ኢኳቶሪያል ጊኒ የመጨረሻዎቹን ሰባት እንግዶቿን ዛሬ ታውቃለች
ህዳር 10, 2007

ኢኳቶሪያል ጊኒ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን የልብ ምት ያስተካከለች ትንሽ አገር ነች። አገሪቷ ምንም እንኳ በህዝብ ብዛትና በቆዳ ስፋት ከአህጉሩ “ትንሽ” የሚያስብላት ቢሆንም ካፍ ግን ይህችን አገር ትንሽ የሚልበትን አይወድም። ምክንያቱ ደግሞ ትንሽ የተባለችዋ አገር ለካፍ ትልቅ ውለታ ውላለችና ነው አስተናጋጅ አጥቶ አየር ላይ ሊቀር የነበረውን የአህጉሪቱን ትልቁን የእግር ኳስ ውድድር ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሚጢጢ አገር ነች ከአየር ላይ አውርዳ መሰረቱን መሬት ላይ እንዲያሳርፍ ያደረገችው። ታዲያ ካፍ ይህችን አገር ባያከብራት ይደንቃል?

አገሪቷ በምድብ ማጣሪያው መግባት ያልቻለች ቢሆንም ሞሮኮ የገፋችውን አስተናጋጅነት እሷ ለማዘጋጀት ፈቃደኛ በመሆኗ ካፍ እንደ ስጦታ የውድድሩ ተካፋይ እንድትሆን አድርጓታል። በዚህም የተሳትፎ እድሏ በሩ ከተዘጋ በኋላ የካፍ ግብዣ በውድድሩ መሳተፏን ከአልጄሪያ ቀጥላ ያወቀች ሁለተኛዋ አገር ሆናለች። ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረገው የምድብ ማጣሪያ አምስተኛ ጨዋታ ባሳለፍናቸው እሁድና ቅዳሜ ምሽት ሲካሄድ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከአልጄሪያ በተጨማሪ ሰባት አገሮች የእሷ የክብር እንግዶች መሆናቸውን አውቃለች።  

በምድብ አንድ የ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅ ደቡብ አፍሪካ የውድድሩ አሸናፊ የነበረችውን ናይጄሪያን ቀድማ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ የምትጓዝ አገር ሆናለች። ባፋና ባፋና ሱዳንን ሁለት ለአንድ አሸንፋ በ11 ነጥብ ይዛ የምድቧ የበላይ ሆና ማጠናቀቋን ስታረጋግጥ የ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ናይጄሪያ ከኮንጎ ኪኒሻሳ እኩል ሰባት ነጥብ ይዛ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ሱዳን ግን ሶስት ነጥብ ብቻ ስለያዘች ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመሄድ ፍላጎት እንጅ እድል የላትም። 

ዋሊያዎቹ ያሉበትን ምድብ የሰሜን አፍሪካዊቷ አልጄሪያ በ15 ነጥብ ማለፏን ያረጋገጠች ሲሆን ማሊና ማላዊ እኩል ስድስት ነጥብ ይዘው የአልጄሪያን እግር ተከትለው ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ለመሄድ አቆብቁበዋል። በአሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ አልጄሪያ ማሊን በሰፊ የግብ ልዩነት ካሸነፈለት እና እሱ ራሱ ደግሞ ማላዊይን ሶስት ለባዶና ከዚያ በላይ በሆነ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ከቻለ ኢቦላ ሳያሰጋው ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ኢኳቶሪያል ጊኒ ይጓዛል ማለት ነው። ለጊዜው ግን ከዚህ ምድብ ማለፉን ያረጋገጠው የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ብቻ ነው።  

ምድብ ሶስትን ሁለቱ ምዕራብ አፍሪካውያን ቡርኪናፋሶና ጋቦን ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። የ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ የነበረው ቡርኪናፋሶ አስር ነጥብ ሲይዝ ተከታዩ ጋቦን ደግሞ ዘጠኝ ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል። ተከታዮቻቸው አንጎላና ሌሴቶ ግን አምስትና ሁለት ነጥብ እንደቅደም ተከተላቸው የያዙ በመሆኑ አለማለፋቸውን በጊዜ አውቀው ተቀምጠዋል። ዛሬ ምሽት የሚያደርጉትን ጨዋታም ለመርሃ ግብሩ ማሟያ እንጅ የነጥቡ አስፈላጊነት እምብዛም ነው። 

አራት ምዕራብ አፍሪካውያን አገሮች ያሉበትን ምድብ አራትን ካሜሩን የበላይ ሆና የሚያስጨርሳትን ነጥብ በመሰብሰቧ ከአይቮሪኮስት ቀድማ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ማለፏን አረጋግጣለች። የእነ ያያ ቱሬ አገር አይቮሪኮስት ስድስት ነጥብ ይዛ ከዴሞክራቲክ ሪፐብለሊክ ኮንጎና ኢቦላ እያሰቃያት ካለችው ሴራሊዮን የተሻለ እድል ስላላት የጎረቤቷን ድግስ የመካፈል እድል አላት። ምድቡን ካሜሩን በ13 ነጥብ ስትመራ አይቮሪኮስት በዘጠኝ ትከተላለች አንድ ነጥብ ብቻ የያዘችው ሴራሊዮን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአምስት ነጥብ ተበልጣ አራተኛ ደረጃን ማንም እንደማይቀማት አረጋግጣለች።  

ከምድብ አምስት አገሮች መካከል አንዳቸውም  የ30ኛው አፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆናቸውን አላረጋገጡም። የአፍሪካ ዋንጫን አራት ጊዜ ማንሳት የቻለችው የእነ አብዲ ፔሌዋ አገር ጋና ከምሥራቅ አፍሪካዊቷ ዩጋንዳ በአንድ ነጥብ ልቃ ስምንት ነጥብ ሸምታ አንደኛ ስትሆን፤ በኢማኑኤል አዲባየር አምበልነት የምትመራው ቶጎ ደግሞ ስድስት ነጥብ ይዛ ከጊኒ በሁለት ነጥብ በልጣ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። በቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ የምትሰለጥነው ዩጋንዳ ከዛሬው ጨዋታ አንድ ነጥብ ማግኘት ከቻለች ከኢኳቶሪያል ጊኒ ድግስ ተቋዳሽ መሆን ትችላለች። 

የደቡባዊ አፍሪካ አገራት በብዛት በተመደቡበት ምድብ ስድስትን ኬፕ ቨርዴ በአስደናቂ አጨራረስ 12 ነጥብ ሰብስባ አንደኛ ሆና ማለፏን አረጋግጣለች። በ2013 ተካሂዶ በነበረው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እና ለብራዚሉ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በተደረገው የምድብ ማጣሪያ አስደናቂ ብቃት ያሳየችው ትንሿ አገር ኬፕ ቨርዴ በእግር ኳስ ግን ታላቅ እየሆነች መጥታለች። የ28ኛው አፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋን ዛምቢያን፣ ሞዛምቢክንና ኒጀርን አስከትላ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ የሚወስዳትን አውሮፕላን ትኬት መቁረጥ ችላለች። ከኬፕ ቨርዴ ቀጥሎ ለማለፍ በሚደረገው ፉክክር  ስምንት ነጥብ ያላት ዛምቢያ የተሻለ እድል ሲኖራት አምስት ነጥብ የያዘችው ሞዛምቢክም ቢሆን ተስፋዋ አልተሟጠጠም። ኒጀር ግን ሁለት ነጥብ ብቻ ስለያዘች የያዘችው ነጥብ የትም ስለማያደርሳት የአፍሪካ ዋንጫን የምትከታተለው በቴሌቪዥን ብቻ ይሆናል ማለት ነው።  

የአፍሪካ ዋንጫን ለሰባት ጊዜ በማንሳት ተወዳዳሪ የሌላት አገር ነች ግብጽ። ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን የግብጽ እግር ኳስ ታላቅነቱ ክዶት ወደታች መንሸራተቱን ተያይዞታል። ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከጎረቤቷ ቱኒዚያ፣ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሴኔጋልና ከደቡባዊ አፍሪካዊቷ ቦትስዋና ጋር ተደልድላ የነበረችው ግብጽ ከመሪዋ ቱኒዚያ በአምስት እንዲሁም ሁለተኛ ሆና ማለፏን ካረጋገጠችው ሴኔጋል ደግሞ በአራት ነጥብ ዝቅ ብላ ስድስት ነጥብ ብቻ ይዛ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ግብጽ ከምድቧ የምትበልጠው አንድ ነጥብ የያዘችውን ቦትስዋናን ብቻ ነው። ግብጽ በውድድሩ ለመሳተፍ ያላት ብቸኛ ተስፋ ዛሬ ካሸነፈች ምርጥ ሶስተኛ ሆና ማለፍ ይሆናል።

የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ የአህጉሪቱ ከተሞች የሚካሄዱ ሲሆን አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ ከማላዊ እንዲሁም ባማኮ ላይ ማሊ ከአልጄሪያ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይገኙበታል። አዲስ አበባ ላይ የሚካሄደው የኢትዮጵያና የማላዊ ጨዋታ ዋሊያዎቹን ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ የሚወስድ ውጤት ካላስመዘገቡ እና ግብጽ ምርጥ ሶስተኛ ሆና ማለፍ ካልቻለች የአፍሪካ ዋንጫን የመሰረቱት ሶስቱም አገሮች ግብጽ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ያልተሳተፉበት የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ይሆናል ማለት ነው። በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ግብጽና ሱዳን ማጣሪያውን ባለማለፋቸው ከመስራቾቹ ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች ብቸኛዋ ተሳታፊ።  ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Israel [1189 days ago.]
 Www.ethiofootball.com

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!