ኢትዮጵያ ቡና ከተከታታይ ድሉ በስተጀርባ
ህዳር 29, 2007

- ኢትዮጵያ ቡና እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች  አራት የቀይ ካርድ ተመዞበታል።

- “እስካሁን የተመለከትናቸው ቀይ ካርዶች ሙሉ በሙሉ በተጫዋቾች ጥፋት ብቻ የተፈጠሩ ናቸው ማለት ይከብዳል። ነገር ግን በተጫዋቾቻችን የቴክኒክ ስህተት የተከሰቱትን አይነት ቅጣቶች እንዳይደገሙ እንሰራለን። ” ጥላሁን መንገሻ ለኢትዮ ፉትቦል

- “ዳዊት እስጢፋኖስ ከጉዳት በተመለሰበት የመጀመሪያ ጨዋታ ያሳየው ብቃት በጣም ጥሩ ነው ከጠበኩት በላይ ሆኖብኛል። ”  ጥላሁን መንገሻ  ለኢትዮ ፉትቦል

Ethiopian Coffee FC players 2007/14


ኢትዮጵያ ቡና በ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስት ጨዋታዎችን አካሂዶ ሁለቱን ጨዋታዎች በተከታታይ በመሸነፍ አጀማመሩን አክፍቶ ነበር። ሆኖም ክለቡ ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራን በቢኒያም አሰፋ ሁለት ጐሎች ማሸነፍ ከጀመረበት ጨዋታ ጀምሮ በተከታታይ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በማሸነፍ ነጥቡን ዘጠኝ በማደረስ ከመሪዎቹ በቅርብ ርቀት ላይ ሊቀመጥ ችሏል። ትናንት በተካሄደው በታላቁ የአገሪቱ ደርቢ ላይም የዘወትር ተቀናቃኙን ቅዱስ ጊዮርጊስን በአስቻለው ግርማ ብቸኛ ግብ አንድ ለባዶ ማሸነፉ ይታወሳል። 
Tilahun Mengesha Ethiopian Coffee Head Coach
ከጨዋታው በኋላ ለኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም አስተያየቱን በስልክ የገለጸው የክለቡ አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ ድል በማድረጋቸው መደሰቱን ገልጾ በተለይ ለረጅም ጊዜያት ከጉዳት ጋር ሲታገል የቆየው አምበሉ ዳዊት እስጢፋኖስ ያሳየውን ብቃትም አወድሶታል። “ከጉዳት በተመለሰበት የመጀመሪያ ጨዋታ ያሳየው ብቃት በጣም ጥሩ ነው ከጠበኩት በላይ ሆኖብኛል። ወደ ፊት ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን አድርጎ ወደ ሙሉ ብቃቱ ሲመለስ ደግሞ ቡድናችንን ይበልጥ እንደሚያጠናክርልን ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል።  

የቡድኑን የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት ተከታታይ ሽንፈት ተመልክተው በአሰልጣኙና በቡድኑ ስብስብ ላይ ጥያቄ አንስተው የነበሩ ደጋፊዎችም አሁን ሃሳባቸውን ቀይረው በቡድናቸው ላይ እምነት ማሳደር ጀምረዋል። አሰልጣኛቸውንና ተጫዋቾቻቸውንም “ከጎናችሁ ነን” እያሉ ይገኛሉ።  

Dereje,Robel, Mussie and Tilahun
ነገር ግን ክለቡ ከተከታታይ ድሉ በተገዳኝ ሜዳ ላይ እያስመዘገበ ያለው ተከታታይ የተጫዋቾች ቀይ ካርድ ደግሞ ክለቡ ቆም ብሎ ራሱን እንዲፈትሽ ያደርገዋል የሚሉ ወገኖች ተፈጥረዋል። በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ሳምንት አሰላ ላይ ከሙገር ሲሚንቶ ጋር በተደረገ ጨዋታ አማካዩን ደረጀ ሀይሉን፣ በአራተኛ ሳምንት ጨዋታው ጎንደር ላይ ተከላካዩ ሮቤል ግርማንና ግብ ጠባቂውን ሙሴ ገብረኪዳንን እንዲሁም በስድስተኛ ሳምንት ጨዋታው ደግሞ አማካዩን ጥላሁን ወልዴን በድምሩ አራት ተጫዋቾችን በቀይ ካርድ እንዲያጣ ተገድዷል። እንደዚህ አይነት ተደጋጋሚ ቀይ ካርዶች ደግሞ ክለቡን ሜዳ ላይ ከመጉዳቱም በተጨማሪ በውጫዊ ምስሉ ላይም የሚፈጥሩት አሉታዊ ተጽእኖዎች ይኖራሉ።  

 ተጫዋቾች ተደጋጋሚ የቀይ ካርድ ሰለባ መሆናቸውን አስመልክቶ ለአሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም በስልክ ጥያቄ አቅርቦለት ነበር። “እስካሁን የተመለከትናቸው ቀይ ካርዶች ሙሉ በሙሉ በተጫዋቾች ጥፋት ብቻ የተፈጠሩ ናቸው ማለት ይከብዳል። ለምሳሌ አሰላ ላይ ደረጀ የተመለከተው ቀይ ካርድ በዳኛው ስህተት ሲሆን እኛም ውሳኔውን በይፋ ተቃውመነዋል። ጎንደር ላይ ሙሴ ያየው ቀይ ካርድም በተጫዋቹ ቴክኒካል ስህተት ሲሆን እንደዚህ አይነት ስህተቶች በድጋሚ ላለማስተናገድ እንሰራለን። የጥላሁንን ካየን ግን በእንቅስቃሴ ላይ እያለ ነው ዳኛው ስህተት ሰርተሃል ያሉት። ለዚህ ውሳኔ የምሰጠው አስተያየት የለም” ሲል ተናግሯል። አያይዞም በትናንቱ ጨዋታ ቡድናቸው ላይ ተሰጥቶ የነበረውንና ፍጹም ገብረማሪያም ያባከነውን ፍጹም ቅጣት ምት ትክክል እንዳልነበረ ተናግሯል። 

ኢትዮጵያ ቡና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በአምስት ጨዋታ ዘጠኝ ነጥብ ይዞ በነጥብ ከሲዳማ ቡና እና መብራት ኃይል ዝቅ ብሎ እንዲሁም ከደደቢት እኩል ነጥብ ሸምቶ በግብ ክፍያ ተበልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ደደቢትን የሚያስተናግድ ይሆናል።

 በሌላ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ አዳማ ላይ አዳማ ከነማና መከላከያ መረባቸውን ሳያሰደፍሩ ባዶ ለባዶ ተለያይተዋል። አዝናኝ እንቅስቃሴና ማራኪ የኳስ ቁጥጥር ባልታየበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በርካታ ለግብ የቀረቡ የግብ አጋጣሚዎች በሁለቱም በኩል መክነዋል። በተከታታይ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ማሸነፍ የተሳነው አዳማ ከነማ በትናንቱ ጨዋታ አሸንፎ እንዲወጣ ደጋፊው ሰፊ እምነት አሳድሮ ወደ ስታዲየም ጎርፎ የነበረ ቢሆንም ጭራሽ በኳስ ቁጥጥርና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመቅረብ ከእንግዳው ቡድን አንሶ ተገኝቷል። በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን የተከታተሉ ደጋፊዎችም በአሰልጣኙና በአንዳንድ ተጫዋቾች ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ታይተዋል። 

ጨዋታውን በረዳት ዳኝነት የመሩት የመስመር ዳኛው በተደጋጋሚ የሰሯቸው ሁለት ስህተቶች ባይፈጠሩ ኖሮ መከላከያ ባለሜዳውን ሁለት ለባዶ ማሸነፍ የሚያስችሉ የግብ እድሎችን ፈጥሮ ነበር። ሆኖም የመስመር ዳኛው የመከላከያ አጥቂዎች መሃመድ ናስርና ሙሉዓለም ጥላሁንን ከጨዋታ ውጭ ሳይሆኑ ከጨዋታ ውጭ ናችሁ ብለው ያገኟቸውን የግብ እድሎች አባክነባቸዋል። 

አንዴ ማሸነፍ ከጀመሩ በኋላ የሶስት ነጥብ ጣዕም የገባቸው የሚመስሉት የ2006 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ክለብ የነበሩት ዳሽን ቢራና ወላይታ ድቻ ትናንትም አሸንፈዋል። ጎንደር ላይ ሙገር ሲሚንቶን ያስተናገደው ዳሽን ቢራ በተዘራ ጌታቸው ብቸኛ ግብ ሲያሸንፍ ሃዋሳ ላይ በደቡብ ደርቢ ሃዋሳ ከነማና ወላይታ ድቻ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ በባዬ ገዛኸኝ ግብ አንድ ለባዶ በማሸነፍ ተመልሷል። 

ዳሽን ቢራ ያለፈውን ሳምንት በፕሪሚየር ሊጉ ለተጫዋቾች ዝውውር በርካታ ገንዘብ አውጥቶ የከረመውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አሸንፎ የነበረ ሲሆን ወላይታ ድቻ ደግሞ በሜዳው አዳማ ከነማን ሶስት ለሁለት ማሸነፉ ይታወሳል። በአንጻሩ በአምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ወልድያ ከነማን አሸንፎ የዓመቱን የመጀመሪያ ሙሉ ሶስት ነጥብ አግኝቶ የነበረው ሃዋሳ ከነማ የሽንፈት ሃንጎቨሩ አገርሽቶበታል። 
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሶስት ነጥብ የሩቅ አገር ዘመዳማቾች ሆነዋል። በፕሪሚየር ሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ሁለት ለባዶ አሸንፎ አጀማመሩን አሳምሮ የነበረው የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማሪያም ቡድን ትናንት ወደ አርባምንጭ ተጉዞ የዓመቱን ሁለተኛ ሽንፈት ተጎንጭቶ ተመልሷል። ንግድ ባንክ እውነትም ትክክለኛ ነጥብ አበዳሪ መሆኑን ትናንት ደግሞታል። አርባምንጭ ከነማ በበኩሉ ከአምስት ተከታታይ ጨዋታ ድል አልባ ጉዞ በኋላ የዓመቱን የመጀመሪያ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት ችሏል።  

ወልድያ የማሸነፊያ መንገዱን የሚያሳየው አልተገኘም። ትናንትም በሜዳው መብራትኃይልን አስተናግዶ ሙሉ ሶስት ነጥብ አስቋጥሮ ሸኝቶታል። በዚህም በዓመቱ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሁሉቱን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ አራቱን ተሸንፎ በሁለት ነጥብ የደረጃውን ግርጌ በብቸኝነት ተቆጠጥሮታል። ወልድያ በተደጋጋሚ ከመሸነፉም በተጨማሪ በርካታ የግብ ናዳ የወረደበት ክለብ እሱ ብቻ ሆኗል። ሌላው ቀርቶ በዓመቱ ውስጥ ካደረጓቸው ጨዋታዎች አንድ አንድ ጊዜ ብቻ ሙሉ ሶስት ነጥብ ያገኙት ሃዋሳ ከነማና ደካማው አዳማ ከነማ ማሸነፍ የቻሉት ወልድያን ነው። ተደጋጋሚ ሽንፈቱ ክለቡን ወደመጣበት እንዳይመልሰው ያሰጋ ሲሆን ክለቡን ከመውረድ ለመታደግ ርብርብ የሚደረግበት ወቅትም አሁን ነው። 

ፕሪሚየር ሊጉን ሲዳማ ቡና በ11 ነጥበ ሲመራ መከላከያ በ10 ይከተላል። ዘንድሮ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀሉት ወልድያና አዳማ ከነማ ደግሞ የመጨረሻዎቹን ሁለት ደረጃዎች ይዘዋቸዋል። ሳሙኤል ሳኖሜና ቢኒያም አሰፋ ደግሞ የሳተና ግብ አግቢዎችን ደረጃ በቀዳሚነት ተቆጣጥረዋቸዋል።  


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Besufekad [1098 days ago.]
 Ethiopia Buna forever!!

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!