Recently Posted News
  የቀጣዩ ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ፊቶች እነማን ይሆናሉ? አዲስ አበባ ከነማ እንደ ማሳያ
ሰኔ 20, 2008

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከቀጣዩ የውድድር ዓመ ጀምሮ በፕሪሚየር ሊጉ የሚወዳደሩ ክለቦችን ቁጥር ወደ 16 እንደሚያሳድግ አስታውቋል። በዚህም ምክንያት በሱፐር ሊጉ የሚወዳደሩ 32 ክለቦችን በሁለት ምድብ ከፍሎ እያወዳደረ ሲሆን ከየምድባቸው አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን የዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦችን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንዲያድጉ ያደርጋል። በሱፐር ሊጉ ምድብ አንድን የአማራ ክልል ክለቦች ፋሲል ከነማ በ44 ነጥብ እና 20 ንጹህ ጎል እና ወልድያ ከነማ በ41 ነጥብና ዘጠኝ ንዑህ ጎሎች አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ይመራሉ። የአዲስ አበባ ው መድን ኢትዮጵያ በ37 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ይከተላቸዋል። ምድብ ሁለትን ደግሞ የኦሮሚያው ጂማ አባቡና በ48 ነጥብ ሲመራ የአዲስ አበባው አዲስ አበባ ከነማ በ44 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በዛሬው ዝግጅታችን የአዲስ አበባ ከነማ እግር ኳስ ክለብን የተመለከተ መጠነኛ ዘገባ ይዘን ቀርበናል።

የቡድኑ የማደግ ተስፋ

አዲስ አበባ ከነማ እግር ኳስ ክለብ በውጤታማው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ እየተመራ የዚህ ዓመት ውድድሩን ጀምሯል። ቡድኑ በምድቡ መሪ ጅማ አባቡና ሁለት ጊዜ እና በደቡብ ፖሊስ ደግሞ አራት ለባዶ በሆነ ሰፊ የጎል ልዩነት ከመሸነፉ ውጭ በቀሪዎቹ ጨዋታዎች አስደሳች ውጤት መቀዳጀት ችሏል። በመጀመሪያው ዙር መርሃ ግብር አስር ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጭ አድርጎ የነበረው የስዩም ከበደ ቡድን በሁለተኛው ዙር ደግሞ አስር ጨዋታዎችን በሜዳው የሚያካሂድ መሆኑ እና አሁንም ገና ተስተካካይ ሁለት ጨዋታዎች አየቀሩት ከተከታዮቹ በሶስት እና ስድስት ነጥቦች ልቆ መገኘቱ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የማደግ ተስፋው የሰፋ መሆኑን አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም ጋር በስልክ ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሯል።

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ አክሎም “ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በሜዳችን የምናደርግ መሆኑ እና ከጠንካራው አላባ ከነማ ጋር ያደረግነውን ጨዋታ በድል መወጣታችን ለእኛ ስኬት ነው። በዚያ ላይ ደግሞ ከመሪው ጋር የነበረንን የነጥብ ልዩነት እንዲጠብ ጅማ አባቡና በጂንካ ከነማ መሸነፉ ረድቶናል” ያለ ሲሆን “ከ20 ዓመት በታች ላለው ብሔራዊ ቡድን ተመርጠው የነበሩት አራት ተጫዋቾቻችን በተደራራቢ ጨዋታ ምክንያት ከእነሙሉ ብቃታቸው ማግኘት ባለመቻላችን እየተጠቀምንባቸው አይደለም። ሆኖም ግን የቡድኔ ስብስብ በተቀራራቢ ችሎታ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የልጆቹ በቋሚነት አለመሰለፍ በቡድኔ ላይ ክፍተት እንዳይኖር ረድቶኛል” ሲል ተናግሯል።

ቡድኑ ዋጋ የከፈለባቸው ጨዋታዎች

አዲስ አበባ ከነማ እግር ኳስ ክለብ በአሰልጣኝ ሰዩም ከበደ መሰለጥን የጀመረው በዚህ ዓመት ሲሆን አሰልጣኙ ቡድኑን ሲረከብ ዘግይቶ በመሆኑ በተጫዋቾች ምርጫ ላይ ችግር እንደነበረበት ተናግሯል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ቀደም ብሎ ተጫዋቾች ወደ ተለያዩ ክለቦች ተዘዋውረው ስለነበረ በቂ ተጫዋቾችን እንዳያገኝ አድርጎት ነበር። ሆኖም ግን አሰልጣኝ ስዩም ሲናገር “ባሉን ልጆች ቡድናችንን አጠናክረን መስራት ስላለብን ተጫዋቾቼን በሚገባ ተቀናጅተው እንዲሰሩ አድርጌያለሁ” ይላል።

ቡድኑ በጠንካራ አመራርና በጀት እንደሚመራ የሚናገረው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ባልተጠበቁ ጨዋታዎች ነጥብ መጣላቸውን ግን አልደበቀም። ለአብነት ያህልም በደቡብ ፖሊስ የደረሰባቸውን የአራት ለባዶ ሽንፈት እና በዋናው ተቀናቃኛቸው ጅማ አባቡና የደረሰባቸውን የደርሶ መልስ ሽንፈት ያስታውሳል። “ከደቡብ ፖሊስ ጋር በነበረብን ጨዋታ እኛ በሰራናቸው ስህተቶች ላይ የእነሱ በእለቱ በጥሩ ብቃት ላይ መሆን ተደምሮ ልንሸነፍ ችለናል” ብሏል። ከጅማ አባቡና ጋር በነበረው ጨዋታም አዲስ አበባ ከነማ የተሻለ የኳስ ቁጥጥርና የጎል ሙከራ የበላይነት ቢኖረውም ከሽንፈት አለመዳኑን አስታውሷል።

የስፖርታዊ ጨዋነት እና የሱፐር ሊጉ ምድብ ሁለት

በኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን አሁን ስታዲየሞች የጦርነት ቀጠና እየመሰሉ መጥተዋል። የፕሪሚየር ሊጉን ትተን በሱፐር ሊጉ የተፈጠሩ አብይ ግጭቶችን ብናነሳ እንኳ የጎንደሩ ፋሲል ከነማ ከትግራዩ መቀሌ ከነማ ጋር አዲግራት ላይ ሲጫወት የደረሰው ግጭት አንዱ ሲሆን ባህር ዳር ላይ ደግሞ አማራ ውኃ ስራዎች ከመቀሌ ከነማ ጋር ባካሄዱት ጨዋታ የመቀሌ ከነማ ተጫዋቾች ዳኛውን ከመደባደብ አልፈው ጨዋታውን አንጫወትም ብለው በልመና እንዲጫወቱ መዳረጉ ሌላው ክስተት ነው። ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር ሲጫወትም ተመሳሳየ ረብሻ ተነስቶ ጨዋታው በፖሊስ እርዳታ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል። ይህ ሁሉ ብጥብጥና ግጭት የበዛበት የሱፐር ሊግ ውድድር በምድብ ሁለት እንዴት እየተካሄደ እነደሆነ ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም የተጠየቀው አሰልጣኝ ስዩም “በሌላኛው ምድብ ደረሰ የምትለውን ግጭትና ብጥብጥ የማየት እድል አላገኘሁም። እንደማንኛውም ሰው ያየሁት በኢንተርኔት አማካኝነት በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ብቻ ነው። ወደ እኛ ምድብ ስመጣ ግን እስካሁን ድረስ ደረሰ የሚባል የከፋ ብጥብጥም ሆነ ግጭት የለም” ሲል ተናግሯል።

የአዲስ አበባ ከነማ አደረጃጀት

የከነማው ክለብ ዓመታዊ በጀቱ 15 ሚሊዮን መሆኑን አዲስ ልሳን ጋዜጣ የዘገበ ሲሆን በሰው ሀይል አደረጃጀት እና ለክለቡ ከአስተዳደሩ እየተደረገለት ያለውን ድጋፍ በተመለከተ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ሲናገር “በጣም ጥሩ ነው። ለውጤታችን ማማር አንዱ ምክንያትም እሱ ነው” ይላል።

ከተመሰረተ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው አዲስ አበባ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደር በተደረገ የመጨረሻ ዙር ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረ ሲሆን በሁለቱም ዓመታት በሩብ ፍጻሜ ተሸንፎ እቅዱ ሳይሳካለት ቀርቷል። ዘንድሮስ?

ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!