ሰባተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለት የአዲስ አበባ ደርቢዎችን ያስተናግዳል
ታህሳስ 03, 2007

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነገና እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ሰባት ጨዋታዎችን ያስተናግዳል። ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲሆን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በጥሩ አቋም ላይ የሚገኙት መብራት ኃይልና ዳሽን ቢራ ይገናኛሉ። ሁለቱ ክለቦች ያለፉትን ጨዋታዎቻቸውን በድል የተወጡ በመሆናቸው በጥሩ የስነ ልቦና ዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ጨዋታውን አስመልክቶ ለኢትዮ ፉትቦል አስተያየቱን በስልክ የገለጸው የዳሽን ቢራው አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ “ቡድናችን በተከታታይ ማሸነፉ በራሳችን ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖረን አስችሎናል። ከሲቲ ካፑ ጀምሮ የነበሩብንን ክፍተቶች እየደፈንን ስለሄድን አሁን በጥሩ ዝግጅት ላይ ነው የምንገኘው” ብሏል። አሰልጣኝ ሳምሶን አያይዞም ክለቡ በዚህ ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በሜዳው ሳያሸንፍ በመቆየቱ በደጋፊው ላይ የተወሰነ ቅሬታ አስነስቶ የነበረ መሆኑንና ባለፈው ሳምንት ሙገርን በማሸነፉ መነቃቃት እንዳሳየ ገልጿል። ከነገው ጨዋታም የጎንደር ህዝብ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘን እንድንመለስ ይፈልጋል ያለው አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ጨዋታውን ለማሸነፍ መዘጋጀታቸውን ተናግሯል። 

  በእለቱ የሚጠበቀው ሌላ ጨዋታ የሚካሄደው ደግሞ የአዲስ አበባዎቹ ኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት የሚያካሂዱት ጨዋታ ነው። ሁለቱ ክለቦች ካላቸው የቆየ ተቀናቃኝነትና የነጥብ መቀራረብ አኳያ በነገው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቀቃል። ሁለቱም ክለቦች የኋላ መስመራቸው ደካማ መሆኑ የሚገር ሲሆን በተለይ ደደቢት ከጠንካራ ክለቦች ጋር ሲገናኝ መቋጠር የማይችለው የግብ መስመሩ በነገው ጨዋታም ዋጋ እንዳያስከፍለው ተሰግቷል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ ጠንካራ የመሃል መስመር ያለው ሲሆን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ እያስመዘገበ ያለው ውጤትና የተጋጣሚው ተደጋጋሚ ሽንፈት ነገም ደጋፊው ከቡድኑ ሙሉ ሶስት ነጥብ እንዲጠብቅበት አስገድዶታል። ጠንካራ አማካይ ክፍል እንዳለው የሚነገርለት ኢትዮጵያ ቡና በነገው ጨዋታ አማካዮቹን ጥላሁን ወልዴን በቅጣት እንዲሁም መስዑም መዳመድንና ሃብታሙ መንገሻን በጉዳት አገልግሎታቸውን የማያገኝ ይሆናል። 

ፕሪሚየር ሊጉ እሁድም ቀጥሎ ሲውል አምስት ጨዋታዎችን ያካሂዳል። ከአዲስ አበባ ውጭ ሶስት ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲሆን ይርጋለም ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በአቋም መዋዠቅ ላይ የሚገኘውን አዳማ ከነማን ያስተናግዳል። አዳማ ከነማ በዚህ ዓመት ያካሄዳቸውን ስድስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል ከሜዳው ውጭ ተጫውቶ ነጥብ ያገኘበት ጨዋታ የለም። ሲዳማ ቡና በበኩሉ በሜዳው ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ብቻ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፏል። 

አሰላ ላይ ሙገር ሲሚንቶ አርባምንጭ ከነማን ያስተናግዳል። ሙገር ሲሚንቶ በዚህ ዓመት አማካዩን በሀይሉ ግርማን በመሸጡ የመሃል ክፍሉ ሳስቷል እየተባለ የሚታማ ቢሆንም እያስመዘገበ ያለው ውጤት ግን ተስፋ ሰጭ ነው ማለት ይቻላል። ባለፈው ሳምንትም ወሎ ድረስ ተጉዞ ባለሜዳውን ወልድያን አሸንፎ መመለሱ ይታወሳል። አርባምንጭ ከነማ በበኩሉ በተጀመረው የውድድር ዓመት ስድስት ጨዋታዎችን አካሂዱ በአንዱ ተሸንፎ አንዱን አሸንፎ በቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች አቻ በመለያየት ሰባት ነጥብ ይዟል። 

ሌላው ክልል ላይ የሚካሄደው ጨዋታ ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ወልድያን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ነው። ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች አዳማ ከነማንና ሃዋሳ ከነማን በተከታታይ በማሸነፍ በጥሩ የራስ መተማመን ላይ የሚገኙት የመሳይ ተፈሪ ልጆች በእሁዱ ጨዋታም ወልድያን የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷቸዋል። ወልድያ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው በዚህ ዓመት መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ አንዱንም እንኳ ማሸነፍ ተስኖት በሁለት ነጥብ የደረጃው ግርጌ ላይ የተቀመጠ ክለብ ነው። ባለሜዳዎቹ ወላይታ ድቻዎች እስካሁን ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች የተሸነፉት ሁለት ጊዜ ብቻ ሲሆን በሜዳቸው የተሸነፉት ደግሞ አንዱን ብቻ ነው በመክፈቻ ጨዋታቸው በዳሽን ቢራ የደረሰባቸው አንድ ለባዶ ሽንፈት። ክልል ላይ የሚካሄዱ ሁሉም ጨዋታዎች የሚጀምሩት በተመሳሳይ ሰዓት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ነው።  

አንድ ለእናቱ የሆነው አዲስ አበባ ስታዲየም እሁድም ሁለት ጨዋታዎችን ያስተናግዳል። ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት መከላከያ ሃዋሳ ከነማን ያስተናግዳል። መከላከያ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አንዱንም ያልተሸነፈ ሲሆን አስር ነጥብ በመሰብሰብም ከመሪው ሲዳማ ቡና ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የታረቀኝ አሠፋ ቡድን ሃዋሳ ከነማ በበኩሉ ከአምስት ጨዋታዎች አንድ ተሸንፎ አንድ አሸንፎ ሶስት በአቻ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን የሰበሰበው ነጥብም ስድስት ብቻ ነው። 

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነውና በጉጉት የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ከቀኑ 11፡30 በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ይካሄዳል። ሁለት ጨዋታዎችን በተከታታይ በዳሽን ቢራና አርባምንጭ ከነማ የተሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና በእሁዱ ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት እችላለሁ ሲል በአሰልጣኙ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም በኩል ድምጹን አሰምቷል። አሰልጣኝ ጸጋዬ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረገው የስልክ ቆይታ “ነጥብ የጣልንባቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ስትመለከት በተጋጣሚዎቻችን ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን በራሳችን ስህተቶችና በዳኛ በደል የተፈጠሩ ናቸው። በእሁዱ ጨዋታ ግን የራሳችንን ስህተት አርመን በመግባት ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን” ሲል ተናግሯል። የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ በተደጋጋሚ ጊዜ በማንሳት ተፊካካሪ የሌለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ሳምንት በታላቁ የሸገር ደርቢ የደረሰበትን ሽንፈት እሁድ ያወራርዳል ተብሎ ይጠበቃል። 


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!