ያለፉት አራት ዓመታት የአፍሪካ ዋንጫ አብይ ክስተቶች ዳሰሳ
ህዳር 07, 2007

የአፍሪካ ዋንጫ ከመነሻው ጀምሮ በበርካታ ፈተናዎች አልፎ ከዚህ የደረሰ ውድድር ነው።  በግብጽ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን አስተባባሪነት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያለፋቸውን መሰናክሎች ሙሉ በሙሉ መዳሰስ ባይቻልም ባለፉት አራት ዓመታት በውድድሩ ላይ የተደቀኑ ፈተናዎችን ለመዳሰስ እንሞክራለን። 

የአውሮፓ ክለቦች ተጽእኖ እና የፊፋ ጣልቃ ገብነት

ታላላቆቹና ባለጸጋዎቹ የአውሮፓ ክለቦች በቡድናቸው ውስጥ አፍሪካውያን ተጫዋቾችን በማሰለፍ ይጠቀማሉ። ክለቦቹ በአፍሪካውያን ተጫዋቾች አገልግሎት ቢደሰቱም የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበርካፍ በየሁለት ዓመቱ በሚያስተናግደው የአህጉሪቱ ትልቁ የስፖርት ውድድር ግን ደስተኛ አይደሉም። ጭራሽ በተደጋጋሚ ጊዜ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ይሰማ ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የክለቦቹ ተደጋጋሚ ቅሬታ እረፍት የነሳው ፊፋም የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበርንካፍ የውድድር ጊዜውን ከወርሃ የካቲት ወደ ወርሃ ሰኔ እንዲያሸጋግር ትዕዛዝ መሰል አስተያየት ይሰጠዋል። 

በተደጋጋሚ እንደተገለጸው በአብዛኛው የአፍሪካ አገራት የክረምት ወቅት የሚጀምረው ከሰኔ መባቻ ጀምሮ በመሆኑ የክረምቱን ወቅት ማባት ተከትሎ የሰማይ መስኮቶች ውሃ መቋጠር ይሳናቸዋል። ይህ ደግሞ ድሮም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆኑት የአህጉሪቱ ስታዲየሞች ለጨዋታ የማይመቹ ያደርጋቸዋል። ይህን የተገነዘበው ካፍም የፊፋን ውሳኔ “አሻፈረኝ” ሲል መለሰ። ፊፋ ደግሞ እንደዛ ማድረግ ካልቻልክ ሌላ ዘዴ ፍጠር እንጅ የአውሮፓ ክለቦችን ጥያቄማ የማትቀበልበት ምክንያት አይኖርም ሲል ደጋግሞ ጉትጎታውን ሲያሰማ የአለቃውን ትዕዛዝ እምቢ ማለት የማይችለው ካፍም ውድድሩን ቀድሞ ይካሄድበት በነበሩ ሙሉ ቁጥር ዓመታት Even Number Years ወደ ጎደሎ ቁጥር ዓመታት Odd number years በመቀየር ውድድሩን ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ማካሄድ ጀመረ ። 
 
የውድድር ዓመቱ በመቀየሩ ደግሞ በውድድሩ ላይ የነበረውን የፉክክር ስሜት ከመቀነሱም በላይ የመጀመሪያውን የጎደሎ ቁጥር ዓመት ዝግጅት የሚያዘጋጅ አገር መጥፋቱ ለካፍ ራስ ምታት ሆኖ ነበር። ዳሩ ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ 19ኛውን የዓለም ዋንጫ ያዘጋጀችው ደቡብ አፍሪካ ካላት የእግር ኳስ መሠረተ ልማት የተነሳ ውድድሩን እንድታዘጋጅ ትዕዛዝ አይነት ልመና ከካፍ ደረሳት። ደቡብ አፍሪካ የካፍን ምላሽ በይሁንታ ብትቀበልም ሌላው የካፍ ፈተና የሆነው ደግሞ የተወዳዳሪ አገሮችን ለተሳትፎ የሚያበቃበት ቅድመ ውድድር ማጣሪያ ፎርማት እንዴት ላድርገው የሚል ነበር። እንደሚታወሰው በካፍ ታሪክ ተደርጎ የማይታወቅ የውድድር ፎርማት ተካሂዶ ደቡብ አፍሪካም ሳታስበው ቤቷ ድረስ ሰተት ብሎ በመጣላት ድግስ ያለ ፈተና ለውድድሩ ቀርባ ጨዋታው ተካሄደ። 

የሰሜን አፍሪካ ሃገራት  እግር ኳስ ደረጃውን  እየለቀቀ ነው 

የአፍሪካ ዋንጫ ለ29 ጊዜያት የተካሄደ ሲሆን ከእነዚህ ጊዜያት መካከል የሚበልጠውን ጊዜ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ የቻሉት የተጠቀሰው የሰሜን  አፍሪካ አገሮች ናቸው። ግብጽ ብቻዋን ሰባት ጊዜ በማንሳት በአህጉሩም በክፍለ አህጉሩም የበላይነቷን ስታረጋግጥ ሞሮኮ፣ አልጀሪያና ቱኒዚያ ደግሞ ሌሎቹ የሰሜን አፍሪካ ታላላቅ የእግር ኳስ አገሮች ናቸው። የወቅቱ የአፍሪካ ቁጥር አንድ የእግር ኳስ አገርም ሰሜን አፍሪካዊቷ አልጀሪያ ነች።

የሰሜን አፍሪካ እግር ኳስ ግን የቱኒዚያዊው “የቡአዚዚ አብዮት” ጥቁር ጥላውን አሳርፎበት ታላቅነቱንም እየተቀማ ይገኛል። ለአብነት ያህልም የአህጉሪቷ የበላይ የነበረችው ግብጽ የ2013 የደቡብ አፍሪካው ድግስ ያለፋት ስትሆን ሊቢያም በ2017 አዘጋጀዋለሁ ብላ ከካፍ ያገኘችውን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት እድል “አይ ይቅርብኝ ሰላም አጥቻለሁ” ብላ ለካፍ ካሳወቀች ቆይታለች። የክፍለ አህጉሩ እግር ኳስ ደረጃው ዝቅ ብሎ መታየት የቻለው በአፍሪካ ዋንጫ ብቻ ሳይሆን በእግር ኳስ ተጫዋቾቹ ደረጃ ላይም ጭምር ነው። ለዚህ ሃሳብ ማጠንከሪያ የሚሆነው ደግሞ ከአልጀሪያ ውጭ ያሉ የሰሜን አፍሪካ አገር እግር ኳስ ተጫዋቾች በአውሮፓ የነበራቸው ሚና ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ነው።
የዓለም ስጋት የሆነው ኢቦላ ገዳይ በሽታ ነው ለዚያውም በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው በመተላለፍ። ይህ ገዳይ ቫይረስ መጀመሪያ በታየባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም። በኢኮኖሚው ብቻ ያልተመለሰው የኦቦላ ተጽእኖ በተጠቀሱት አገሮች ዜጎች ላይም የማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ አስከትሏል። እንደ ካናዳ እና አውስትራሊያ አይነት አገሮች ከምዕራብ አፍሪካ በተለይም ሴራሊዮንና ላይቤሪያ ጋር የነበራቸውን የአየር በረራ ለጊዜው በማቋረጣቸው የኢቦላ ተጽእኖ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ መድረሱን አመላካች ነው።  

ለዓለም አስጊ የሆነው ቫይረስ መነሻውን ምዕራብ አፍሪካ ያድርግ እንጅ የ2015ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት እድል ተሰጥቷት የነበረችው ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮም “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” በሚለው ብሂል ተመርታ “የውድድሩ አዘጋጅነት ይቅርብኝ ኢቦላ ከሚያደርስብኝ ዘርፈ ብዙ ጉዳት ይልቅ ካፍም ሆነ ፊፋ የሚጥሉብኝን ቅጣት ብቀበል ይቀለኛል” ብላ ውድድሩን ላለማዘጋጀት ያሳየችውን እምቢታ ገፍታበታለች። ኢቦላም የሚያደርሰውን አሉታዊ ተጽእኖ ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ወደ ስፖርቱ ማስፋፋቱን የሞሮኮ ውሳኔ አሳይቷል። በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተደቀነ አዲስ ፈተና ኢቦላ። 
ይቀጥላል

ዘገባ፦ ይርጋ አበበ 
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!