የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነገና እሁድ በተለያዩ ከተሞች ቀጥሎ ይውላል
ህዳር 19, 2007- "ጎንደር ላይ ያገኘነውን ሙሉ ሶስት ነጥብ አዲስ አበባ ላይ በመድገም ደጋፊዎቻችንን ልናስደስት  ተዘጋጅተናል።" አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ

- “የዳኞች የተዛባ ውሳኔ ክለባችንን እየጎዳው ነው። አዳማ ላይ ሙሉ ሶስት ነጥብ እንዳንወስድ ያደረገን አለአግባብ የተጨመረብን ስድስት ደቂቃ ነው” አሰለጣኝ ታረቀኝ አሰፋ

በአምስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነገ ሃዋሳ ላይ ባለሜዳው ሃዋሳ ከነማ አዲሱን የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ወልድያን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ያስተናግዳል። ሁለቱም ክለቦች በውድድር ዓመቱ መክፈቻ እለት ጀምሮ ያካሄዷቸውን ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻሉ ሲሆን የነገውን ጨዋታ በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። 

“የዳኞች የተዛባ ውሳኔ ክለባችንን እየጎዳው ነው” የሚሉት የሃዋሳ ከነማው አሰለጣኝ አቶ ታረቀኝ አሰፋ አዳማ ላይ ሙሉ ሶስት ነጥብ እንዳንወስድ ያደረገን አለአግባብ የተጨመረብን ስድስት ደቂቃ ነው ሲሉ ለኢትዮፉትቦል ዶት ኮም ገልጸዋል። አሰልጣኙ አያይዘውም ለአገሪቱ እግር ኳስ እድገት የዳኞች ፍትሃዊነት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የዳኞች ኮሚቴ ጉዳዩን በጥልቀት እንዲመለከተው አስገንዝበዋል። ነገ በሜዳቸው የሚያደርጉትን ጨዋታም ለማሸነፍ ዝግጅት ማድረጋቸውን ጨምረው ገልጸዋል። 

ከሜዳው ውጭ ያደረጋቸውን ሁለቱንም ጨዋታዎች የተሸነፈውና በሜዳው ሲጫዎት ደግሞ አቻ የሚለያየው ወልድያ በበኩሉ ያለፈ መጥፎ ሪከርዱን ለመቀየር መዘጋጀቱን ለክለቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል። 

አዲስ አበባ ላይ መከላከያ ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ደደበት ጋር ከቀኑ አስር ሰዓት የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ ጨዋታ ነው። መከላከያ በዚህ ዓመት ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች አንዱንም ያልተሸነፈ ሲሆን አንዱን አሸንፎ ሶስቱን በአቻ ውጤት በመለያየት ስድስት ነጥብ ይዞ ከመሪው ደደቢት በሶስት ነጥብ ዝቅ ብሎ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ደደቢት በበኩሉ ሶስትንም የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎቹን በማሸነፉ ፕሪሚየር ሊጉን አናት ላይ ሆኖ እየመራው ሲሆን አጥቂው ሳሙኤል ሳኖሜ ደግሞ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር የግብ ጠባቂዎች ስጋት መሆኑን እያሳየ ይገኛል። 

ፕሪሚየር ሊጉ እሁድም ቀጥሎ የሚውል ሲሆን ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ያስተናግዳል። ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሲጫዎት በቀላሉ ይሸነፍ የነበረው ሲዳማ ቡና ዘንድሮ ግን ጠንካራ አጀማመር እያሳየ የሚገኝ በመሆኑ በእሁዱ ጨዋታ በቀላሉ እጁን ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም። 

የፕሪሚየር ሊጉ ግርጌ ላይ ተረጋግቶ የተኛው ወላይታ ድቻ በበኩሉ ቦዲቲ ላይ አዳማ ከነማን ያስተናግዳል። የመሳይ ተፈራ ቡድን ወላይታ ድቻ ባለፈው ሳምንት በጥቃቅን ስህተቶች በደደቢት መሸነፉ ዋጋ ያስከፈለው በመሆኑ ከአዳማ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በጥንቃቄ እንደሚያካሂድ ይጠበቃል። ሙገር ሲሚንቶ አሰላ ላይ መብራት ኃይልን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ሌላው ክልል ላይ የሚካሄድ የሳምንቱ መርሃ ግብር ነው። ሁለቱም ቡድኖች በዚህ ዓመት ያልተሸነፉ በመሆናቸው ጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር የሚካሄድበት እንደሚሆን ይገመታል። 
በአሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንከ አዲስ አበባ ላይ ዳሽን ቢራን ያስተናግዳል። በተደጋጋሚ ጊዜ የዳኛ በደል ደረሰብኝ እያለ ቅሬታውን ሲያሰማ የቆየው ዳሽን ቢራ በአራት የፕሪሚር ሊግ ጨዋታዎቹ አንዱን አሸንፎ በሶስቱ ተሸንፎ ዘጠንኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባንክ በበኩሉ አንድ አሸንፎ ሶስት አቻ ወጥቶ በስድስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ጨዋታው የሚካሄደው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ነው። 

ሌላው የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ ቡና አርባምንጭ ከነማን የሚያስተነግድበት ጨዋታ ነው። ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎቹን ተሸንፎ ወቀሳ በዝቶበት የቆየው የጥላሁን መንገሻ ቡድን ባለፈው ማክሰኞ ዳሽን ቢራን አሸንፎ ሙሉ ሶስት ነጥብ በማግኘቱ መነቃቃት እያሳየ ይገኛል። ባለፉት ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎቹ ሶስት ተጫዋቾቹን በቀይ ካርድ ያጣው ኢትዮጵያ ቡና በእሁዱ ጨዋታ የተወሰነ የአሰላለፍ ለውጥ አድርጎ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። 
ጎንደር ላይ ቀምሶ ያጣጣመውን ሙሉ ሶስት ነጥብ አዲስ አበባ ላይ በመድገምም ደጋፊዎቹን እንደሚያስፈነድቅ መዘጋጀቱን አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ ለኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም በስልክ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ቡና እና የአርባ ምንጭ ከነማ ጨዋታ ከቀኑ 11 ሰዓት የሚካሄድ ይሆናል። 

ደደቢት በዘጠኝ ነጥብና በስምንት ተጨማሪ የግብ ክፍያ ፕሪሚየር ሊጉን ሲመራ ሲዳማ ቡና በስምንት ነጥብ ሁለተኛ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መከላከያ ተመሳሳይ ስድስት ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ላይ ተቀምጠዋል። ያለፈው ዓመት ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሙገር ሲሚንቶ ጋር ተመሳሳይ አምስት ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ተበልጦ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ኢትዮጵያ ቡና በሶስት ነጥብ አስረኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከፍተኛ ግብ አግቢነቱን የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሜ በስድስት ግቦች ይመራል።ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
እድል መኩሪያ [1146 days ago.]
 የቀጥታ ጨዋታ መዘገብ መጀመራችሁ አሪፍ ነው, ቶሎ ቶሎ የክፍለ ሀገር ጨዋቶችን, ሰንጠረዦችን, በወቅቱ update ብታደርጉ ደግሞ ገፃቹ ይበልጥ አሪፍ ይሆናል።

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!