Recently Posted News
  25ኛው የፕሪሚየር ሊግ መርሃ ብር ውጤቶችና አብይ ክስተቶች
ሰኔ 18, 2008

በይርጋ አበበ

ማሸነፍ የተሳነው የታችኛው ክፍል

ሀድያ ሆሳዕና ባለፈው የውድድር ዓመት የብሔራዊ ሊጉ የብር ሜዳሊያ ባለቤት መሆኑን ተከትሎ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተቀላቀለ አምስተኛው የደቡብ ክልል ተወካይ ክለብ ነበር። ነገር ግን በቀጣዩ የውድድር ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ የማንመለከተው ክለብ መሆኑን ያረጋገጠው ገና በውድድር ዓመቱ መጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ነበር። በ25 ሳምንታት የውድድር ጊዜው ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ማሸነፍ የቻለው ሀድያ ሆሳዕና ከሊጉ የተሰናበተ የመጀመሪያው ክለብ ሲሆን እሱን ተከትሎ ወደ ቁልቁለቱ የሚያመራውን ክለብ ለመለየት የሚደረገው ፉክክር ግን አጓጊ ሆኗል።

በ25ኛው ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ትናንትና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተካሄደ ሲሆን በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኙት ዳሽን ቢራ እና ኤሌክትሪክ ወደ ደቡብ ክልል ተጉዘው አንድ አንድ ነጥብ ብቻ ይዘው ሲመለሱ ሌላው ወራጅ ክለብ ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ በሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ ሁለት ለአንድ ተሸንፏል። ለሀድያ ብቸኛዋን ጎል ዱላ ሙላቱ ሲያስቆጥር ለቡና ደግሞo ያቡን ዊሊያም እና ሳዲቅ ሴቾ አስቆጥረዋል። ኤሌክትሪክ ከወላይታ ድቻ ጋር ባዶ ለባዶ ሲለያይ ዳሽን ቢራ ከሀዋሳ ከነማ ጋር ሁለት ለሁለት በተለያዩበት ጨዋታ ደግሞ ይተሻ ግዛው እና ኤዶም ሆሮውስኪ ለዳሽን ቢራ ሲያስቆጥሩ ፍርዳወቅ ሲሳይና ዮሃንስ ለሀዋሳ ከነማ አስቀቆጥረዋል።

ከመውረድ ስጋት ነጻ የሆነው አርባ ምንጭ ከነማ በበኩሉ ወደ ይርጋዓለም ተጉዞ ከሲዳማ ቡና ጋር ያደረገውን ጨዋታ በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ ችሏል። በዚህ ጨዋታ በተለይ የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ ፍቅሩ ወልዴ ያሳየው ብቃት ከፍተኛ እንደነበረ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ሊጉን በዚህ ዓመት የተቀላቀለው የምስራቅ ኢትዮጵያው ተወካይ ድሬዳዋ ከነማ በበኩሉ በመጀመሪያው ዙር ጥሩ ተፎካካሪ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር የወረደ አቋም በማሳየት ላይ ይገኛል። ትናንትናም በሜዳው ከደደቢት ጋር ተጫውቶ ሁለት ለአንድ ተሸንፏል። ለደደቢት ሁለቱን ጎሎች ዳዊት ፈቃዱ እና ሳሙኤል ሳኑሜ አስቆጥረዋል። ሌላው የታችኛው ህብረተሰብ የሆነው መከላከያ በበኩሉ በሜዳው ከሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ለ86 ደቂቃዎች ያህል በመሀመድ ናስር ጎል ሲመራ ቢቆይም በ94ኛው ደቂቃ ዳዋ ሁጤሳ ሻምፒዮኖቹን ከሽንፈት የታደገች ግሩም ጎል አስቆጥሯል። በዚህም መሰረት ከ10ኛ እስከ 14ኛ ደረጃ ያሉት ስድስት ክለቦች አንዳቸውም ማሸነፍ ያልቻሉበት ሳምንት ሆኗል ማለት ነው።

የተረሳው ኮከብ - ዳዋ ሁጤሳ

ከኦሮሚያ ክልል ኤሊባቡር ከተማ የተወለደው ረጅሙ ወጣት ዳዋ ሁጤሳ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ቤተሰብ ጋር በፋት በተዋወቅ የጀመረው በአሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ አማካኝነት ለብሔራዊ ቡድን ከተመረጠ በኋላ ነበር። በወቅቱ ለድሬዳዋው “ናሽናል ሴሚንቶ እግር ኳስ ክለብ” ይጫወት የነበረው ዳዋ ሁጤሳ ለብሔራዊ ቡድን መመረጡን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የግሉ ሲያደርገው አፍታ አልቆየም ነበር። ሆኖም ግን በፈረሰኞቹ ቤት ብዙም ሳይቆይ ከቋሚ አሰላለፍ ውጭ በመሆን ቦታውን አንጋፋዎቹ እነ አዳነ ግርማ እና ሳላሃዲን ሰይድ እነዲረከቡት በመደረጉ ወደ ተጠባባቂ ወንበር ወረደ። በዚያውም የልጁ ችሎታ አብሮ ወረደ።

በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት የተረሳውን ኮከብ ሀዋሳ ከነማ በጥር ወር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት መከፈቱን ተከትሎ የግሉ ሊያደርገው ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም በፈረሰኞቹ እምቢተኝነት ልጁ በቅዱስ ጊዮርጊስ ካምፕ እንዲቆይ ሆኗል። ትናንትና ተቀይሮ ገብቶም ፈረሰኞቹን ከሽንፈት የታደገች ግሩም ኳስ ማስቆጠር ችሏል። የተዘነጋው ኮከብ ተቀይሮ በመግባት ያስቆጠራት ጎልም ፈረሰኞቹ የድል ባለቤት በሆኑ ማግስት የሽንፈት ጽዋን እንዳይጎነጩ የታደገች ጎል ነበረች።

የ25ኛው ሳምንት አጠቃላይ ገጽታ

ሁለት ጨዋታዎች በዝናብ ምክንያት ሆዱ በራደበት አዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂደው አምስቱ ከአዲስ አበባ ውጭ የተካሄዱት የ25ኛው ሳመንት መርሃ ግብር ከሁለቱ ጨዋታዎች በስተቀር አምስቱ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁበት ሳምንት ነው። የት ይደርሳል ተብሎ ሰፊ ግምት ተሰጥቶት የውድድር ዓመቱን የጀመረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከአዳማ ከነማ ጋረ ያደረገውን ጨዋታ ባዶ ለባዶ ተለያይቷል። ምንም አይነት የእግር ኳስ ጨዋታ ውበት ባለታየበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በሁለቱም በኩል ግብ ጠባቂዎቹ ኳስ ናፍቋቸው ነበር ጨዋታውን ያጠናቀቁት። በሀሉቱም ወገን አጥቂ ይዘው የገቡ ያልመሰሉበትን ጨዋታ ንግድ ባንኮች በፍቅረ የሱስ ተክለብርሃን አማካኝነት አንድ ጥሩ የማግባት ሙከራ ሲያደርጉ አዳማ ከነማዎች በበኩላቸው በታፈሰ ተስፋዬ አማካኝነት አንድ ጊዜ የባንክን በር ማንኳኳት ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ለሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ውበት አልባ መሆን የስታዲየሙ ጭቃ ምክንያት ነው።

ሌላው አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የተካሄደው የፈረሰኞቹ እና የጦሩ ጨዋታም አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን በዚያ ጨዋታ መከላከያዎች የነበራቸው ብቃት ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል። በመሀል ሜዳ የኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል ደጋግሞ በመቅረብ መከላከያዎች የተሻሉ ሲሆኑ ብዙ ፋኦሎችን በመስራት ደግሞ ፈረሰኞቹ አቻ አልነበራቸውም። ያም ሆኖ ግን እንደ ምንያህል ተሾመ አይነት የኳስ ሊቅ በፈረሰኞቹ በኩል አይነ ግቡ እንስቃሴ ያደረገ ሲሆን አንጋፋዎቹ አጥቂዎች ሳላዲን ሰይድ እና አዳነ ግርማ ደግሞ ጭራሽ የጨዋታው አካል ሳይመስሉ የመጠናቀቂያው ፊሽካ ተነፍቷል።

በመከላከያ በኩል ሳሙኤል ታዬ እና ሚካኤል ደስታ በአማካይ በኩል እንዲሁም መሀመድ ናስር በአጥቂ በኩል እና አዲሱ ተስፋዬ በተከላካይ በኩል መልካም የነበሩ ሲሆን ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው በእለቱ ያሳየው ብቃት እጅግ የተዋጣለት ነበር። የቅዱሰ ጊዮርጊሱ አምበል ደጉ ደበበ ቡድኑን በመምራትም ሆነ ኳስን በማደራጀት ከቡድኑ አማካዮች ተሽሎ የታዬ ሲሆን እድሜው ቢገፋም ችሎታው ግን አሁንም አብሮት መሆኑን ያሳየበት እለትም ነበር ማለት ይቻላል።

በሌሎች ጨዋታዎች ደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና ወደ ምስራቅ እና ደቡብ አቅንተው ማሸነፍ ችለዋል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሁለቱም ክለቦች ትናንት ማሸነፍ የቻሉት ባለፈው በያዝነው ዓመት ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀሉትን ድሬዳዋ ከነማን እና ሀድያ ሆሳዕናን ሲሆን ሌላው አስገራሚ የሆነው ደግሞ ሁለቱም ክለቦች ማሸነፍ የቻሉባቸውን ጎሎች ያስቆጠሯቸው ተጫዋቾች ናቸው። ለቡና ሳዲቅ ለደደቢት ዳዊት ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ያቡን ዊሊያም እና ሳሙኤል ሳኑሜ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ያልሆኑ ተጫዋቾች ናቸው።

ሀዋሳ በሜዳው ነጥብ መጣሉን ሲቀጥል ጎረቤቱ ሲዳማም ይርጋለም ላይ ጎል ማግባት እንደተሳነው ነው። ወላይታ ድቻ በበኩሉ በዓመቱ ካካሄዳቸው ጨዋታዎች መካከል አብዛኛውን ጨዋታ ያጠናቀቀው በአቻ ውጤት ሲሆን ትናንትም ከኤሌክትሪክ ጋር በአቻ ውጤት ጨዋታውን ጨርሷል።

 


ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!