Recently Posted News
  የፕሪሚየር ሊጉን ውድ ተጫዋቾች ያስፈረመው ኢትዮጵያ ቡና ምን አይነት አሰላለፍ ይጠቀማል?
ነሐሴ 22, 2008

በይርጋ አበበ

ከአስር ወራት በፊት ነው በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ቡና ከንግድ ባንክ ጋር ተጫውቶ አንድ ለባዶ ካሸነፈ በኋላ ለአዛውንቱ ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች “የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ይችላሉ?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው። በኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ታሪክ የመጀመሪያው የውጭ ዜጋ ሆነው በሚፋጀው የቡና አሰልጣኝነት ወንበር ላይ የተቀመጡት ፖፓዲች ለጥያቄው መልስ ሲሰጡ “ዋንጫውን ለማንሳት የደደቢቱ 11 ቁጥር ያስፈልገኛል” አሉ። አሰልጣኙ ሳሙኤን ሳኑሚን በስም ስለማያውቁት ነበር በቁጥር የገለጹት። በዚያን ዓመት ከደደቢት ጋር ውል የነበረው ናይጄሪያዊው የቀድሞ ፈረሰኛ ሳሙኤል ሳኑሚ በዚህ ዓመት የዝውውር መስኮት ደደቢትን ተሰናብቶ በወር 100 ሺህ ብር ያልተጣራ ደመወዝ እየተከፈለው ለሁለት ዓመት ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ተስማምቷል።

ቡና ለሳኑሚ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙ እስካሁን ድረስ በሊጉ ታሪክ ውዱ ዝውውር ሲሆን ከሳኑሚ ቀደም ብሎ በሊጉ ታሪክ እጅግ ውዱ ተከፋይ የነበረው የቡናው ኤሊያስ ማሞ ውሉን ያደሰበት ነበር። ይህም ማለት ቡና በሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለአራት ተጫዋቾች ማለትም ለአስቻለው ግርማ አንድ ነጥብ 35 ሚሊዮን ብር፣ ለአምበሉ መስዑድ መሀመድም በተመሳሳይ አንድ ነጥብ 35 ሚሊዮን ብር፣ ለኤሊያስ ማሞ አንድ ነጥብ 50 ሚሊዮን ብር እና ለሳሙኤል ሳኑሚ አንድ ነጥብ 56 ሚሊዮን ብር የተጣራ የፊርማ ክፍያ መክፈል ችሏል። ከአራቱ ውድ ፈራሚዎች በተጨማሪ ደግሞ ለቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካይ አብዱልከሪም ሁሴን ወይም ምርምር፣ ለተከላካዮ ኤፍሬም ወንድወሰን እና ለግብ ጠባቂው ዮሃንስ በዛብህ የፊርማ ክፍያ በመክፈል ቡድኑን የማጠናከር ስራ እያከናወነ ሲሆን የዳሽን ቢራውን አስራት መገርሳን ለማስፈረምም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ከላይ ከተጠቀሱት የተጫዋቾች ዝውውር በተጨማሪ አዳዲሶቹ ተጫዋቾች እና ነባሮቹ የክለቡ ተጫዋቾች ከአዲሱ ሰርቢያዊ የ55 ዓመት ጎልማሳ አሰልጣኝ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ምን ይመስላል? የቡድኑ አሰላለፍስ ምን ሊመስል ይችላል? የሚሉትን ሁለት ነጥቦች እንዲሆም ክለቡ በሊጉ ሊኖረው ስለሚችል ደረጃ መጠነኛ ሙያዊ ዳሰሳ አካሂደናል ከዚህ በታች ቀርቧል።

የተጫዋቾቹ የእርስ በእርስ እና ከአሰልጣኙ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት

ሰርቢያን ጨምሮ አብዛኞቹ ምስራቅ አውሮፓዊያን ዜጎች በባህሪያቸው ቁጥብነት እና ለስነ ስርዓት ተገዥ የመሆን ባህሪ አላቸው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አገራቱ በኮሚኒስታዊ ስርዓት ማለፋቸው እና አብዛኞቹ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ መሆናቸው የፈጠረላቸው ይመስላል። አዲሱ የቡና አሰልጣኝ ነጎሻ ቪቺቼቪች ወይም ኦሽኬ ከሰርቢያ የመጡ መሆናቸው ታውቋል። አሰልጣኙ ካላቸው ተፈጥሯዊ ቁጥብነትና ስነ ስርዓት አክባሪነት የተነሳ ከተጫዋቾቻቸው ጋር ምን አይነት ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል? የሚለው ነጥብ ትልቅ ጥያቄ ነው።

ከአንድ ዓመት በፊት ከቡና ጋር በቆዩት ድራጋን ፖፓዲች ላይ አብዛኞቹ ሲኒየር ተጫዋቾች ደስተኛ እንዳልነበሩ ይገለጻል። በተለይ አንዳንዶቹማ ክለቡን እስከመልቀቅ የሚያደርስ ውሳኔ ለማሳለፍም ደርሰው እንደነበረ ይነገራል። ከፖፓዲች በፊት የነበሩት እንደ ጥላሁን መንገሻ እና ጳውሎስ ጌታቸው አይነት ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞችም በተጫዋቾች በተገቢው መልኩ የሚከበሩ እንዳልነበረ ከክለቡ የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል። አዲሱ አሰልጣኝ በኤሊያስ ማሞ እና አስቻለው ግርማ ለሚመሰረተው አጨዋወታቸው ከተጫዋቾች ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ከወዲሁ ማወቅ ባይቻልም ከክለቡ ባገኘነው መረጃ ለማወቅ እንደቻልነው ግን አሰልጣኙ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ስለ ቡና እና አጠቃላይ ስለ ሊጉ በሚገባ መረጃ ሰብስበው መምጣታቸውን ነው።

ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ከሚታሙባቸው ደካማ ጎኖቻቸው መካከል በዋነኛነት ጠንካራ የፊትነስ ስራ አለመውደዳቸውና በምሽት መዝናኛ ክለቦች አዘውትረው መዝናናትን መፈለጋቸው የሚሉት ይጠቀሳሉ። በዚህ በኩል የቡና ተጫዋቾች ከአሰልጣኛቸው ጋር እንዳያጋጫቸው አሰልጣኙ በቅድሚያ የወሰዱት እርምጃ በስፖርት ሳይንስ የሁለተኛ ዲግሪ ባለቤት የሆኑትን አቶ ዘሩ በቀለን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነታቸው ወስዶ ለክለቡ ፊትነስ ኮች አድርጎ መቅጠሩ ምናልባት የፊትነስ ጉዳዮችን ለመመለስ መልስ ይሆናቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ምክንያቱም እኒህ ባለሙያ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው የአገራቸውን ልጆች ደካማ እና ጠንካራ ጎን ለይተው ስለሚያውቁ በተጫዋቾች የሚወደዱ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚችሉ ተስፋ ተጥሎባቸዋልና። አሁን በሀዋሳ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እየሰሩ ያሉት ቡናዎች አሁን ባለው የቡድን ስብስብና የአሰልጣኙ ስራ ደስተኛ መሆናቸውን የቡድኑን ቅድመ ዝግጅት የተመለከቱ የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ምንጮች አስታውቀዋል።

ሌላው የተጫዋቾችን እና አሰልጣኞችን ግጭት ከሚያባብሱት መንገዶች አንዱ እና ዋነኛው የስፖርተኞቹ ኢጎ ነው። ተጫዋቾች ለአሰልጣኞች አለመታዘዝ እና የተጫዋቾች የምሽት መዝናኛ ቤቶች አድማቂ መሆን በቡና ክለብ ውስጥ ላለመፈጠሩ ማረጋገጫ ባይኖርም በቅርቡ በምሽት መዝናኛ ክለቦች ሲዝናና በአንድ አይኑ ላይ የብሌን መፍሰስ አደጋ የደረሰበት የአዳማ ከነማው ታከለ አለማየሁ ጉዳት በኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ላይ የማንቂያ ደወል ሳይደውልባቸው እንዳልቀረ ይታመናል።

የተጫዋቾች እርስ በእርስ ግንኙነትን በተመለከተ መስመሩን ስቶ በቡድኑ የሜዳ ላይ ውጤትም ሆነ በክለቡ ካምፕ ውስጥ መጥፎ አሻራውን ጥሎ እንዳያልፍ የአሰልጣኙ እና የሲኒየር ተጫዋቾች ሚና የጎላ ነው። ለዚህ ደግሞ በተለይ ለመጫወት የሚደረገው ፉክክር ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል አሰልጣኙ ሊጫወቱት የሚገባ ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ቡና ደግሞ በአንድ ቦታ ላይ የሚጫወቱ በርካታ ተጫዋቾችን የያዘ በመሆኑ እና የአብዛኞቹ ተጫዋቾች ግላዊ ባህሪም ኢጎ የሚያጠቃቸው መሆኑ ለዚህ ችግር መፈጠር ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ይጠበቃል።

የክለቡ አሰላለፍ

አስቻለው ግርማ፣ ሳሙኤል ሳኑሚ፣ አብዱልከሪም ሁሴንን እና ዮሃንስ በዛብህን በአዲስ መልክ ያስፈረመውና በቅርቡ አስራት መገርሳን ለማስፈረም የመጨረሻ ሙከራውን እያደረገ ያለው ኢትዮጵያ ቡና ከነባር ተጫዋቾቹ መካከል ደግሞ ኤፍሬም ወንድወሰን፣ መስዑድ መሀምድ እና ኤልያስ ማሞን ውላቸውን አድሷል። እነዚህ የተጫዋቾች ፊርማዎች በቡድኑ አሰላለፍ ላይ ሊኖራቸው የሚችለው ፉክክር ምን ሊመስል እንደሚችል ከዚህ በታች እንመለከታለን።

ሰርቢያዊው የ55 ዓመት ጎልማሳ አሰልጣኝ በግብ ጠባቂ መስመሩ ቤኒናዊውን ሀሪሰንን እንደሚጠቀሙ ግልጽ ነው። በመሃል ተከላካይ መስመራቸው ደግሞ ኤፍሬም ወንደወሰንን ከወንድይፍራው ጋር ለማጣመር እንደሚያስቡ የተጠበቀ ሲሆን ሁለቱ ፈጣን የመስመር ተከላካዮች አብዱልከሪም መሀመድ እና አህመድ ረሺድ ለግራ እና ቀኝ መስመር ቦታዎቹ የቅድሚያ ግምት የተሰጣቸው ተጫዋቾች ናቸው። በክለቡ የኋላ መስመር ላይ የሚሰለፉትን ተጫዋቾች ለመምረጥ ለአሰልጣኙ ፈተና የሚሆንባቸው አይሆንም። ለአሰልጣኙ ፈተና የሚሆነው በመሃል ሜዳው ላይ የሚሰለፉትን ተጫዋቾች መምረጡ ላይ ነው።

ከንግድ ባንክ የኮበለለው አብዱልከሪም ሁሴን ምርምር፣ ለ2008 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት እጩ ሆኖ የቀረበው ጋቶች ፓኖም፣ አምበሉ መስዑድ መሀመድ፣ ኤርሚያስ በለጠ እና ውዱ የአማካይ መስመር ተጫዋች ኤሊያስ ማሞ በመሀል ሜዳ ስብስባቸው የያዙት ኦሽኬ በቅርቡ ደግሞ አስራት መገርሳን የሚያስፈርሙ ከሆነ ለመሰለፍ የሚደረገውን ፉክክር ይበልጥ ያጠነክረዋል። ከአንድ ዓመት የሀዋሳ ከነማ ቆይታ በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ የተመለሰው ፈጣኑ አቻለው ግርማ፣ ባለፈው የውድድር ዓመት በምርጥ ብቃት የጨረሰው እያሱ መንገሻ፣ ወጣቱ አማኑኤል ዮሀንስ፣ የቀድሞው ፈረሰኛ ዮሴፍ ደሙዬ፣ እና ከወጣት ቡድኑ ያደጉት ሁለት ወጣት የመስመር አማካዮች የቡናን የመስመር ክፍል ለመቆጣጠር የሚፎካከሩ ተጫዋቾች ናቸው። ያለፈው ዓመት የክለቡ ከፍተኛ ጎል አግቢ የሆነው ያቡን ዊሊያም፣ በመጨረሻው የውድድሩ ወራት ወደ ምርጥ ብቃቱ የተመለሰው ወጣቱ ሳዲቅ ሴቾ እና አዲሱ ፈራሚ ሳሙኤል ሳኑሚ ደግሞ በአጥቂ መስመሩ ላይ ለመሰለፍ ፉክክር የሚያደርጉ ተጫዋቾች ናቸው።

አሰልጣኝ ኦሽኬ እነዚህን ፈተናዎች በብቃት እና ጥበብ በተሞላበት መንገድ መፍታት ከቻሉ ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ የሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይጠበቃል። ምናልባትም የተጫዋቾች ጉዳት እና ቅጣት ካልገጠመውም ክለቡ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ጥሩ እድል እንዲኖረው የሚያስችል ስብስብ ይዟል ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም የሚጀመር ይሆናል። 

 


ethiopianathletics.net
 
Share this News/Article on your facebook page:    
 
arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text

arachni_name [65 days ago.]
 arachni_text)

arachni_name) [65 days ago.]
 arachni_text

Your Comment /አስተያየት
Name:
Email:
 
 
Comment:  *
 
 
 
 
Copyright© 2014 Ethiopianathletics.net All rights reserved!