ኢትዮጵያ ቡና 4ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄደ
ህዳር 26, 2007

ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ አራተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ትናንት በአዲስ አበባ ኔክሰስ ኢንተርናሽናል ሆቴል አካሂዷል። በጉባዔውም የተለያዩ ነጥቦች ተዳስሰዋል። የክለቡ የ2006 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸምና የ2007 ዓ.ም በጀት እቅድ ለጉባዔው ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት በሙሉ ድምጽ ጸድቋል። የክለቡ የሂሳብ ኦዲትም በውጭ ኦዲተር ተመርምሮ ሪፖርት ቀርቧል። ክለቡ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ አካባቢ እያስገነባ ያለውን የተጫዋቾች መኖሪያ ካምፕ ያለበትን ደረጃ የመሚያሳይ ዘጋቢ ፊልምም ለተሳታፊዎች ለእይታ ቀርቧል። 

ክለቡ በ2006 ዓ.ም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውን ሪፖርት ያቀረቡት የክለቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ የወንዶች ዋናው ቡድን የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በደብረዘይት ሲያካሂድ ቆይቶ ከአራት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ካደረገ በኋላ ወደ ውድድር መግባቱን ገልጸዋል። የፕሪሚየር ሊግ ውድድሩን ከመጀመሩ በፊትም በአዲስ አበባ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው ሃያል ክለብ ቲፒ ማዘንቤ ጋር ለሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን መጫዋቱንና በጨዋታው ምንም እንኳ ሶስት ለአንድ የተሸነፈ ቢሆንም ሰፊ ልምድና ጥሩ የስታዲየም ገቢ ያገኘበት ጨዋታ እንደነበር ተናግረዋል። ክለቡ በሙሉ የውድድር ዓመቱ 26 ጨዋታዎችን አካሂዶ 14 አሸንፎ ስድስቱን በአቻ ውጤት ሲለያይ በስድስቱ ደግሞ ተሸንፎ 48 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁንም በሪፖርታቸው ገልጸዋል።  

ከዋናው ቡድን በተጨማሪ በተስፋ ቡድን፣ በታዳጊዎችና በሴቶች ቡድን ሰፊ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን አቶ ገዛኸኝ ጠቁመዋል። የሴቶችን ቡድን በታዳጊዎችና በተተኪዎች ላይ የተገነባ በመሆኑ ሜዳ ላይ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ እንዳልቻለ ነገር ግን የተስፋና የታዳጊ ቡድኖቹ በተወዳደሩባቸው ውድድሮች ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል ሲሉ ተናግረዋል። 
የክለቡ የቦርድ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ በበኩላቸው በቅድሚያ ለክለቡ ስኬት የጀርባ አጥንት ናቸው ያሏቸውን አካላት በማመስገን ንግግር በማድረግ ጀምረው የ2007 ዓ.ም የክለቡን እቅድ አቅርበዋል። ክለቡን ለማጠናከር የመጀመሪያ ተመስጋኝ እንደሆኑ የሚጠቀሱት የቡና ቤተሰቦች ማለትም ቡና ላኪዎች ቡና ቆይዎች አጠቃላይ በቡና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ አካላት የሚለግሱትን ገንዘብ በወቅቱ መሰብሰብ እና የተጫዋቾችን መኖሪያ ካምፕ ግንባታ ማጠናቀቅ የዚህ ዓመት እቅድ መሆኑን ተናግረዋል። አያይዘውም በዚህ ዓመት 15 ሚሊዮን ብር ከቡና ቤተሰቦች እንደሚሰበሰብ እቅድ መያዙን ገልጸዋል።   

መቶ አለቃ ፈቃደ የክለቡ ችግር ሆነዋል ካላቸው ውጫዊ ችግሮች መካከል ኢትዮጵያ ቡና በርካታ ደጋፊ እንዳለው የሚታወቅ ቢሆንም ክለቡ በዓመት ከስታዲየም የሚያገኘው ገቢ መጠኑ አነስተኛ መሆኑ አንዱ ችግር ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት ኢትዮጵያ ቡና ከስታዲየም ገቢ ያገኘው ጠቅላላ ገንዘብ መጠን 750 ሺህ ብር ብቻ ነው። ይህ አኃዝ ደግሞ የክለቡን ደረጃ አይመጥንም ብለው እንደሚያምኑ ነው ፕሬዚዳንቱ የሚገልጹት። ክለቡም በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ለውይይት እንደተዘጋጀ የሚገልጹት መቶ አለቃ ፈቃደ በተለይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለችግሩ መፍትሄ እንዲሰጠው ለማድረግ ሰፊ ርቀት መጓዛቸውን ለጉባኤው ገልጸዋል። ነገር ግን ሌሎች ክለቦች በዚህ ጉዳይ ሊተባበሯቸው እንዳልቻሉ ገልጸዋል። 

ሌላው ለክለቡ እቅድ ስኬት ግቡን አለመምታት ምክንያት ብለው ያቀረቡት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በታዳጊዎችና በወጣት ቡድኖች መካከል ውድድር አለመካሄዱን ነው። የክለቡ ሥራ አስኪያጅ የተስፋውና የታዳጊ ቡድኑን በጠቀሱበት ሪፖርታቸው የገለጹት ውጤት የተገኘውም የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው የክለቦች ውድድር መሆኑን ተናግረዋል። ነገር ግን ለአንድ አገር እግር ኳስ እድገት የሚበጀው ተጫዋቾችን ከክለብ ክለብ እያዘዋወሩ መጠቀም ሳይሆን የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ክለቦች በታዳጊዎችና በተተኪዎች ላይ ሰፊ ሥራ ሲሰሩ መሆኑን አያይዘው ገልጸዋል። 

በእለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የፌዴራል ሰፖርት ኮሚሽን የማህበራት ማደራጃና እውቅና ዳይሬክተር አቶ አበባው ከልካይ ኢትዮጵያ ቡና ውጫዊ ችግር ሆነብኝ ያለው የስታዲየም ቲኬት ገቢ ችግር ለስፖርት ኮሚሽንም ራስ ምታት ሆኖበታል ብለዋል። እንደ አቶ አበባው ከልካይ ገለጻ የስታዲየም መግቢያ ቲኬት ጉዳይ በሽያጭ ብቻ ሳይሆን በህትመትም ችግር አለበት። “በሽያጭ ብቻ ሳይሆን ፎርጅድ የመግቢያ ቲኬቶች እየታተሙ” በመሰራጨት ላይ መሆናቸውን ነው አቶ አበባው ከልካይ የገለጹት። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ጊዜ የማሻሻያ ሥራዎችን ለመሥራት ሙከራ ያደረገ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች እንዳልተሳካ ገልጸው ወደፊት ግን ክለቦችም እንዲተባበሩት አሳስበዋል። 

አቶ አበባው አክለውም “እንደ ኢትዮጵያ ቡና አይነት ህዝባዊ ክለቦች ራሳቸውን በገቢ ማጠናከር ያለባቸው የራሳቸውን ህጋዊ ምልክቶች በጋዜጣ አሳውጀው የባለቤትነት መብታቸውን አስከብረው የክለባቸውን መገለጫ የሆኑ ቁሳቁሶችን በመሸጥ ነው። በዚህ በኩል መንግሥት ማንኛውም ህዝባዊ ክለብ በስፖርት እቃዎችና የክለባቸው አርማ ያረፉባቸውን ቁሳቁሶች ለመሸጥ የሚያስችላቸውን ፈቃድ ሰጥቷል። ኢትዮጵያ ቡናም የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ወደ ገበያ እንዲገባና ራሱን በገቢ አሳድጎ ወደ ፕሮፌሽናልነት እንዲያድግ ማድረግ አለበት” ብለዋል። አሁን ያለው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ አወቃቀር ፕሮፌሽናልነትን የተከተለ እነደሆነም ገልጸዋል።  

በመጨረሻም ከአምስት ወራት በፊት የደጋፊዎች ማህበርና በክለቡ ጽ/ቤት በኩል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ በማበጀት በሰላም በመፍታት ጉባዔው ተጠናቅቋል። 


ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ አ
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!