነት ይልቅ በእግር ኳሱ ሜዳ የሚፈጠሩ ግጭቶች ሆነዋል። ሆኖም በግጭቶች እና በፌዴራል ፖሊስ ታጅቦ እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ልማዱ ዘንድሮም ገና ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች እያሉት ተከታዮቹን ሁሉ አስከንድቶ ዋንጫውን ማንሳቱን ያረጋገጠው ባሳለፍነው ሰኞ ምሽት ነበር። ለመሆኑ ዘንድሮ ፈረሰኞቹ የውድድር ዓመቱን እንዴት አሳለፉት እነማንስ የቡድኑ ወሳኝ ሰዎች ናቸው ቀጣይ የክለቡ ጉዞስ ምን ይመስላል የሚሉትን ወደፊት የምንመለስባቸው ቢሆንም ለዛሬው ዝግጅታችን ግን ከዚህ በታች ያለውን መጠነኛ ዳሰሳ አቅርበነዋል።

13+13+13 = 2008 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ

ሰኔ 13 ቀን ከምሽቱ 11 ፡30 ሲሆን እንደለመደው የአዲስ አበባ ስታዲየም በሰማዩ እንባ ምክንያት ሆድ ብሶት ማልቀስ ጀምሯል። ሆኖም ወደ ታችኛው ሊግ ለመውረድ በቋፍ ላይ ያለው ዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለብ ለህልውናው ፈረሰኞቹ ደግሞ ለክብር ሲሉ ሆድ በባሰው የአዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የተፋለሙበት እለት ነው ሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2008 ዓ.ም። ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙለት እንዲሉ በእለተ ሰኞ አብራጃው ላይ የተገናኙት ሁለቱ ክለቦች በሜዳው አስቸጋሪነት እና በክለቦቻቸው የአጨዋወት ባህል ምክንያት ለተመልካች አሰልች የሆነ ጨዋታቸውን እያካሄዱ ቆይተው 20ኛው ደቂቃ ሲደርስ ሳላዲን ሰይድ ፈረሰኞቹን የዋንጫው ባለቤት ልታደርግ እንደምትችል ምልክት የሰጠችዋን ጎል በዳሽን ቢራ መረብ ላይ አሳረፈ። እስከ እረፍትም ሆነ ከእረፍት መልስ ሜዳ ላይ ጥሩ መጫወት ያልቻሉት ሁለቱ ክለቦች በጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ ሲነፋ የውጤት ማሳያ ሰሌዳው አዳነ ግርማ እና ሳላዲን ሰይድ ያስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ኤዶም ያስቆጠራትን የዳሽን ቢራ ብቸኛ ጎል አስንቀው ፈረሰኞቹ ለ13ኛ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫ ባለቤት መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ አደረጉ። ሰኔ 13 የጊዮርጊሱ አምበል ደጉ ደበበ ከፈረሰኞቹ ጋር የቆየበት 13ኛ ዓመት እና ፈረሰኞቹ የሊጉን ዋንጫ ለ13ኛ ጊዜ ያነሱበት አጋጣሚ። 13+13+13 = 2008 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ።

የፈረሰኞቹ የድል ሚስጢር

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለመጻፍ ሰፊ ጥናት እና ሪሰርቾችን መስራት አስፈላጊ ቢሆንም ለዛሬው ግን ፈረሰኞቹ በዚህ ዓመት ስኬታማ የውድድር ጊዜ እንዲያሳልፉ ምክንያት ከሆኗቸው ነጥቦች መካከል የተወሰኑትን ብቻ እናነሳለን። በክለቡ ውስጥ በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾች ከክለቡ ጋር ለረጅም ዓመታት የሚቆዩበት ባህል አለ። ይህ በመሆኑ ምክንያት ደግሞ ተጫዋቾቹ እንዲግባቡ የሚያደርጋቸው ከመሆኑም በላይ የቤታቸው ያህል ክለባቸው እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል። ይህ ደግሞ ለአንድ ቡድን ስኬት ወሳኝነት አለው።

እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ የሊጉ ኮከብ ግብ ጠባቂ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ሮበርት ኦዶንካራ ምንም እንኳን በዚህ ዓመት ብዙም የተፈተነበት አጋጣሚ ባይኖርም ዘንድሮም ከእነ ሙሉ ብቃቱ የውድድር ዓመቱን ጨርሷል። ለ13 ዓመታት የአንድን ክለብ ማሊያ ብቻ ገላው የለበሰው ደጉ ደበበ ያለምንም ጥርጥር ለፈረሰኞቹ የኋላ መስመር ጥንካሬ ተጠቃሽ ነው። አመለ ሸጋውና የተረጋጋው አምበል የኋላ መሰመሩን ከማደራጀትም በላይ በወሳኝ ሰዓት ለክለቡ ያስቆጠራቸው ጎሎች ክለቡ ከሰበሰበው 51 ነጥብ ላይ የራሱን ድርሻ ማሳረፍ ችሏል። ከደጉ ባልተናነሰ በዚህ ዓመት ፈረሰኞቹ የተቀላቀለው ሌላው የደቡብ ክልል ተወላጅ አስቻለው ታመነ ክለቡን በተቀላቀለበት ዓመት ስኬታማ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ መሆኑ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ጥንካሬ ተጠቃሽ እንዲሆን አስችሎታል።

በሀይሉ አሰፋ አሁንም ከእነ ሀይሉ ነው እየተጫወተ ያለው። በቅርቡ የልጅ አባት የሆናል ሲባል በድንገት ልጁን በሞት ምክንያት ያጣው ጥበበኛው አማካይ የልጁ ሞት ሳይረብሸው ሀዘኑን በውስጡ ይዞ ያሳየው ብቃት ከደጋፊም ከተመልካችም ሆነ ከስፖርት ቤተሰቡ አድናቆትን ያሰጠው ሆኗል። አዳነ ግርማ እና ሳላዲን ሰይድ የፈጠሩት ጥምረት ድንቅ ነው። ይህ ድንጠሯቸውን ጎሎች ብዛት ወደ ስምንት ማሳደግ አስችሏቸዋል። ይህ ደግሞ ፈረሰኞቹ አስፈሪ የአጥቂ መስመር እንዲይዙ አድርጓቸዋል ያስብላል።

ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ አማካይ ተከላካዩ ታስፋዬ አለባቸው ቆቦ እና አሰልጣኝ ስታፉ ሳይዘነጋ ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ፈረሰኞቹ እነደ ቡድን በዚህ ዓመት ጠንካራ ሆነው ባይቀርቡም ተጋጣሚዎቻቸው በሙሉ ደካሞች መሆናቸውንም ማንሳቱ ተገቢ ይሆናል።

ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
sintayehu belay [606 days ago.]
 ለምንድነው የወልድያንና የአውስኮድ ጭዋታን ውሳኔ የማይሰጠው ስንት ስንት ውሳኔዎችን እያሳለፋቹ ይቺ ቀላሉአ ነገር ይሄን ያክል ጊዜ ሊፈጅ ቻለ፡ ህዝቡም ሰልፍ ሊወጣ ትንሽ ቀርቶታል ፡ ፍትህ ለወልድያ ስፖርት ክለብ

sintayehu belay [606 days ago.]
 ለምንድነው የወልድያንና የአውስኮድ ጭዋታን ውሳኔ የማይሰጠው ስንት ስንት ውሳኔዎችን እያሳለፋቹ ይቺ ቀላሉአ ነገር ይሄን ያክል ጊዜ ሊፈጅ ቻለ፡ ህዝቡም ሰልፍ ሊወጣ ትንሽ ቀርቶታል ፡ ፍትህ ለወልድያ ስፖርት ክለብ

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!