በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተወካይ የሌለው ምሥራቅ አፍሪካ
ህዳር 11, 2007

ምሥራቅ አፍሪካ ክፍለ አህጉር እንደ ጠርሙስ የተሰባበረችውን ሶማሊያንና ለሁለት የተከፈለችውን ሱዳንን ጨምሮ በድምሩ 12 አገራትን ይዟል። አህጉረ አፍሪካ ደግሞ በአጠቃላይ 55 አገሮችን የያዘ ሲሆን ምሥራቅ አፍሪካ የአህጉሩን 22 በመቶ የሚሸፍን ክፍለ አህጉር ነው። የአህጉሩን 22 በመቶ የሚሸፍን አገሮችን መያዝ የቻለው ምሥራቅ አፍሪካ ግን በእግር ኳሱ ለአህጉሩ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።  የፊታችን የካቲት ትንሿ አገር ኢኳቶሪያል ጊኒ በምታስተናግደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ አገሮች ተጠቃልለው የታወቁ ሲሆን በኢኳቶሪያል ጊኒ ሰማይ ስር በሚካሄደው ውድድር ከሚሳተፉ አገሮች መካከል አንድም የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ የለም። 

ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በተደረገው የምድብ ማጣሪያ ውድድር 28 አገሮች በሰባት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ሲያደርጉ በምድብ ማጣሪያው መካፈል የቻሉት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነሱም ኢትዮጵያና ዩጋንዳ ብቻ ነበሩ። ዩጋንዳ በምድብ አምስት ከጠንካራዎቹ ጋና፣ ጊኒ እና ቶጎ ጋር ተደልድላ የነበረ ቢሆንም እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመጓዝ እድሏ በእጇ ላይ ነበር። ነገር ግን በምድቧ የመጨረሻ ጨዋታ ጊኒ ቢሳው ላይ በጊኒ ተሸንፋ በውድድሩ የመካፈል እድሏን አጣች። ዩጋንዳን ያሸነፈችው ጊኒም 11 ነጥብ ይዛ አንደኛ ሆና ያለፈችውን ጋናን ተከትላ በሰባት ነጥብ ሁለተኛ ሆና በማለፍ የ30ኛው አፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆን ችላለች።
 
የዋሊያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በታሪኩ ለዘጠኝ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ ችሏል። ከእነዚህ ተሳትፎዎቹ ውስጥ ሶስቱን ማለትም ሶስተኛን ስድስተኛውንና አስረኛውን በአዘጋጅነቱ ያገኛቸው ሲሆን ሁለቱን አንደኛaWንNነና ሁለተኛውን ደግሞ ያለማጣሪያ በቀጥታ በማለፉ ያሳካቸው ናቸው። ቀሪዎቹን አራት የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዎቹን ያገኘው ደግሞ የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን አካሂዶ ነው። ይህ የሚያሳየው ብሔራዊ ቡድኑ አንድም ጊዜ የማጣሪያ ጨዋታ አድርጎ ከምድቡ አልፎ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ አድርጎ የማያውቅ መሆኑን ነው። ስለ ብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ይህን ያህል ካልን ስለዘንድሮው የማጣሪያ ጨዋታዎቹ ጉዞ በተለይም ስለትናንት ምሽቱ ጨዋታ የሚከተለውን እንይ።  

በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የነበረው ብሔራዊ ቡድን በ30ኛው ውድድር ለመሳተፍ የግድ በምድብ ማጣሪያው የሚገጥሙትን ቡድኖች እየገነደሰ መሄድ ነበረበት ወይም እሱን እየገነደሱ ሌሎች ሊራመዱት ግድ ነበር። በዚህም መሰረት የወቅቱ የአህጉሩ ቁጥር አንድ የእግር ኳስ አገር አልጄሪያና የ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚዋ ማሊ ከዋሊያዎቹ ጋር መደልደላቸውን ቀድመው ሲያውቁ የደቡባዊ አፍሪካ አገሯ ማላዊ ደግሞ ቤኒንን በደርሶ መልስ አሸንፋ ከዋሊያዎቹ ጋር ለመጋጠም የተመደበች ሶስተኛዋ አገር ሆና ተዘጋጀች። ዋሊያዎቹ ከሁለት ዓመት በፊት በደርሶ መልስ ሱዳንን ከመግጠማቸው በፊት ቤኒንን አሸንፈው ማለፋቸው ይታወሳል 

በካፍ የምድብ ድልድል መሰረት ዋሊያዎቹ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸው አልጄሪያን በሜዳቸው አስተናግደው ሙሉ ሶስት ነጥብ አሳቅፈው ሲሸኙ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ደግሞ ወደ ማላዊ ተጉዘው ለማላዊ ሶስት ነጥብና ሶስት ግብ ሰጥተው ተመለሱ። ሶስተኛውን የምድባቸው ጨዋታም ሶስት ነጥብ ማግኘት እንዳማራቸው አሁንም ለማሊ እጃቸውን ሰጡ። በሶስት ተከታታይ ጨዋታ ያለምንም ነጥብ በምድቡ የደረጃውን ግርጌ የተቆናጠጡት ምሥራቅ አፍሪካውያኑ በምድባቸው አራተኛ ጨዋታ ግን በርካታ የስፖርት አፍቃሪያንን ባስገረመ መልኩ ባማኮ ላይ ማሊን አሸንፈው ተመለሱ። ይህ ደስታቸው ግን ከቀበሮ ደስታነት መዝለል አልቻለም ነበር በምድባቸው አምስተኛ ጨዋታ በአልጄሪያ ተሸንፈው አሁንም የደረጃውን ግርጌ መልሰው ተቆጣጠሩት።  

 የዋሊያዎቹ የመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ 

አልጄሪያ አምስቱንም የምድቧን ጨዋታዎች አሸንፋ በ15 ነጥብ አንደኛ ሆና ማለፏን ስታረጋግጥ ማሊና ማላዊ ደግሞ እኩል ስድስት ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ዋሊያዎቹን ከላይ ሆነው እየመሩ ነበር የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ የተካሄደው። የኢትዮጵያ የማለፍ ተስፋ ማሊ ተሸንፋ ኢትዮጵያ ደግሞ በሶስት ግብ ልዩነት ማላዊይን ማሸነፍ ከቻለች ብቻ ነበር። ነገር ግን ማሊም አልተሸነፈች ማላዊይም በዋሊያዎቹ አልተሸነፉ። ዋሊያዎቹም ከ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውጭ መሆናቸውን አወቁ።  

አዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ በሩን ከፍቶ የዘወትር የስታዲየም አድማቂዎቹን የዋሊያዎቹን ደጋፊዎች መጠባበቅ ጀመረ። ለወትሮው በተመልካች እገባለሁ በፖሊስ አትገባም ቆይ በሩ ይከፈት ቲኬት ቆራጮቹ ይምጡ ውዝግብ ይታወቅ የነበረው ካምቦሎጆ ትናንትና ግን እስከ ምሽቱ 12፡30 ድረስ በተመልካች አልሞላም ነበር። እንደ ሰንበቴ ማህበርተኛ የስታዲየም ታዳሚዎችም አንድ ሁለት እያሉ እየተንጠባጠቡ ቀስ በቀስ ስታዲየሙን ከአፍ እስከ ገደፉ መሙላት የቻሉት ጨዋታው ሊጀመር ትንሽ ደቂቃዎች ከቀሩት በኋላ ነው።   

ጨዋታው ተጀመረ 

አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ሁለቱን ወሳኝ አጥቂዎቻቸውን ሳላሃዲን ሰይድንና ጌታነህ ከበደን በጉዳትና በቅጣት እንዲሁም ተከላካዩን ዋሊድ አታን በሁለት ቢጫ ካርድ የተነሳ ማሰለፍ ስላልቻሉ በትናንቱ ጨዋታ መጠነኛ የአሰላለፍ ለውጥ አድርገው ነበር ልጆቻቸውን ወደ ሜዳ ያስገቧቸው። “ለዝግጅት ወደ ብራዚል ስጓዝ ይዤው ባለመሄዴ ይቆጨኛል” ብለው ችሎታውን የመሰከሩለትን የሲዳማ ቡናውን አብዱልከሪም መሃመድን በቀኝ ተመላላሽ መስመር ሲያሰልፉ በዚያ ቦታ ቀደም ብሎ ይሰለፍ የነበረውና ለስህተት በእጅጉ ቅርብ ነው እየተባለ የሚታማውን ቢያድግልኝ ኤሊያስን ደግሞ የመሃል ተከላካይ አድርገው ከሳላሃዲን ባርጌቾ ጋር አሰልፈውታል። የመሃል ሜዳውን ወጣቱ ናትናኤል ዘለቀ ልምድ ካላቸው ታደለ መንገሻና ሽመልስ በቀለ ጋር እንዲዋሃዱ ሲያደርጉ የፊት መስመራቸውን ደግሞ በኡመድ ኡክሪና የሱፍ ሳላ ፊት ለፊት ዳዊት ፈቃዱን አሰልፈው ነበር የገቡት። 4 3 3 አሰላለፍ  
በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል አልፎ አልፎ ሙከራ ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ የቻለው ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነበር በአጥቂው ኡመድ ኡክሪ አማካኝነት። ኡመድ ከ18 ክልል ውጭ አክርሮ ወደ ግብ የላካትን ኳስ የማላዊው ግብ ጠባቂ ማክዶናልድ ሃባዋ ጨርፎ ከግቡ ቋሚ ጋር እንድትጋጭ በማድረጉ የኳሷን ማረፊያ መረብ ላይ እንዳይሆን አድርጓል። ከዚህች ሙከራ በኋላ ብዙም ለግብ ጠባቂ ፈታኝ የሆነ ሙከራ በሁለቱም በኩል አልታየም ነበር ዳዊት ፈቃዱ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መጠናቀቂያ አካባቢ እሰከሞከረበት ደቂቃ ድረስ።  

Ethiopia Vs Malawi


በማላዊ በኩል ተጫዋቾቹ ከአዲስ አበባ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ባዶ እጃቸውን ላለመሄድ ይመስላል ለሁለቱም ቡድኖች የማይበጀውን ነጥብ ተጋርቶ መውጣት  ሰዓት ማባከን ሲጠቀሙ ታይተዋል። በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ሁለት ጊዜ ብቻ ወደ ዋሊያዎቹ የግብ ክልል ኳሶችን የላኩ ሲሆን አንዷ ሙከራም የተገኘችው ጀማል ጣሰው በሰራው ስሀተት ነው። 

ባማኮ ላይ እየተካሄደ የነበረው የማሊና የአልጄሪያ ጨዋታ በማሊ አንድ ለባዶ መሪነት ለእረፍት መውጣታቸውን መረጃው ስለደረሳቸው ነው መሰል በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች ለማሸነፍ ፍላጎት ሳያሳዩ በመሃል ሜዳ የተወሰነ እንቅስቃሴ ብቻ ሲያደርጉ ታይተዋል። አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶም ወደ አፍሪካ ዋንጫው ባይጓዙም ሜዳቸው ላይ ሙሉ ሶስት ነጥብ ለማግኘት በመፈለጋቸው በእለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ ያላመሹትን የሱፍ ሳላን በ63ኛው ደቂቃ እና ዳዊት ፈቃዱን በ70ኛው ደቂቃ አስወጥተው እንዳለ ከበደንና ራምኬል ሎክን በማስገባት ውጤት ለማግኘት ሙከራ አድርገው ነበር አልተሳካላቸውም እንጅ። ዋሊያዎቹ ከምድባቸው አለማለፋቸው ደግሞ ክፍለአህጉሩን ኢኳቶሪራል ጊኒ ላይ የሚወክለው አገር እንዳይኖር አድርጎታል። በጨዋታው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀኝ መስመር ተሰልፎ የተጫወተው አብዱልከሪም መሃመድ ከተመልካች አድናቆት የተቸረው ሲሆን በእለቱ የተመዘገበውን ብቸኛ የቢጫ ካርድ ደግሞ ሽመልስ በቀለ ተመልክቷል። አልጄሪያና ማሊ በ15 እና ዘጠኝ ነጥብ ተከታትለው ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያስገባቸውን ውጤት ሲያገኙ ማላዊ በሰባት እንዲሁ ኢትዮጵያ በአራት ነጥብ ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘው የማጣሪያ ጨዋታቸውን አጠናቅቀዋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአኃዝ
የማዕዘን ምትኢትዮጵያ አምስት ማላዊ አንድ
ቅጣት ምትኢትዮጵያ 15 ማላዊ 12
የግብ ሙከራ.ኢትዮጵያ ሰባት ማላዊ አራት
ከጨዋታ ውጭ offside .ኢትዮጵያ ሁለት ማላዊ ስድስት
ቢጫ ካርድኢትዮጵያ አንድ ማላዊ አንድ
ቀይ ካርድ…በሁለቱም በኩል አልተመዘገበም።  

ዘጋቢ፦ ይርጋ አበበ 
ኢትዮ ፉትቦልethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
DAN ADANE [385 days ago.]
 እጂግ በጣም ጥሩ ነዉ

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!