በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከቦችን በማስመረጥ የክለቦች ሪከርድ
ህዳር 24, 2007

-  በ17 ዓመታት የፕሪሚየር ሊጉ ቆይታም ፈረሰኞቹ አምስት ጊዜ፣ ቡናማዎቹ ሶስት ጊዜ፣ እንዲሁም መብራት ኃይል፣ ደደቢትና ሃዋሳ ከነማ ሁለት ሁለት ጊዜ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋቾችን ማስመረጥ ችለዋል።  

- ዮርዳኖስ አባይ በ1993 ፣ 1994 እና በ1995 ዓ.ም  በተከታታይ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የተመረጠ፥ እስካሁን የኮከብ ግብ አግቢነት ሪከርዱን  በ24ጐል እየመራ ያለ ብቸኛ  ኮከብ ተጫዋች።

- ታፈሰ ተስፋዬ እና ዮርዳኖስ አባይ እያንዳንዳቸው ሶስት ሶስት ጊዜ ኮከብ ግብ አግቢ መሆን ሲችሉ አዳነ ግርማ እና ጌታነህ ከበደ ደግሞ ሁለት ሁለት ጊዜ ኮከብ ግብ አግቢ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው። 


የዛሬውን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ስነሳ የመረጃ ክፍተት ገጥሞኝ ነበር። የኢትዮጵያን እግር ኳስ የሚከታተሉ በርካታ አንባቢያን እንደሚረዱት የአገራችን እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃዎችን በመልክ በመልኩ አዘጋጅቶ ለጸሃፊያንና ለጋዜጠኞች በማቀረብ በኩል ከፍተኛ ክፍተት አለበት። በዚህም ምክንያት በርካቶች በየዓመቱ የሚፈጠሩ ክስተቶችን የማወቅ እድላችን የተገደበ እንዲሆን አድርጎናል። እኔም ይህን መጣጥፍ ሳዘጋጅ የጋዜጠኛ ፈለቀ ደምሴ “የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉዞ” የሚለው መጽሃፍ ትልቅ ግብዓት ሆኖኛል። ለዚህም የመጽሃፉን አዘጋጅ በአንባቢያን ስም አመስግኜ ወደ ዋናው ሃሳቤ ላምራ። 

 ኮከብ አሠልጣኞችን በማስመረጥ 

ፕሪሚየር ሊጉ በ1990 ዓ.ም መካሄድ ሲጀምር ተሳታፊ ከነበሩ ክለቦች መካከል አንዱ መሆን አልቻለም ነበር ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ። ነገር ግን ክለቡ በተደጋጋሚ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማንሳት የሚስተካከለው አላገኘም። ፈረሰኞቹ 11 ጊዜ ፕሪሚየር ሊጉን በማንሳት ቀዳሚ ሲሆኑ ከፈረሰኞቹ  ቀጥሎ ያለውን ደረጃ የያዙት መብራት ኃይልና ሀዋሳ ከነማ ናቸው እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ጊዜ በማንሳት። ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኞችን ደጋግሞ በማስመረጥም ቀዳሚው ክለብ ነው። 

ፕሪሚየር ሊጉ በተጀመረበት የመጀመሪያ የውድድር ዓመት መብራት ኃይል የዋንጫው ባለቤት ሲሆን ክለቡን ያሰለጥን የነበረው ሐጎስ ደስታ ደግሞ የዓመቱ ኮከብ አሠልጣኝ ሆኖ ተመርጧል። በ1991 ዓ.ም ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው ቅዱስ ጊዮርጊስ የዋንጫው ባለቤት ሲሆን አስራት ኃይሌ ደግሞ የዓመቱን ኮከብ አሰልጣኝነት ክብር በመቀዳጀት የመጀመሪያው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሆኗል። በ1992 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በድጋሚ ሲያነሳ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌም በድጋሚ የኮከብነት ዘውዱን መድፋት ቻለ። ከዚህ በኋላ መብራት ኃይል የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለሁለተኛ ጊዜ በአሸናፊነት ሲያጠናቅቅ የክለቡ አሰልጣኝ ጉልላት ፍርዴ ኮከብ አሰልጣኝ መሆን ችለዋል።  

በ1994 እና 1995 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪሚየር ሊጉን ክብር በድጋሚ ከመብራት ኃይል ተቀብሎ የበላይ ሲሆን አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በተከታታይ ለሁለት ዓመታት ኮከብ አሰልጣኝ መሆን ችለዋል። የስዩም ከበደ ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው በተከታታይ መመረጣቸው ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን በስድስት ዓመታት ውስጥ አራት ጊዜ የዋንጫና የኮከብ አሰልጣኝ ባለቤት በመሆን ቀዳሚ አድርጎታል። 
የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ከአዲስ አበባ ከተማ ክለቦች ውጭ እስካሁን ማንሳት የቻለው ሃዋሳ ከነማ ነው። ሃዋሳ ከነማ በ1996 እና በ1999 የፕሪሚየር ሊጉን ክብር ሲቀዳጅ የክለቡ አሰልጣኝ የነበሩት ከማል አህመድ የፕሪሚየር ሊጉ ኮኮብ አሰልጣኝ መሆን ችለዋል። 

  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ  ኮከብ አሰልጣኝ በመሆን የመጀመሪያው የውጭ አገር ዜጋ ሰርቢያዊ ዜግነት ያላቸው የቅዱስ ጊዮርጊሱ  አሰልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቹ ናቸው። ሰርዲዮቪች ሚቹ የመጀመሪያው የውጭ አገር ዜጋ ብቻ ሳይሆን ለአምስት ጊዜ በተደጋጋሚ ኮከብ ሆነው በመመረጥ ቀዳሚው አሰልጣኝ ናቸው። አሰልጣኙ በ1997 ዓ.ም ኮከብ ተብለው መመረጥ የጀመሩ ሲሆን በ1998፣ በ2000፣ በ2201 እና በ2002 ዓ.ም ኮከብ አሰልጣኝ መሆን የቻሉ አሰልጣኝ ናቸው። 

በ2003 ዓ.ም ኢትዮጵያ ቡና የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ሲችል አሰልጣኙ ውበቱ አባተ ደግሞ የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው ተመርጠዋል። በ2004 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደገና የፕሪሚየር ሊጉን ክብር ዘውድ ማስመለስ ሲችል የክለቡ አሰልጣኝ ዳንኤሎ ፒዮርሊጂ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው ተመርጠዋል። በ2005 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ደደቢት በአሸናፊነት በማጠናቀቁ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ከደደቢት የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ ሆነዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ዓመት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ተከታዮቹን በሰፊ የነጥብ ልዩነት በልጦ አሸናፊ ሲሆን    ኮከብ አሰልጣኝ በመሆን ለ11ኛ ጊዜ ኮከብ አሰልጣኝ በማስመረጥ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል።  

ኮከብ ተጫዋቾችን በማስመረጥ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ በሚያዘጋጀው ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የተሻለ ብቃት ማሳየት የቻሉ ተጫዋቾችን ለይቶ “ኮከብ ተጫዋች” አድርጎ ይመርጣቸዋል። በዚህ በኩል የመብራት ኃይሉ አንዋር ያሲን የመጀመሪያው ኮከብ ተጫዋች በመባል ስሙን በታሪክ መዝገብ ላይ ማስፈር ችሏል። የአሁኑ የኢትዮጵያ ቡና ምክትል አሰልጣኝ አንዋር ያሲንንትልቁ አንዋር ተከትሎ በዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው የምድር ባቡሩ አጥቂ አህመድ ጁንዲ ነው።  

በአሁኑ ወቅት የስፖርት ትጥቆችን በማከፋፈል ስራ ላይ የሚገኘው ሲራጅ ትንሹ አንዋር በ1992 ዓ.ም ከመብራት ኃይል ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል። የተከላካዩ አንዋር ሲራጅ መመረጥም በሁለት ዓመት ውስጥ መብራት ኃይልን ለሁለተኛ ጊዜ ኮከብ ተጫዋች በማስመረጥ ቀዳሚ ክለብ አድርጎታል። በ1993 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ አሸናፊ ግርማ የዓመቱ ታላቅ ተጫዋች ሆኗል። በቀጣዩ የውድድር ዓመት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ ሙሉዓለም ረጋሳ አዲሱ ባለተራ ሆኖ ብቅ ብሏል። 

በ1995 ዓ.ም በነበረው የፕሪሚየር ሊጉ የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ቡናው አሸናፊ ግርማ ለሁለተኛ ጊዜ ኮከብ ሆኖ በመመረጥ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል። ከኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ሁሉ በአመለሸጋነቱ ተለይቶ የሚታወቀው የሃዋሳ ከነማው ሙሉጌታ ምህረት በ1996 የታላቅ ተጫዋችነትን ዘውድ መድፋት ችሏል። ቀጣዮቹን ሁለት የውድድር ዓመታት ግን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ናቸው የኮከብነት ዘውዱን መውሰድ የቻሉት። በ1997 የውድድር ዓመት ተከላካዩ ደጉ ደበበ አርባምንጭ ጨርቃጨርቅን ለቆ ከተቀላቀለው አዲሱ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የዋንጫ ባለቤት ሲሆን እግረ መንገዱንም የዓመቱ ኮከብ ተጫዋችነት ክብርን ተቀዳጅቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በደጉ ደበበ የተቀበለውን የኮከብ ተጫዋችነት ክብርን አስጠብቆ በክለቡ እንዲቆይ ያደረገው አጥቂው ቢኒያም አሰፋ ነው በ1998 የውድድር ዓመት። 

ሃዋሳ ከነማ በ1999 ለሁለተኛ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫና የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ ባለቤት ሲሆን አማካዩ ሙለጌታ ምህረትም ለሁለተኛ ጊዜ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች በመሆን ከአሸናፊ ግርማ ጋር ተጋርቷል። በኢትዮጵያ አዲሱ ሚሊኒየም የተካሄደውን የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊስ በአሸናፊነት ሲያጠናቅቅ የኢትዮጵያ ቡናው ታፈሰ ተስፋዬ ደግሞ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። በ2001 ዓ.ም ደግሞ ከብሔራዊ ሊግ ያደገው ደቡብ ፖሊስ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ባይችልም አጥቂውን ጌታነህ ከበደን ኮከብ ተጫዋች አድርጎ ማስመረጥ ችሏል።  

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠ ብቸኛው ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው ነው። ጀማል ጣሰው የዓመቱ ኮከብ ተጫዋቸ ተብሎ የተመረጠው በ2002 ዓ.ም ሲሆን በጊዜው የሚጫወተው ለደደቢት ነበር። ቀጣዮቹን ሁለት የውድድር ዓመታት ደግሞ ኮከብ ተጫዋቾችን በማስመረጥ ፈረሰኞቹ ባለተራዎች ሆነዋል። በ2003 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳው ኢትዮጵያ ቡና ቢሆንም ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው ግን የፈረሰኞቹ አጥቂ አዳነ ግርማ ነበር። በቀጣዩ ዓመትም “የፈረሰኞቹ ታማኝ አገልጋይ” እየተባለ የሚጠራው ተከላካዩ ደጉ ደበበ ለሁለተኛ ጊዜ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠበትን እድል አግኝቷል በ2004 የውድድር ዓመት።  

ደደቢት የዋንጫ ባለቤት ሆኖ ባጠናቀቀበት 2005 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ደግሞ ጌታነህ ከበደ ከደደቢት ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል። ጌታነህ በደቡብ ፖሊስ ቆይታው አንድ ጊዜ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠ በመሆኑ የመጀመሪያው ተጫዋች አድርጎታል ከተለያዩ ሁለት ክለቦች ጋር ኮከብ በመሆን። ባለፈው ዓመት ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ኡመድ ኡክሪ ባለተራ ሆኖ ክብሩን ተቀዳጅቷል። በ17 ዓመታት የፕሪሚየር ሊጉ ቆይታም ፈረሰኞቹ አምስት ጊዜ፣ ቡናማዎቹ ሶስት ጊዜ፣ እንዲሁም መብራት ኃይል፣ ደደቢትና ሃዋሳ ከነማ ሁለት ሁለት ጊዜ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋቾችን ማስመረጥ ችለዋል።  

ኮከብ ግብ አግቢዎችን በማስመረጥ

ፕሪሚየር ሊጉ በ1990 ዓ.ም ተጀምሮ መብራት ኃይል ዋንጫውን አንስቶ ኮከብ አሰልጣኝና ኮከብ ተጫዋች ሲያስመርጥ የኢትዮጵያ መድኑ አጥቂ ሐሰን በሽር የከፍተኛ ግብ አግቢነቱ ባለቤት በመሆን ስሙን በደማቅ ቀለም ማጻፍ ከቻሉት ተጫዋቾቸ አንዱ ሆኗል። በ1991 ዓ.ም ቅዱሰ ጊዮርጊስ በአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ እየተመራ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ አድጎ በመጀመሪያ ዓመት ቆይታው የዋንጫውና የኮከብ አሰልጣኝ ክብሩ ባለቤት ሲሆን የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ክብር መቀዳጀት የቻሉት ግን ሁለት ተጫዋቾች ነበሩ በጣምራ።  የፈረሰኞቹ ግብ አነፍናፊ ጥበበኛው አሸናፊ ሲሳይና የሀዋሳ ከነማው በረከት ሐጎስ ነበሩ ኮከብ ግብ አግቢ መሆን የቻሉት።  

ብዙዎች “ቆጬ” በሚለው ቅጽል ስሙ ያውቁታል። ከግብ አፋፍ ላይ ያገኛትን ኳስ ከመረብ ጋር በማገናኘት የበረኞች ጠላት መሆኑን ደጋግሞ ማሳየት ችሏል ስንታየሁ ጌታቸው። ከአርባምንጭ ጎዳናዎች ተነስቶ በምድር ባቡር በኩል አልፎ ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው ስንታየሁ ጌታቸው ቆጬ በ1992 ዓ.ም 20 ግቦችን ለቢጫ ለባሾቹ በማስቆጠር የዓመቱ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኗል። ቆጬ 20 ግቦችን በተጋጣሚ ግብ ጠባቂዎች ግብ ላይ ባዘነበበት ዓመት ፈረሰኞቹ የዋንጫው ባለቤት ሲሆኑ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌንም የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ አድርገው አስመርጠዋል።  
በመልከ መልካምነቱና ለእግር ኳስ ባለው ትልቅ ፍቅር ተለይቶ የሚታወቀው ዮርዳኖስ አባይ ቀጣዮቹን ሶስት የውድድር ዓመታት የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ክብር ለብቻው ነግሶባቸዋል። ዮርዳኖስ አባይ በ1993 እና 1994 ከመብራት ኃይል ጋር ሆኖ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሲሆን በ1995 ዓ.ም ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሆኖ ኮከብ ግብ አግቢ መሆን ችሏል። ዮርዳኖስ ለሶስተኛ ጊዜ ኮከብ ግብ አግቢ በሆነበት ዓመት ክብሩን ከምድር ባቡሩ አህመድ ጁንዲ ጋር ነበር የተጋራው።  
አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ለማንሳት ከጫፍ ደርሶ ለጥቂት ዋንጫውን ባጣበት 2006 ዓ.ም አጥቂው መሳይ ተፈራ ኮከብ ግብ አግቢ መሆን ችሏል። በደረሰበት ጉዳት በጊዜ ከእግር ኳስ የተለየው መሳይ ተፈራ በአሁኑ ሰዓት የወላይታ ድቻ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ነው። ትራንስ ኢትዮጵያ በ1997 የውድድር ዓመት አጥቂውን መድሃኔ ታደሰን የዓመቱ ኮከብ ግብ አግቢ አድርጎ ማስመረጥ ችሎ ነበር።  

የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የነብሳቸውን ያህል የሚወዱትና የሚያከብሩት አጥቂ ቢኖር ታፈሰ ተስፋዬ ነው።  ቡናማዎቹ ለታፌ ትልቅ ፍቅር ቢኖራቸው አይገርምም ምክንያቱም የሃዋሳው ተወላጅ ለኢትዮጵያ ቡና ከተጫወተባቸው ዓመታት ውስጥ ሶስቱን ዓመታት ማሳለፍ የቻለው የዓመቱ ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኖ በመጨረስ ነበር። ታፈሰ በ1998 እንዲሁም በ2001 እና በ2002 ዓ.ም አከታትሎ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የጨረሰ ሲሆን በ2000 ዓ.ም ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የጨረሰው ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሳላሃዲን ሰይድ ነው። በአሁኑ ወቅት ለግብጹ ሃያል ክለብ አልሃሊ የሚጫወተው ሳላሃዲን ካለው ግብ የማግባት ችሎታ አኳያ ለተደጋጋሚ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ መሆን ያልቻለው ለሁለት ዓመታት በመቀጣቱና ቅጣቱን ከጨረሰ በኋላም ለፕሮፌሽናልነት ወደ ውጭ አገር ሂዶ በመጫወቱ ነው።  
የፈረሰኞቹ 19 ቁጥር ለባሽ አዳነ ግርማ በ2003 ዓ.ም ከደደቢቱ ጌታነህ ከበደ ጋር በጣምራ ኮከብ ግብ አግቢ ሆነው ሲጨርሱ በ2004 ዓ.ም ደግሞ አዳነ ግርማ ብቻውን የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት ክብር ተቀዳጅቷል። በ2003 ከአዳነ ግርማ ጋር የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት ክብር ያገኘው ጌታነህ ከበደ ከሁለት ዓመታት በኋላ ማለትም በ2005 ዓ.ም ክለቡ ደደቢት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ አጥቂው ደግሞ በግሉ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ዓመቱን ጨርሷል። ያለፈው ዓመት ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የጨረሰው ደግሞ ከዚህ ዓመተ ጀምሮ ለግብጹ እስክንድሪያ ክለብ ለመጫወት ወደ ግብጽ ያመራው ኡመድ ኡክሪ ነው ከቅዱስ ጊዮርጊስ።  
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17 ዓመታት ጉዞ አምስት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ለስድስት ጊዜ ኮከብ ግብ አግቢ ሆነው ሲጨርሱ ሁለት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ደግሞ አራት ጊዜ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አግቢ መሆን ችለዋል። ታፈሰ ተስፋዬ እና ዮርዳኖስ አባይ እያንዳንዳቸው ሶስት ሶስት ጊዜ ኮከብ ግብ አግቢ መሆን ሲችሉ አዳነ ግርማ እና ጌታነህ ከበደ ደግሞ ሁለት ሁለት ጊዜ ኮከብ ግብ አግቢ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው። ዮርዳኖስ አባይ ከሁለት ክለቦች ጋር ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን ብቸኛው ተጫዋች ነው። እንዲሁም በአንድ የውድድር ዓመት 24 የፕሪሚየር ሊግ ግቦችን በማስቆጠር ባለሪከርድ ነው።  

ዘንድሮስ ዋንጫው፣ ኮከብ አሰልጣኙ፣ ተጫዋቹና ግብ አግቢው ከየትኛው ክለብ ይሆኑ? ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!