Recently Posted News
  የዝውውር ዜናዎች
ሐምሌ 08, 2008

የዝውውር ዜናዎች

በይርጋ አበበ

ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ከክለብ ክለብ የሚዘዋወሩበት የዝውውር መሰኮት ከተከፈተ አንድ ሳምንት ሞላው። በእነዚህ ስምንት ቀናት ውስጥ ከፍተኛ የዝውውር መረጃዎች ባይወጡም መጠነኛ መረጃዎች ግን እየወጡ ነው። ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች ግዙፍ ሊባሉ የሚችሉ የዝውውር ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ምንጮች ገልጸውልናል።

ፈረሰኞቹ

ከመከላከያ ጋር ስኬታማ ጊዜ ያሳለፈውንና በቅርቡ ለሲዳማ ቡና ይፈርማል ተብሎ በስፋት ሲነገርለት የቆየውን ፍሬው ሰለሞን ወይም ጣቁሩን ማስፈረማቸውን ምንጮች ገልጸዋል። በምን ያህል የዝውውር ሂሳብ እንደፈረመ ባይነገርም ከክለቡ ውስጥ አዋቂዎች በደረሰን መረጃ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ለቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ ተጫዋች እስከ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ወጭ ሳያወጣ እንዳልቀረ ተነግሯል።

ከውል ውጭ የሆነው ወጣቱ አጥቂ ዳዋ ሁጤሳ ከፈረሰኞቹ ጋር ለመቆየት ፍላጎት አለው። በሌላ በኩል ደግሞ ተጫዋቹን ሀዋሳ ከነማን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ ክለቦች እየፈለጉት ነው። ክለቡ እና ዳዋ ስምምነት ላይ ባይደርሱም በዚህ የዝውውር መስኮት ማረፊያው የት ሊሆን እንደፈሚችል ለማወቅ ግን የቀናት እድሜ ብቻ ነው የሚያስፈልገው።

ኢትዮጵያ ቡና

ባለፈው ዓመት በቅጣት የውድድር ዓመቱን ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና በዝውውር ጉዳይ ሰፊ ትኩረት የሳበ ክለብ ሆኗል። ክለቡን ለአንድ ዓመት የመሩት ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ኮንትራታቸው በመጠናቀቁ ዛሬ ወደ ቤልግሬድ በርረዋል። የፖፓዲችን ተተኪ ለማስፈረምም ቡና ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ከንግድ ባንክ ፈርሞ ቡናን በከፍተኛ ደረጃ ባይሆንም በጥሩ ብቃት ያገለገለው አማካዩ ኤሊያስ ማሞ ከኮንትራት ነጻ ሆኗል። ክለቡ ለተጫዋቹ ከታክስ ነጻ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ቢያቀርብለትም ኤሊያስ ግን ከሁለት ሚሊዮን ብር በታች ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለሁም ብሏል። በዚህም ምክንያት የሁለቱ ወገኖች ድርድር በሂደት ላይ ይገኛል።

ከዳዊት እስጢፋኖስ ቡናን መልቀቅ በኋላ ክለቡን በአምበልነት የመራው አመለ መልካሙ መስዑድ መሃመድም ከቡና ጋር በኮንትራት ጉዳይ እየተደራደረ ሲሆን በቅርቡም እልባት ያገኛል ተብሏል። ቡና ለመስዑድ እስከ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ክፍያ ሳያቀርብ እንዳልቀረም ተገልጿል።

ከአሰጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም ጋር አይስማማም ተብሎ የሚታማው አብዱልከሪም መሃመድ ማረፊያውን ኢትዮጵያ ቡና አደረገ። ኳስ አቀጣጣዩ አብዱልከሪም ወይም “ምርምር” ኤሊያስ ማሞ ኮንትራቱን ካላራዘመ የቦታው ትክክልኛ ምትክ ይሆናል ተብሎ በቡና ቤት ተስፋ ተጥሎበታል። በሌላ በኩል ኳስን ተረጋግቶ የሚጫወተው ተከላካዩ ኤፍሬም ወንድወሰን ከቡና ጋር ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ለመጫወት ኮንትራቱን አደሰ። ተከላካዩ በቡና ደስተኛ መሆኑን ደጋግሞ ሲገልጽ የሚሰማ ሲሆን በአዲሱ ኮንትራቱ መሰረትም ዳጎስ ያለ ደመወዝ ሳይቀርብለት እንዳልቀረ ከክለቡ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ኤሌክትሪክ

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ ላለመውረድ እየተጫወተ የሚገኘው ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ የመቅጠር ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል። ለክለቡ ቅርብ የሆኑ የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ምንጮች እንዳረጋገጡልን ኤሌክትሪክ የቀድሞውን የቡና አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲችን ይፈልጉታል። ኢትዮጵያን እንደወደዷት ደጋግመው የሚናገሩት አሰልጣኝ ፖፓዲችም “ክለቡ ከፈለገኝ ደስተኛ ነኝ” ማለታቸውን ሰምተናል።

በሌላ በኩል ኤሌክትሪክ ለፖፓዲች ቀደም ሲል ቡና ይከፍለው የነበረውን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ደመወዝ ከመክፈል በአገር ውስጥ አሰልጣኝ መመራትን ምርጫው ለማድረግ እንዳሰበም ተገልጿል። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ለአምስት ወራት ለማሰልጠን የተስማማውን ገብረመድኅን ኃይሌን የመጀመሪያ ምርጫው አድርጓል። ገብሬመድኅን ከጦሩ ጋር ያለው ኮንትራት የተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ አዲስ ነገር ካልተፈጠረ ምናልባት ኮረንቲዎቹን ለማሰልጠን ሊስማማ እንደሚችል ተገምቷል።

ሌሎች የዝውውር ዜናዎች

ከፕሪሚየር ሊጉ የወረደው ዳሽን ቢራ እና አምበሉ አስራት መገርሳ በኮንትራት ጉዳይ እየተወያዩ ነው። አስራት መልቀቂያ ከተሰጠው ሳይውል ሳያድር ማረፊያውን ኢትዮጵያ ቡና ለማድረግ አስቧል። በቡና ደጋፊዎች የሚወደደው አስራት እሱም በግሉ ለቡና መጫወት የቆዬ ምኞቱ መሆኑን ለተጫዋቹ ቅርብ የሆኑ ምንጮቻችን ገልጸውልናል።

ከአርባምንጭ ከነማ ጋር ላለመውረድ ሲጫወት የከረመው ኳስ አቀጣጣዩ ታደለ መንገሻ በቀጣዩ የውድድር ዓመትም የጋሞ ጎፋ ዞኑን ክለብ ሊያገለግል እንደሚችል ሰምተናል። በኢትዮጵያ ቡና በጥብቅ እየተፈለገ ያለው ጥበበኛው አማካይ ለአርባምንጭ የሚፈርም ከሆነ በሊጉ ታሪክ ከፍተኛው ተከፋይ ይሆናል ሲሉ ከአርባምንጭ የደረሱን መረጃዎች አመልክተዋል።


ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!