ቡና ደጋፊዎቹን ሲያስደስት ንግድ ባንክ በዳሽን ነጥብ ጥሏል
ህዳር 21, 2007


ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም  በተከናወኑት የፕሪሚየር ሊጉ አምስተኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ንግድ ባንክ በሜዳው ባልተጠበቀ ሁኔታ በዳሽን 1ለ0 ተሸንፎ ሲወጣ ኢትዮጵያ ቡና አርባ ምንጭን 3ለ1 አሸንፏል።


CBE vs Dashen

 በዛሬው ጨዋታ ብዙም ጥሩ ያልነበሩት ንግድ ባንኮች በእንግዳው ዳሽን የኳስ ቁጥጥር ተበልጠው ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ  ባዶ ለባዶ ካለቀ በኋላ  ንግድ ባንኮች ከረፍት መልስ ተጭነው ይጫወታሉ ተብሎ ሲጠበቅ ከመጀመሪያው አጋማሽ ምንም የተሻለ ለውጥ ሳያሳዩ በዳሽኖች አልፎ አልፎ ለሚደረግ ጥቃት እራሳቸውን ሲያጋልጡ ከቆዩ በኋላ ዳሽኖች በቀኝ ጥላፎቅ በአንድ ሁለት ቅብብል በ60ኛው ደቂቃ ላይ ያሳለፉትን ኳስ  10 ቁጥሩ ምንተሻው ተቀብሎ ወደጐል  ለማሻማት የላካት ኳስ በረኛውን ከፊት አስቀርታ ድንገተኛ ጐል ለመሆን በቃች። በገባባቸው ጐል የተደናገጡት ንግድ ባንኮች ጨዋታውን ለመቀየር የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ጫላ ድሪባንና አልሳዲክ አልማኒን ወደ ሜዳ አስገቡ።  በ70ኛው ደቂቃ ፊሊፕስ ዳውዝ በካታንጋ ቀኝ ክንፍ ሁለት ተከላካዮችን ተጋፍቶ ወደመሃል ያሻማውን ኳስ  ኤፍሬም አሻሞ ብቻውን ተረጋግቶ ቢያገኛትም ወደ ጐል  መቀየር ተስኖት ኳሷን የበረኛ ሲሳይ አድርጓታል። ጨዋታው እየተሟሟቀ በመጣበት በ73ኛው ደቂቃ ላይ ዳሽኖች ከመሃል ጥሩ ቅብብል አድርገው ከመሃል በቀጥታ ወደ ጐል የመቷት ድንቅ ኳስ ጐል ከመሆን የዳነችው የባንኩ በረኛ አብይ ታደሰ በአስደናቂ ሁኔታ ተወርውሮ ጨርፎ ስላወጣት ነበር።ለጐል ሙከራውና ኳሱን ተወርውሮ ላወጣው አብይ ተመልካቹ በጭብጨባ አድናቆቱን ለግሷል።

Dashen 1-0 cbe


 ጨዋታው በዳሽን 1ለ0  አሸናፊነት ከመጠናቀቁ በፊት በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ተጭነው ቢጫወቱም አቻ ሊያደርጋቸው የሚችሉበትን አጋጣሚ በ91ኛው ደቂቃ ላይ አምልጧቸዋል። የዳሽን ተከላካይ ኳስ አወጣለሁ  ሲል የመታው ኳስ በራሱ መረብ ላይ እንዳያርፍ የገደበው አንግሉ ብቻ ነበር።

CBE 0-1 Dashen


በሁለተኛው ጨዋታ የተገናኙት ኢትዮጵያ ቡናና አርባምንጭ ከነማ ነበሩ። ጨዋታው ፊሽካ የበዛበት ከመሆኑ በስተቀር በሁለቱም በኩል በርካታ የግብ ሙከራ የተደረገበት፥ ሁለቱም ቡድኖች ለመሸናነፍ አጥቅተው የተጫወቱበት ጨዋታ ነበር። 
Coffee vs arbaminch


በደጋፊዎቻቸው ዝማሬ እየታገዙ የኳስ የበላይነቱን  ተራ በተራ እየተነጣጠቁ ሲጫወቱ ካመሹት ሁለቱ ቡድኖች የጐል ማግባቱን ቀዳሚነት የያዙት አርባ ምንጮች ነበሩ። በ6ኘው ደቂቃ ላይ በረከት ደሙ በአየር ያገኘውን ኳስ በግንባር በመግጨት የመጀመሪያውን  ጐል ለአርባ ምንጭ አስቆጠረ። ቡናዎች በ18ኛው ደቂቃ ቢኒያም አሰፋ አቻ የምታደርጋቸውን ጐል   ከማስቆጠሩ በፊት ተረጋግተው ለመጫወት ተስኗቸው ነበር።  

Coffee vs arbaminch

ቡናዎች የበላይነቱን በያዙባቸው  በ20ዎቹ መጨረሻና በ30ዎቹ መጀመሪያ ደቂቃዎች ጐል ሊሆን የሚችል ኳሶችን አግኝተው ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል በ27ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ አንግል ሲገጭባቸው፣ በ30ኛውና  በ35ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን  ጥሩ ጥሩ ኳሶች አልተጠቀሙባቸውም፥ በተለይ በ35ኛው ደቂቃ ላይ አንዳርጋቸው ብቻውን ቦታ ይዞ ይጠብቀው ለነበረው  ቢኒያም አሰፋ ኳስ መስጠቱን ትቶ እራሱ ሞክሮ የሳተው ኳስ ለቡናዎች ከረፍት በፊት  ጨዋታውን መርተው እረፍት ሊያስወጣቸው የሚችል ምቹ አጋጣሚ ነበሩ። የመጀመሪያው አጋማሽ 1ለ1 ከማለቁ በፊት አርባ ምንጮች በ43ኛው ደቂቃ ላይ በበረከት ደሙ አማካኝነት ጐል ለማግባት ያደረጉት ጥረት በአዲሱ ናይጄሪያዊ  የቡና በረኛ ሮጦ ወጥቶ በሸርታቴ ሊያከሽፍ ችሏል። 

ከረፍት መልስ የነበረው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የበለጠ ጥሩ ፉክክር የታየበት ነበር። ኳስ ባበደችበት በመጀመሪያዎቹ የሁለተኛ አጋማሽ አስር ደቂቃዎች ውስጥ በ52ኛው ደቂቃ ላይ አርባ ምንጮች ግሩም የግብ ሙከራ አድርገው ሳይሳካላቸው ሲቀር በተመሳሳይ ቡናዎች  በ53ኛው ደቂቃ ላይ ለቢኒያም ጥሩ የአየር ኳስ ደርሶት ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከቢኒያም ሙከራ አንድ ደቂቃ  በኋላ  አርባ ምነጮች በድጋሚ ጐል  ሊሆን የሚችል ንጹ ኳስ በ53ኛው ደቂቃ ላይ ሲስቱ ቡናዎች በ54ኛው ደቂቃ ላይ ሳቱ። ጨዋታው ተመልካቹን ቁጭ ብድግ እያሰኘ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ለመሸናነፍ የሚደረገው ፉክክር ተጋግሎ ቀጠለ።  በ74ኛው ደቂቃ ላይ የአርባ ምንጩን በረኛ አቋቋም ቀድሞ ያስተዋለው ቢኒያም አሰፋ በካታንጋ ግራ ክንፍ በኩል የተላከለትን ኳስ በቀጥታ ወደጐል  በመምታት  ለቡድኑና ለራሱ ሁለተኛውን ጐል አስቆጠረ። በዛሬው ጨዋታ ጥሩ አቋም የነበራቸው አርባ ምንጭቸ  አቻ ሊያደርጋቸው የሚያስቸላቸውን ጐል  ለማግባት በፍጹም መረጋጋት ኳስ ይዘው እስከመጨረሻው ቢጫወቱም ጨዋታው ከመጠናቀቁ በፊት ሶስተኛ ጐል ማግባት የቻሉት ቡናዎች ነበሩ። የቀድሞ የመከላከያ ተጫዋች የነበረው ጥላሁን ወልዴ በመልሶ ማጥቃት መሀል ላይ የገኘውን ኳስ ወደፊት ይዞ በመግፋት አንድ ተጫዋች አታሎ ሌሎች ተከላካዮችን በፍጥነት ሮጦ በማምለጥ ለቡድኑ ሶስተኛውን ግሩም ጐል በ84ኛው ደቂቃ ላይ ማስቆጠር ቻለ። በቀሪዎቹ 8 ደቂቃዎች ውስጥ በሁለቱም ቡድኖች ጐል  ሉሆኑ የሚችሉ ሙከራዎች ቢደረጉም ጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

በተመሳሳይ በክልል በተደረጉ የፕሪሚየር ሊጉ የ5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በሜዳው ሁለት ለባዶ አሸንፏል። ሁለቱን ጐሎች ያስቆጠሩት ባለፈው ሳምንት ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ላይ ከመከላከያ ጋር 1ለ1 በተለያየበት ጨዋታ ጥሩ አቋም ላይ ያልነበሩት በሃይሉ አሰፋና አዳነ ግርማ ናቸው። በሃይሉ ቱሳ በዛሬው ጨዋታ በጉዳት ከሜዳ መውጣቱ ታውቋል። 

ወላይታ ድቻ አዳማ ከነማን በሜዳው አስተናግዶ 3ለ2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ሙገር ሲሚንቶ በተመሳሳይ መብራት ሀይልን በሜዳው አስተናግዶ 3ለ2 በሆነ ውጤት አሸንፏል። 

የፕሪሚየር ሊጉን መሪነት ደደቢት በ4ት ጨዋታና በ9ኝ ነጥብ ሲመራ መከላከያ በ5ት ጨዋታና በ9ኝ ነጥብ ይከተላል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በ4ጨዋታና በ9ኝ ነጥብ ሶስተኛ ቦታን ይዟል።

የኮኮብ ግብ አግቢነቱን ፉክክር የደደቢቱ ሳሙኤለ ሳኑሚ በ6ት ጐል ሲመራ በሁለት ጨዋታ 4ት ጐል ማስቆጠር የቻለው የቡናው ቢኒያም አሰፋ በ4ጐል በሁለተኝነት ይከተላል። በ3ት ጐል ሶስተኛ ቦታን ይዞ ከመሪዎቹ በቅርብ እርቀት እየተፎካከረ  የሚገኘው የንግድ ባንኩ ፊሊፕስ ዳወዝ  ነው።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
mesfin [1178 days ago.]
 EEPCO 3 - 2 Muger epco point 6, rank 5 please update the table and other data.

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!