የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደረጃው ወርዷል?
ህዳር 07, 2007

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋሊያዋቹ በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ነበሩ። በውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታቸውም የ28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋን ዛምቢያን ገጥመው አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ ከሜዳ ቢሰናበባቸውም አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት ጨዋታውን ጨረሱ። በርካታ የስፖርት አፍቃሪዎችም ቡድኑን “ከአይን ያውጣህ” ብለው አድናቆታቸውን ቸሩት። አድናቆት እንደ ጎርፍ ከተቸረው ከዚያ ጨዋታ በኋላ ዋሊያዎቹና ውጤት ሆድና ጀርባ ሆኑ በተከታታይ ሁለት የምድባቸው ጨዋታዎች ስድስት ግብ ተቆጥሮባቸው አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶባቸው ከምድባቸው አራተኛ ደረጃን እንዲሁም ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ከነበሩ 16 አገሮችም 16ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ።

Saladin vs Mosse


ከላይ የተመዘገበው ተከታታይ ሽንፈት ተስፋ ያላስቆረጣቸው የብሔራዊ ቡድኑ ደጋፊዎች “ዋናው እንኳን ወደ ውድድር መድረኩ ተመለስን እንጅ ውጤት በቀጣይነት የሚገኝ ነገር ነው” ሲሉ ተጽናኑ። አስተያየት ሰጭዎቹ ትክክል ናቸው ብሔራዊ ቡድኑ ከአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከራቀ 31 ዓመታትን አስቆጥሮ ስለነበር ወደ መድረኩ መመለሱ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው ብሎ መቀበል ጤነኝነት ያለው አስተያየት ነው። የተወሰኑ አስተያየት ሰጭዎች ደግሞ “በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባንካፈል ኖሮ ውርደት ይሆን ነበር እንጅ መካፈላችን ስኬት ተደርጎ ሊቆጠር አይገባውም” ሲሉ ጎራ ለይተው ይሞግታሉ። ሃሳባቸው ውሃ እንዲያነሳ የሚያቀርቡት ምክንያት ደግሞ ወደ አፍሪካ ዋንጫ በሚወስደው መንገድ ላይ ዋሊያዎቹ ያገኟቸውን ቡድኖች ወቅታዊ የእግር ኳስ ደረጃ በመጥቀስ ነው። 

በጊዜው የአቶ ሰውነት ቢሻው ጦር የተፋለመው ከቤኒንና ሱዳን ጋር ሲሆን ከሁለቱ አገሮች ጋር ባደረገው የደርሶ መልስ ጨዋታ ስድስት ግቦች ተቆጥረውበት በምትኩ ደግሞ ስድስት ግቦችን አስቆጥሮ ነበር። ከዋሊያዎቹ ጋር የተጋጠሙት ቤኒንና ሱዳን በወቅቱ የነበራቸው የእግር ኳስ ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች የተለያዩ መመዘኛዎችን አቅርበው ይከራከሩ ነበር። 

የአቶ ሰውነት ቢሻው ስብስብ ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎውና ለብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ምድቡን በበላይነት ከመጨረሱ በተጨማሪ በቻን ዋንጫና በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫሴካፋ ላይ ተሳትፎ ያደረገ ቢሆንም በቻን ዋንጫ አንድም ግብ ሳያስቆጥር በሶስቱም ጨዋታዎች ተሸንፎ ከውድድሩ ወጣ በሴካፋ ደግሞ በሩብ ፍጻሜው ከውድድሩ ተሰናበተ በሱዳን ሁለት ለባዶ ተሸንፎ። ከእነዚህ ተደጋጋሚ ሽንፈቶች በኋላ አቶ ሰውነት ቢሻው ከእነረዳቶቻቸው ከኃላፊነት ሲነሱ ቦታቸውን ፖርቹጋላዊው ማሪያኖ ባሬቶ እንዲረከቡት ተደረገ። 

ሚስተር ማሪያኖ ባሬቶ የያዙት ቡድን አምስት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎችን አድርጎ በአራቱ ሲሸነፍ አንዱን ብቻ አሸንፏል። 12 ግቦች ሲቆጠሩበት በአጸፋው ደግሞ ሰባት ግቦችን አስቆጥሯል። ይህን ውጤት በመጥፎ ሪከርድ በሚመዘግቡና ውጤቱን በጸጋ ተቀብለው በሁለት ጎራ ተቧድነው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ። እውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደረጃው ካለፉት ሁለት ዓመታት የወረደ ነው ወይስ የተሻለ? የሚለውን ጥያቄ ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም የተወሰኑ ነጥቦችን አንስቶ ሃሳቡን ያስቀምጣል። ይህ ጽሁፍ የተዘጋጀው ይህኛውን አሰልጣኝ ከቀድሞው ጋር እያነጻጸሩ ማቅረብ አይደለም በወቅቱ ብሔራዊ ቡድን ላይ ተከሰተ የተባለው ቀውስ እውን ቀውስ ብቻ ነው? ከቀውሱ በስተጀርባ ያለውስ ምንድን ነው? የሚለውን ለማንሳት ብቻ ነው።

ቡድኑ በውጤት ደረጃ  

Sewenet Team

የማሪያኖ ባሬቶን ስብስብ ባስመዘገበው ውጤት ለመለካት ከሞከርን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ማግኘት ከነበረበት 15 ነጥብ ሶስት ብቻ ያሳካ ሲሆን 12 ተቆጥሮበት ሰባት ብቻ ማስቆጠሩ እንደ ስኬት ሊቆጠርለት አይገባም። ነገር ግን ቡድኑ የተጋጠመው ከየትኞቹ አገሮች ጋር ነው? የሚለውን ነጥብም አንስቶ መወያየት የሚገባ ይመስለናል። በአንድ ወቅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረችውን አልጀሪያን “አልጄሪያ በዓለም ዋንጫው የአፍሪካ ኩራት የኢትዮጵያ ደግሞ ስጋት” የሚል ርዕስ አስነብቦ ነበር። በጊዜው የጋዜጣው ሪፖርተር ያነሳቸው ነጥቦች የአልጀሪያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫው ያሳየው ጥንካሬ ለአህጉሪቱ እግር ኳስ እድገት የሚያስመሰግነው ቢሆንም የስነ ልቦና ዝግጅት በሌለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ ግን ስጋትን እንደሚያሳድር ነበር። ምክንያቱም ሁለቱ አገሮች በአፍሪካ ዋንጫው ማጣሪያ በአንድ ምድብ መደልደላቸውን ያወቁት ከዓለም ዋንጫው ቀደም ብሎ በመሆኑ ነው። 

ያም ሆኖ ግን የማሪያኖ ባሬቶ ስብስብ ከወቅቱ የአፍሪካ ቁጥር አንድ የእግር ኳስ አገር ጋር በደርሶ መልስ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አምስት ለሁለት በሆነ ድምር ውጤት ተሸንፏል። ይህ ሽንፈት ግን ቡድኑን እንደ ወደቀ ያስቆጥረዋል ወይ? ብሔራዊ ቡድኑ ከአልጀሪያ ጋር ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠረ መሆኑ ቡድኑ ከሜዳ ውጭ ከጠንካራ አገሮች ጋር ተጫውቶ ግብ ማስቆጠሩ ከቡድኑ ላይ የታየ አዲስ ለውጥ ነው።

 እንዲሁም ከማሊ ጋር የተደረገው ጨዋታ የቡድኑን መለወጥ እንጅ መውረድ የሚያሳይ ሆኖ አላገኘነውም። ቀደም ባሉት ረጅም ዓመታት የብሔራዊ ቡድናችንና የክለቦቻችን ትልቁ ችግር ሆኖ የዘለቀው ከሰሜንና ምዕራብ አፍሪካ አገራት ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በሽንፈት ነበር የሚጨርሰው። የአሁኑ ብሔራዊ ቡድን ግን አዲስ አበባ ላይ ከጨዋታ ብልጫ ጋር በማሊ የተሸነፈ ቢሆንም ባማኮ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሶስት ግቦችን አስቆጥሮ ማሸነፍ ችሏል። ይህ ደግሞ ቡድኑ ወደቀ ከሚለው ነጥብ በላይ ሊነሳ የሚገባው ይመስለናል። 

በዝግጅት በኩል

Bareto Team

አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ቡድኑን በተረከቡበት ወቅት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተጠናቀቀ ነበር። ለዚህም ነው አሰልጣኙ የመጀመሪያ ቡድናቸውን ሲመርጡ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ዘመን የነበሩ ተጫዋቾችን እንዳሉ መርጠው የነበረው። ነገር ግን ቀስ በቀስ ቡድኑን በወጣቶችና በተተኪዎች ላይ በመመስረት ላይ ትኩረት አደረጉ። አሰልጣኙና ቡድኑ በደንብ ሳይተዋወቁ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው ደረሰ። በዚያ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚከተለው ዘመኑን ያላማከለ አሰራር የተነሳ ክልል ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች አሰልጣኙ እየተገኙ ጨዋታዎችን የሚከታተሉበትን ሁኔታ አላመቻቸም ነበር። በዚህ አጭር ዝግጅት ከጠንካራዎቹ አልጄሪያና ማሊ ጋር ተደልድሎ የተመዘገበን ውጤት እንደ ውድቀት ቆጥሮ መጮህ ምናልባት ሌላ የግል ፍላጎት ከሌለ በስተቀር በቡድኑ ላይ የሚፈጠር አንዳች መልካም ለውጥ ይኖራል ብሎ ማመን ይከብዳል። 

በተተኪዎች ላይ የተሰራ ሥራ

አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ሥራቸውን በጀመሩበት የመጀመሪያ ቀን ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ የተናገሩት “የመጣሁት የነገውን ብሔራዊ ቡድናችሁን ልሰራላችሁ ነው” ብለው ነበር። ምንም እንኳ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞችና ለስፖርቱ ቅርበት ያላቸው ሰዎች አሰልጣኙን ቢተቿቸውም በተተኪዎች ላይ የሰሩት ሥራ ግን የአሁኑን ቡድን ስኬት ያሳየ ሆኗል። አስራት መገርሳን የመሰለ የተሳካለት አማካይ ማግኘት የሚቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ይህን የተረዱት አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶም ናትናኤል ዘለቀ የተባለን ለክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ጨዋታ እንኳ አድርጎ የማያውቅን ተጫዋች አገራዊ ኃላፊነት ሰጥተው ሜዳ ማስገባት አስገራሚ ነበር። በርካታ ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች የልጁን ትክክለኛ ችሎታ አልረዳለት ብለው የነበረውን ኡመድ ኡክሪን በተለይ በአንድ ወቅት አቶ ሰውነት ቢሻው ጎል አላገባልኝ ካለ ፍርድ ቤት አልከሰው ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል እንደገና እንዲጎመራ ማድረጋቸው፣ ዋሊድ አታን እና የሱፍ ሳላን መጠቀማቸው በአሁኑ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የታዩ ለውጦች ናቸው ማለት ይቻላል።ነገር ግን ዛሬ ሽንፈት በዝቶባቸዋል ተብለው የሚተቹ ተተኪዎችን አብዝቶ መኮነን ደግሞ ተገቢ ነው ብሎ መቀበል ይከብዳል። 

በኳስ ቁጥጥር የታየ ለውጥ

ምናልባት በአሁኑ ብሔራዊ ቡድንና ከሁለት ዓመታት በፊት በነበረው ብሔራዊ ቡድን መካከል የታየው ትልቁ ለውጥ የአሁኑ ብሔራዊ ቡድን በኳስ ቁጥጥር ሜዳ ላይ ሲበለጥ ማየታችን ነው። ቡድኑ አዲስ አበባ ላይ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በአካል እንዲሁም ከአገር ውጭ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ደግሞ በተንቀሳቃሽ ምስል በቴሌቪዥን የመመልከት እድል ያገኘን የስፖርቱ ተከታታዮች በሙሉ የሚያስማማን ነጥብ ቢኖር የማሪያኖ ባሬቶ ስብስብ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ሲወሰድበት ማየት ችለናል። 

ሁለት የተከላካይ አማካይ ተጫዋቾችን አስራት መገርሳና አዲስ ህንጻ እየተጠቀሙ ተብለው ሲተቹ የነበረው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚያሰለጥኑት ቡድን በተጋጣሚ ቡድን በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ሲወሰድበት አይታይም ነበር። ባይሆን የቀድሞው ቡድን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ዳገት ይሆንበት ነበር እንጅ። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም የአፍሪካ ዋንጫን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያና በቻን ዋንጫ ባደረጋቸው አስር ጨዋታዎች በማጣሪያው አራት በአፍሪካ ዋንጫ ሶስት እንዲሁም በቻን ሶስት ሰባት ግብ ብቻ አስቆጥሮ 17 ግብ የተቆጠረበት። የአሁኑ ቡድን ግን የኳስ ቁጥጥሩ ደካማ መሆኑ በግልጽ ታይቷል። ያም ሆኖ ግን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ በመድረስ በኩል የተሻለ ነው ብሎ መናገር ያስደፍራል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በአምስት ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው ሰባት ግቦችና ለመቁጠር የሚያዳክቱ ያመከናቸው የግብ እድሎች ናቸው። 

እንደ ማጠቃለያ፦ የኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም አንባቢያን በዚህ ሃሳብ ዙሪያ መወያየት ከፈለጉ ድረ ገጹ በሩን ከፍቶ የሚጠብቃችሁ መሆኑንና የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ይርጋ አበበም ገንቢ በሆኑ ሃሳቦች ዙሪያ ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለሁ። 

መልካም ጊዜ ለእግር ኳሳችን። 

ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል
ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
kassaw [1193 days ago.]
 whatever u say our coach mariano is not good for as,he said that he gives chance for youngsters,but cannot play as former players like adane,asrat,minyah....so what is the advantage of this.he is playing for pont,for afcon not for friendly! I am ashamed of by this team,I will never see Ethiopian game unless mariano out.stupid and coach!!

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!