Recently Posted News
  ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመቱን የድርብ ድል ባለቤት ሆኖ አጠናቀ
ሰኔ 23, 2008

በይርጋ አበበ

የ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት ምሽት በይፋ ተጠናቋል። ቀድሞ ዋንጫውን ማንሳቱን ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሀዋሳ ከነማን አስተናግዶ ሁለት ለአንድ በማሸነፍ አጨራረሱን አሳምሯል። የሰኔ ሰማይ መቋጠር ያልቻለውን ዝናብ እንዲያስተናግድ የፈረደበት አዲስ አበባ ስታዲየም እንኳንስ ለኳስ መጫወቻ ለምንም አገልግሎት አመቺ ያልሆነ ቢሆንም ፈረሰኞቹ እና ሀዋሳ ከነማ ጨዋታቸውን አካሂደውበታል። ከሁለቱ ክለቦች ግጥሚያ ቀደም ብሎ ደግሞ ደደቢት ቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠውን ሀድያ ሆሳዕናን አስተናግዶ አራት ለአንድ ረምርሞታል። ከአራቱ የደደቢት ጎሎች የከፍተኛ ጎል አግቢነት ደረጃውን ይፎካከሩ የነበሩት ዳዊት ፈቃዱ እና ሳሙኤል ሳኑሜ አንድ አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከነማ ጨዋታ ስንመጣ ሁለቱ ክለቦች ጨዋታቸውን በይፋ ከመጀመራቸው በፊት በ19987 እና 98 ዓ.ም ለፈረሰኞቹ የተጫወተውንና ትናንት በይፋ ከእግር ኳስ የተገለለውን የሀዋሳ ከነማውነ አምበል ሙሉጌታ ምህረትን የሚያወድስ የስጦታ ፕሮግራም አዘጋጅተውለት ነበር። በእግር ኳስ ዘመኑ አንድም ቀይ ካርድ ተመልክቶ የማያውቀውና ለደደቢት ለሀዋሳ ከነማ እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድን ተጫውቶ ያሳለፈው ሙሉጌታ ምህረት ከቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የክብር ስጦታ ተበርክቶለታል።

ከእረፍት በፊት በነበረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የጎል የረባ ሙከራ ባይካሄድበትም በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አዳነ ግርማ በግንባሩ ገጭቶ አግዳሚ ብረት የመለሰበት እና በሀዋሳ በኩል ደግሞ ሀይማኖት ወርቁ ከርቀት አክርሮ የሞከራትና ሮበርት ኦዶንካራ የመለሳት ሙከራ ተጠቃሽ ናቸው። “እንኳን ጥጃ ረግጣኝ ድሮም አልቅስ አልቅስ ይለኛል” እንዲሉ እንኳንስ ስታዲየሙ በጭቃ ዳክሮ ይቅርና ቀድሞውንም ማራኪ ያልነበረው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የትናንት ምሽቱ ግን ከመቼውም ጊዜ በባሰ መልኩ አሰልች ነበር ማለት ይቻላል። ምንም አይነት የእግር ኳስ ውበት ያለታየበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከእረፍት መልስ በመጠኑም ቢሆን መሻሻል የታየበት ሲሆን አዳነ ግርማ እና ራምኬል ሎክ አከታትለው ያስቆጠሯቸው ጎሎች ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችለዋል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ በእጣት የሚቆጠሩ ደቂቃዎች ሲቀሩ ግን የውድድር ዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተሸለመው አስቻለው ታመነ በመድሃኔ ታደሰ ላይ የሰራውን ጥፋት ዳኛው ለሀዋሳ ከነማ ፍጹም ቅጣት ምት ሰጡ።ፍጹም ቅጣት ምቱንም ትናንት በይፋ ከእግር ኳስ የተሰናበተው ሙሉጌታ ምህረት ሀዋሳዎችን ያነቃቃች ጎል አስቆጠረ። ከጎሏ መቆጠር በኋላ በሁለቱም ቡድኖች መካከል መጠነኛ መነቃቃትና ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ ቢችሉም ተጨማሪ ጎል ግን ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። የሙሉጌታ ምህረት ጎልም የውድድር ዓመቱ የመጨረሻ ጎል ሆና ስትቆጠር ለሙሉጌታ ደግሞ የእግር ኳስ ዘመኑ የመጨረሻ ጎሉ ሆናለታለች። ፍጹም ቅጣት ምት እንዲሰጥ ምክንያት የነበረው አስቻለው ታመነ ደግሞ የውድድር ዓመቱን የመጨረሻ ቢጫ ካርድ የተመለከተ ተጫዋች ሲሆን በግሉም ስድስተኛ የውድድር ዓመቱ ቢጫ ካርዱ ሆኗል።

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን በተለይ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም የሰጡ የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ነበሩ። አማካዩ ምንተስኖት አዳነ ደጋፊዎቻችን የውጤታችን ምክንያቶች ናቸው ሲል በውድድር ዓመቱ አጋማሽ ክለቡን ሊለቅ ተቃርቦ የነበረውና በፈረሰኞቹ እምቢተኝነት ወደ ሀዋሳ ከነማ ሊያደርገው የነበረውን ዝውውር የሰረዘው ዳዋ ሁጤሳ በበኩሉ በድሉ ከፍተኛ ደስታ እነደተሰማው ገልጾ “ይህ ትልቅ ክለብ ነው። ከትልቅ ክልብ ደግሞ ዋንጫ ይጠበቃል” ሲል ተናግሯል።

የዓመቱ ምርጦች

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በውድድር ዓመቱ የተለየ ብቃት አሳይተዋል ያላቸውን የእግር ኳስ ሰዎች ሽልማት ሰጥቷል። በዚህ የሽልማት መስፈርት ደግሞ ፈረሰኞቹ አሁንም ተንበሽብሸዋል። የጎሉን መስመር ነቅቶ የጠበቀው ሮበርት ኦዶንካራ ዘንድሮም እንዳለፉት ዓመታት የውድድሩ ኮከብ ጎል ጠባቂ ተብሎ ለአምስተኛ ጊዜ ተሸልሟል። የዋንጫ እና የ15 ሺህ ብር ሽልማትም ከፌዴሬሽኑ ተሰጥቶታል። ከኦዶንካራ ፊት ቆሞ የተጋጣሚ አቂዎችን ወረራ በብቃት ሲመክት የከረመው አስቻለው ታመነ የውድድር ዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የዋንጫ እና የ25 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል። የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ ማርቲን ኖይ ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው የዋንጫ እና የ25 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ከፈረሰኞቹ ካምፕ ውጭ የሆነ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው የአዳማ ከነማው አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ ነው። 15 ጎሎችን ያስቆጠረው አንጋፋው አጥቂ የዋንጫ እና የ25 ሺህ ብር ተሸላሚ ያደረገውን ኮከብ ጎል አግቢነት ክብር መቀዳጀት ችሏል። በእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ አንድም ቀይ ካርድ ያለተመለከተው ሙሉጌታ ምህረት ልዩ ተሸላሚ ሆኖ ተመርጧል።

መከላከያ በውድድር ዓመቱ አመለ ሸጋ ቡድን ተብሎ የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን አዳማ ከነማ የ75 ሺህ ብር እና የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ የ100 ሺህ ብር እና የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዋንጫው በተጨማሪ የ150 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል።

 


ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!