በዳሶ ሆራ ወደ ወልድያ አመራ
ህዳር 02, 2007

የቀድሞው የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ አጥቂ በዳሶ ሆራ ወደ አዲሱ የፕሪሚየር ሊግ ተወዳዳሪው ወልድያ እግር ኳስ ክለብ መዘዋወሩን ከወልድያ ስፖርት ክለብ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የወልድያ ስፖርት ክለብ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ዘመላክ ለኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም እንደገለጹት አጥቂው በዳሶ ሆራ ከአንድ ሳምንት በፊት ጀምሮ የሰሜኖቹ ንብረት ሆኗል። “ያለብን ልምድ ያለው ተጫዋች እጥረት ነው ለዚህ ደግሞ በዳሶ ሆራ በተለያዩ ክለቦችና በብሔራዊ ቡድን ያሳለፈውን ሰፊ ልምድ ይዞ ወደ ክለባችን ሲመጣ በብዙ መልኩ ይጠቅመናል” ሲሉ ለኢትዮ ፉትቦል ተናግረዋል። 

ወልድያ ከነማ ከብሔራዊ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያድግ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረለትን አጥቂውን ተስፋዬ ነጋሽን አብሮት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ላደገው አዳማ ከነማ መሸጡ ይታወሳል። በተቃራኒው በዳሶ ሆራ ከመከላከያ ወደ አዳማ ከነማ  ተዘዋውሮ የነበረው በተጀመረው የውድድር ዓመት ነበር። ሆኖም ለጊዜም ምክንያቱ ባልተገጸ ችግር አዳማ ከነማና በዳሶ ሆራ ውላቸውን በማፍረሳቸው ክለብ አልባ ሆኖ ነበር። ይህንን የተረዳውና በልምድ ችግር እየተጎዳ እንደሆነ ያመነው ወልድያ እግር ኳስ ክለብ የበዳሶ ሆራ አዲስ ማረፊያ ሆኗል። 

በፕሪሚየር ሊጉ የሰሜን ኢትዮጵያው ተወካይ ወልድያ ስፖርት ክለብ  ከበዳሶ ሆራ በተጨማሪ የቀድሞውን የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሳሙኤል ደግፌንም አስፈርሟል። ያለፉትን ሶስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በጉዳት ያልተሰለፈው አማካይ ተከላካዩ ዳንኤል ሞገስም ከጉዳቱ አገግሞ ለቀጣይ ጨዋታዎች ዝግጁ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል። አቶ ተፈራ “በተለይ አማካዩ ዳንኤል ሞገስ በጉዳት ያለፉትን ጨዋታዎች አለመሰለፉ የክለባችን የተከላካይ መስመር ላይ ሚዛኑን እንዳይጠብቅ ችግር ፈጥሮብን ነበር ሆኖም ግን አሁን የዳንኤል ወደ ጨዋታ መመለስ የክለቡን ክፍተት ሊደፍን ይችላል። ወደፊትም ጠንካራውን ወልድያ ስፖርት  ክለብ የምናይበት ቀን ሩቅ አይሆሆንም” ሲሉ ተናግረዋል።   

በተያያዘ ዜና ከዚህ ቀደም ወልድያ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ይባል የነበረው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ስሙ ወልድያ ስፖርት  ክለብ የተባለ መሆኑንና መገናኛ ብዙሃንም ወልድያ ስፖርት ክለብ የሚለውን ስሙን እንዲጠቀሙ ሥራ አስኪያጁ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል። 


ዘጋቢ፦ ይርጋ አበበ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!