Recently Posted News
  ወደ ስዊድን ተጉዞ ጎቲያ ካፕ ላይ የሚሳተፈው አሴጋ እግር ኳስ አካዳ
ሰኔ 30, 2008


በይርጋ አበበ

አሴጋ እግር ኳስ አካዳሚ በጎቲያ ካፕ ለመሳተፍ ሰሞኑን ወደ ስፍራው ያቀናል። የአካዳሚው መስራችና ባለቤት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና ኢትዮጵያ ቡና አጥቂ የነበረው አሰግድ ተስፋዬ ነው። አሰግድ ተስፋዬ ኢትዮፉትቦል ዶትኮም እንደተናገረው በውድድሩ ለመሳተፍ ሁለት ቡድኖች ከ15 ዓመት እና ከ17 ዓመት በታች ወደ ስዊድን የሚያቀኑ ሲሆን የተጫዋቾቹ ብዛትም 36 እንደሆነ ተናግሯል።

ከ80 አገራት የተውጣጡ 1700 ክለቦች በውድድሩ እንደሚሳተፉ የገለጸው አሰግድ ተስፋዬ “በውድድሩ ከስድስት ዓመት እስከ 18 ዓመት የሚደርሱ ታዳጊዎችና ህጻናት ይወዳደራሉ። በዚህ ውድድር የእኛ ቡድን ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ መወዳደር ችሎ ነበር። በመጀመሪያ የውድድሩ ተሳትፏችን በውጤት በኩል ጥሩ የሚባል ውጤት ማምጣት ባንችልም ጥሩ ትምህርት አግኝተንበት ተመልሰን ነበር። ዘንድሮ ግን ልጆቻችን በሳምንት ሶስት ቀናት ልምምድ ሲሰሩ ስለከረሙ ጥሩ ውጤት ይዘን እንደምንመለስ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል።

የአካዳሚው አሰልጣኝ አቶ አብይ ካሳሁን በበኩሉ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያወዳድረው ከ 17 ዓመት በታች ክለቦች ውድድር ላይ ቡድኑ ሲሳተፍ መቆየቱን ገልጿል። በውድድሩም ብዙዎቹ ክለቦች የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን ካላቸው የጠነከረ ፍላጎት ምክንያት ቡድኖቹ የእድሜ ችግር እንደነበረባቸው አስታውሶ ያም ቢሆን ግን “ለእኛ የጨዋታ ልምድ ለማግኘት ጠቅሞናል። በውድድር ዓመቱ 13 ጨዋታዎችን አካሂደናል። ይህ ደግሞ ለቡድናችን የጨዋታ ልምድ እንዲያገኝ የረዳን ሆኗል” ብሏል። አሰልጣኝ አብይ ካሳሁን እግር ኳስ መጫወትን አቁሞ ወደ አሰልጣኝነቱ ከመግባቱ በፊት በቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለቦች የወጣትና የተስፋ ቡድን ተጫዋች ነበረ። ሆኖም ክለቦቹ ለወጣቶች ትኩረት አለመስጠታቸው በግሉ እንደሚጸጽተው ገልጾ ነገር ግን “በእኔ የደረሰ በሌሎች ታዳጊዎች ላይ እንዲደርስ አልሻም” ብሎ አሁን ሙሉ ጊዜውን ህጻናትን እና ታዳጊዎችን በማሰልጠን የተሻለ ነገ እንዲያስቡ እና እንዲያልሙ እያደረገ መሆኑን ተናግሯል።

ለእግር ኳስ እድገት የታዳጊዎች ስልጠና ወሳኝ መሆኑን በቅርቡ ከዳሽን ቢራ ፋብሪካ ጋር በመተባበር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በታዳጊዎች እግር ኳስ አሰለጣጠን ላይ ስልጠና የሰጡትን የአርሴናል አሰልጣኞች ትምህርት የሚያስታውሰው ወጣቱ አሰልጣኝ “በመጀመሪያ ደረጃ ለህጻናት የስልጠና እድል መስጠት ያስፈልጋል። እድሎችን ባሰፋህ ቁጥር ኤሊት የሆኑ ታዳጊዎችን ታገኛለህ። በእኛ አገር ያየህ እንደሆነ ግን ክለቦች የራሳቸው አካዳሚ የሌላቸው ሲሆን ያለው አንድ የመንግስት አካዳሚ ደግሞ በዓመት 20 ተጫዋቾችን ነው ከመላው ኢትዮጵያ መልምሎ የሚያሰለጥነው። ሌላው በውጭ አገር የተለመደው የታዳጊዎች አካዳሚ የሚያቋቁሙት ክለቦች ናቸው። መሆን ያለበትም እንደዛ ነው። ምክንያቱም ዛሬ በአካዳሚ የሚሰለጥኑት ልጆች ነገ የዚያ ክለብ ተጫዋቾች ስለሚሆኑ በተገቢው መልኩ ያሰለጥናቸዋል” ብሏል።

በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት እጅግ ዘመናዊ ሊባሉ የሚሉ ስታዲየሞች መገንባታቸውንና እየተገነቡ ያሉ ስታዲየሞች መኖራቸው በስፋት እየተዘገበ ይገኛል። ነገር ግን ይህ ለእግር ኳሱ እድገት የሚበጅ እንዳልሆነ ይነገራል። በዚህ ዙሪያ አስተያየቱን ኢትዮፉትቦል ዶትኮም የሰጠው አብይ “ከስታዲየሞች ግንባታ ይልቅ በታዳጊዎች ማዘውተሪያ ላይ ቢሰራ መልካም ነው። ነገር ግን ይህ ካልሆነ የእግር ኳሱ እድገት ሊሳካ አይችልም” ሲል ተናግሯል።

የአካዳሚው ሰልጣኝ የሆነውና የ14 ዓመቱ ታዳጊ ሳሙኤል ሲራክ ነገ ትልቅ እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ህልም አለው። በአሴጋ እግር ኳስ ክለብ አካዳሚ ውስጥ እየሰለጠነ ሲሆን “በአካዳሚው መሰልጠን ከጀመርን በኋላ የቡድን አንድነት ስሜት እና ህብረት አግኝተናል። በየአንዳንዳችን ላይ የክህሎት መሻሻል አይተናል” ሲል ይናገርና “ባለፈው ዓመት ለተመሳሳይ ውድድር ወደ ስዊድን አቅንተን ጥሩ ልምድ ይዘን ተመልሰናል። በስዊድን ቆይታችን የተመለከትኩት በእኛ እና በእነሱ በውድድሩ ተሳታፊ ከነበሩ ቡድኖች መካከል ሰፊ ልዩነት መኖሩን ነው። በተለይ በፊዚካል ፊትነስ እና በፍጥነት በኩል እኛ ገና ወደ ኋላ የቀረን መሆኑን ነው። ዘንድሮ ወደ ስዊድን ከመሄዳችን በፊት በድክመቶቻችን ላይ ሰርተን ከሄድን ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ይዘን እንደምንመለስ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል። ታዳጊው ልጅ አያይዞም “እግር ኳሳችን እንዲያድግ የመጀመሪያ ትኩረት ማድረግ ያለብን በህጻናት ላይ ነው። በውጭ አገር ያየህ እንደሆነ ትኩረታቸው በሙሉ በህጻናቱ ላይ ነው። በእኛ አገር ያለው ልምድ ግን በ20 እና በ21 ዓመታቸው ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ገብተው ሲጫወቱ ታያለህ። ይህ መስተካከል አለበት” ሲል ተናግሯል።

 


ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!