የወልዲያ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች የገቢ ማሰባሰቢያ ባዛር አዘጋጅተው በሚሊዮን የሚቆጠር ብር አሰባሰቡ
ታህሳስ 03, 2007

"በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ የታሰበውን ያህል ገንዘብ ተገኝቷል"  አቶ ጸሀዬ ደመላሽ የከተማዋ ከንቲባና የክለቡ የቦርድ ተጠሪ ለኢትዮ ፉትቦል 

ወልድያ እግር ኳስ ክለብ በ2006 ዓ.ም በብሔራዊ ሊግ ሲወዳደር ቆይቶ በያዝነው ዓመት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገ ክለብ መሆኑ ይታወቃል። ክለቡ በተጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አንዱንም እንኳ ማሸነፍ ተስኖት ሁለት ነጥብ ብቻ ይዞ ዘጠኝ የግብ እዳ ተሸክሞ የደረጃው ግርጌ ላይ ተቀምጧል። ለክለቡ ድል አልባ ጉዞ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የልምድ ማነስ፣ የኢኮኖሚ አቅም ውስንነትና እንደ ነጋድራስ ከሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ጫፍ እስከ ደቡብ ምዕራብ አጥናፍ እየተጓዘ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ መጓዙ ናቸው። 

ለዚህም ይመስላል ክለቡና የክለቡ ሽንፈት የእኛም ሽንፈት ነው የክለቡ ትንሳኤ ደግሞ የእኛም ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች ክለቡን በገቢ ለማጠናከር ሰሞኑን በወልድያ ከተማ የገቢ ማሰባሰቢያ ባዛር ያዘጋጁት። በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ የታሰበውን ያህል ገንዘብ መገኘቱን የከተማዋ ከንቲባና የክለቡ የቦርድ ተጠሪ አቶ ጸሀዬ ደመላሽ ለኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም በስልክ ገልጸዋል። እንደ ከንቲባው ገለጻ ክለቡ ያለበትን የገንዘብ ውስንነት በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ ታስቦ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም የክልሉ መንግሥት አንድ ሚሊዮን ብር በእርዳታ መልክ ለግሷል። ሌሎች ባለሃብቶችና የተለያዩ ድርጅቶችም ልባቸው ያሳሰባቸውንና ኪሳቸው የፈቀደውን እያወጡ ከመስጠት ወደኋላ አላሉም። በዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል ከንቲባ ጸሀዬ ደመላሽ። 

አንድ ክለብ ተቋቁሞ ለውድድር ሲዘጋጅ ቀድሞ ሊታሰብባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች ቀዳሚው ነጥብ ክለቡ ለቅድመ ውድድር፣ ለውድድር፣ ለወዳጅነት ጨዋታና ለኢንሹራንስ የሚደረጉ ወጭዎችን ነው። በዚህ መልኩ ያልተዋቀረ ክለብ በሚወዳደርበት የውድድር መስክ ሁሉ መንገዶች ፈታኝና አጥር የበዛባቸው መሆኑ ግልጽ ነው። ወልድያ ከነማንም የገጠመው ትልቁ የውጤት ቀውስ የጀመረው ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ከማለፉ በፊት ክለቡ እዚህ ይደርሳል ተብሎ የታሰበ ባለመሆኑ ነው። ሰገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ አይነት። ይህ በመሆኑም ክለቡን ተጫውተው ያልጠገቡ ሩጠው ያልደከሙ ባለክህሎት ወጣቶችን ልምድና ብቃት ካላቸው ተጫዋቾች ጋር በማቀናጀት ማደራጀት ባለመቻሉ አሁን ሜዳ ላይ እያሳየ ያለው ውጤት ምስክር ሆኗል። ቶሎ መታከም ሲቻል ዘግይቶ መድሃኒት ፍለጋ መሮጥ።  

ክለቡ ይህንን ቀድሞ ባለማሰቡ ለተጫዋቾች ዝውውር የፊርማ ክፍያ የሚያወጣው ገንዘብ እንኳ ከደሃ ማሰሮ እንደሚንጨለጨል ዘይት የተቆጠበ ነው። ክለቦች ቢችሉ ለዋንጫ ባይችሉ በፕሪሚየር ሊጉ ለመቆየትና ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ለመገኘት ረብጣ ብሮችን በአንድ ጀምበር በሚያፈሱበት በዚህ ወቅት የወልድያ አካሄድ ግን ዘመኑን ያልተከተለ ሆኗል። ራሱን በአዳዲስ ተጫዋቾች ማደራጀት ሲገባውም ጭራሽ እንደ ተስፋዬ ነጋሽ አይነት የራሱን ኮከብና ወሳኝ ተጫዋቾች ለተቀናቃኞቹ በመናኛ ክፍያ መሸጡ አስገራሚ ነው። 

ሌላው የክለቡ ችግር የሚባለው የተጫዋቾች የጥራት ደረጃ ነው። ከላይ በተጠቀሰው አሳማኝ ምክንያት የተነሳ ወልድያ ስፖርት ክለብ ወሳኝ አጥቂውን ተስፋዬ ነጋሽን ሽጦ በምትኩ ማዘዋወር የቻለው እድሜ ጠገቦቹንና ተፈላጊነታቸው እዚህ ግባ የማይባሉትን አብይ በየነንና በዳሶ ሆራን ነው። ወልድያ እየሰጠመ ያለ መርከብ ነው። እነዚህ ተጫዋቾች ደግሞ በመስመጥ ላይ ያለውን መርከብ መታደግ የሚችሉ ብልህ ካፒቴኖች ናቸው ማለት ይከብዳል።  

ዘግይቶም ቢሆን የመጣ ከመቅረት ይሻላልና አሁንም ወልድያ በጥር ወር በሚከፈተው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሲከፈት ክለቡን ከውድቀት ሊታደጉ የሚችሉ ተጫዋቾችን ማዘዋወር ይችላል። ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን እያካሄደ ያለው የገቢ ማሰባሰቢያ ባዛር ወሳኝነቱ የማያጠያይቅ ጉዳይ ነው። ለክለቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለኢትዮፉትቦል ዶት ኮም እንደገለጹት ክለቡ በገቢ ማሰባሰቢያ ባዛሩ ወደ አስር ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰብ ችሏል። የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ ክለቡ በባዛሩ ማግኘት ችሎ ከሆነ ዛሬ በበርካታ የግብ እዳ የተሞላው የክለቡ የነጥብ መያዣ ቦርሳ ያኔ የራሱን ነጥብ መቋጠር ያስችለዋል ማለት ነው። 
 
ዘጋቢ፦ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦልethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!