በእሁዱ የሸገር ደርቢ ማን በበላይነት ያጠናቅቃል?
ህዳር 25, 2007

-“በጉዳት የምናጣው ተጫዋች ሀብታሙ ረጋሳ ብቻ ሲሆን በቅጣት የማይሰለፉት ግን ተከላካዮቹ ደረጀ ሀይሉና ሮቤል ግርማ ብቻ ናቸው። ዳዊት እስጢፋኖስ ከጉዳት ድኖ በጨዋታው ስለሚሰለፍ እንዲሁም ቡድናችን በተከታታይ እያሸነፈ በመምጣቱ ጨዋታውን የምንጀምረው በራስ መተማመን ላይ ሆነን በመሆኑ እናሸንፋለን ” የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ  ለኢትዮ ፉትቦል

-  “ቡድናችን ጨዋታውን በአሸናፊነት ለመጨረስ ዝግጁ ነው። በጉዳትም ሆነ በቅጣት ያጣነው ተጫዋች ስለሌለ ጥሩ ጨዋታ ጋር በአሸናፊነት ጨርሰን ያለንን የታሪክ የበላይነት እናስጠብቃለን።”  የቅዱስ ጊዮርጊሱ ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ለኢትዮ ፉትቦል

ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻልን ወደ መሪነቱ ስለሚያቀርበን በአሸናፊነት ለመጨረስ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።"  ዳዊት እስጢፋኖስ  ለኢትዮ ፉትቦል

StGeorge Vs Ethiopian Coffee


የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነገና እሁድ ሰባት ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።  በፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር መሠረት የፊታችን እሁድ ከአመሻሹ 11፡30 በአዲስ አበባ ስታዲየም የአገሪቱ ታላቅ ደርቢ ይካሄዳል የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ። ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ በስፖርት አፍቃሪው ቤተሰብ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ጨዋታ ሲሆን ቡድኖቹም ከፍተኛ ዝግጅ አድርገው ወደ ሜዳ ይገባሉ። የእሁዱን ጨዋታ አስመልክቶ የሁለቱም ክለቦች አሰልጣኞች ከኢትዮ ፉትቦል ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
 
የቅዱስ ጊዮርጊሱ ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ “ቡድናችን ጨዋታውን በአሸናፊነት ለመጨረስ ዝግጁ ነው። በጉዳትም ሆነ በቅጣት ያጣነው ተጫዋች ስለሌለ ጥሩ ጨዋታ ጋር በአሸናፊነት ጨርሰን ያለንን የታሪክ የበላይነት እናስጠብቃለን።” ሲል የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ በበኩሉ “በጉዳት የምናጣው ተጫዋች ሀብታሙ ረጋሳ ብቻ ሲሆን በቅጣት የማይሰለፉት ግን ተከላካዮቹ ደረጀ ሀይሉና ሮቤል ግርማ ብቻ ናቸው። ዳዊት እስጢፋኖስ ከጉዳት ድኖ በጨዋታው ስለሚሰለፍ እንዲሁም ቡድናችን በተከታታይ እያሸነፈ በመምጣቱ ጨዋታውን የምንጀምረው በራስ መተማመን ላይ ሆነን በመሆኑ እናሸንፋለን” ብሏል።  

“እንደሚታወቀው የሁለታችን ጨዋታ  የአገሪቱ ታላቅ ደርቢ በመሆኑ ከባድ ፉክክር ይታይበታል። የዘንድሮውን ጨዋታ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ማድረጋችን ደግሞ ለሁለታችንም ወሳኝነቱ አያጠያይቅም። ምክንያቱም ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻልን ወደ መሪነቱ ስለሚያቀርበን በአሸናፊነት ለመጨረስ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። የቡድናችን ስብስብ የሚያሳየውም ይህንን ነው” ሲል ለረጅም ጊዜ በጉዳት ከሜዳ ርቆ የቆየው የኢትዮጵያ ቡናው አምበል ዳዊት እስጢፋኖስ ተናግሯል። 

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ምንተስኖት አዳነ በቡና በኩል ደግሞ ዳዊት እስጢፋኖስ ከጉዳታቸው ሙሉ በሙሉ ድነው ለእሁዱ ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን አሰልጣኞቹ ተናግረዋል። ዳዊት እስጢፋኖስ ለረጅም ጊዜ ከጉዳት ጋር ሲታገል ቆይቶ ወደ ሜዳ ሲመለስ መስኡድ ማሀመድ ደግሞ የእሁዱን ጨዋታ በተቀያሪነት እንደሚጀምር ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በ2007 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ካስትል ዋንጫ ሁለቱ ቡድኖች በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው መደበኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለት እኩል ተለያይተው በመለያ ምት ኢትዮጵያ ቡና ማሸነፉ ይታወሳል። ሁለቱ ክለቦች በተገናኙበት አጠቃላይ ጨዋታ ግን ፈረሰኞቹ በሰፊ ልዩነት ቡናማዎቹን ይበልጧቸዋል። ባለፈው ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ውድድርም ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ጨዋታ ሁለት ለባዶ ሁለተኛውን ደግሞ ሁለት ለአንድ ማሸነፉ ይታወሳል። 

በሌላ የስድስተኛ ሳምንት ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ነገ ቅዳሜ ደደቢት የደቡብ ክልሉን ሲዳማ ቡናን በአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናግዳል። ሁለቱ ቡድኖች ያለፈውን ሳምንት ጨዋታቸውን በሽንፈት ያጠናቀቁ በመሆኑ በነገው ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ደደቢት በ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሁሉንም ግጥሚያዎቹን ያደረገው በአዲስ አበባ ስታዲየም ነው። 

እሁድ ከሚካሄዱ ስድስት ጨዋታዎች መካከል ከቅዱስ ጊዮርጊስና ከቡና ጨዋታ ውጭ አምስቱ ጨዋታዎች የሚካሄዱ በክልል ስታዲየሞች ነው። ወልድያ ላይ ወልድያ ከነማ መብራት ኃይልን የሚያስተናግድ ሲሆን ጎንደር ላይ ደግሞ ዳሽን ቢራ ሙገር ሲሚንቶን ይገጥማል። ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በኢትዮጵያ ቡና የተሸነፈው አርባምንጭ ከነማ በሜዳው በተመሳሳይ በዳሽን ቢራ የተሸነፈውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያስተናግዳል። አርባምንጭ ከነማ ፕሪሚየር ሊጉ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ጨዋታ አሸንፎ የማያውቅ ሲሆን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ከአምስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ነው ያሸነፈው። 

ሳምንትለት ቦዲቲ ላይ ሽንፈት ያስተናገደው አዳማ ከነማ በሜዳው መከላከያን ይገጥማል። መከላከያ ባለፈው ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉን መሪ ደደቢትን ያሸነፈ በመሆኑ በእሁዱ ጨዋታ በራስ መተማመን እንደሚገባ ይጠበቃል። በአሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ የሚሰለጥነው ሃዋሳ ከነማ በሜዳው ወላይታ ድቻን ያስተናግዳል። ሁለቱ ክለቦች በደቡብ ክልል የሚገኙ በመሆናቸው ጨዋታው የደቡብ ደርቢ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ሁለቱም ክለቦች ያለፈውን ሳምንት በድል በመወጣታቸው የእሁዱ ጨዋታም ወሳኝ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። 

 ፕሪሚየር ሊጉን ከላይ ደደቢት ከታች ደግሞ ወልድያ ሲመሩት ከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ደግሞ ሳሙኤል ሳኖሜ ከደደቢት በስድስት እና ቢኒያም አሰፋ ከቡና በአራት ግቦች አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ይመሩታል። 


ዘጋቢ፦ይርጋ አበበ 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!