በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መብራት ኃይል መሪነቱን ሲጨብጥ ደደቢት እየተንሸራተተ ነው
ታህሳስ 05, 2007


የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎችን አካሂዷል። ከቀኑ 9፡00 የተገናኙት የአጥናፉ ዓለሙ ቡድን መብራት ኃይል ከሰሜን ኢትዮጵያው ተወካይ ዳሽን ቢራ ጋር ነበር። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ተደጋጋሚ የግ ሙከራዎች የተደረጉበትና ጥሩ የኳስ ፍሰት የታየበት ነበር። 

ባለሜዳዎቹ መብራት ኃይሎች በእለቱ ድንቅ ሆኖ ያመሸው ፕሮፌሽናሉ ፒተር ያቀበለውን ኳስ አምበሉ አዲስ ነጋሽ በ26ኛው ደቂቃ ባገባት ግብ መምራት ቻለ። ከሁለት ሳምንት በፊት ዳሽን ቢራ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ለባዶ ሲያሸንፍ የማሸነፊዋን ግብ ያስቆጠረው ይተሻ ግዛው ደግሞ ዳሽን ቢራን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር በ41ኛው ደቂቃ። ጨዋታው በአቻ ውጤት በቀጠለበት ሰዓት የቀድሞው የመብራት ኃይልና የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ ዮርዳኖስ አባይ ከየመን ቆይታው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታውን አድርጎ የመጀመሪያ ግቡንም አስቆጠረ ለቀድሞ ክለቡ ለመብራት ኃይል። ዮርዳኖስ አባይ ያስቆጠራትን ግብ አመቻችቶ በማቀበል ትልቁን የቤት ሥራ የሠራው አሁንም ፕሮፌሽናሉ ፒተር ነው። ውጤቱን ተከትሎም መብራት ኃይል የዛሬውን የሲዳማ ቡናን ጨዋታ ውጤት እስኪጠብቅ ድረስ ፕሪሚየር ሊጉን መምራት አስችሎታል።

Coffee vs Dedebit
በእለቱ የተካሄደው ሁለተኛ ጨዋታ በበርካታ ደጋፊ ተሞልቶ የተከናወነው የኢትዮጵያ ቡና እና የደደቢት ጨዋታ ነው። የአዲስ አበባ ስታዲየም ከአፍ እስከ ገደፉ በተመልካች በተጨናነቀበት ጨዋታ ከአመሻሹ 11፡30 የተጀመረው ጨዋታ ብዙም ማራኪና እንቅስቃሴ አልታየበትም ነበር። በዚህ ጨዋታም የደደቢቱ አዳሙ መሃመድ ለኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ውለታ ሰርቷል በራሱ ላይ ግብ በማስቆጠር። 
Coffee supporters celebrating the first goal
ለዚህች ግብ መቆጠር ፈጣኑ የመስመር ተጫዋት የኢትዮጵያ ቡናው አስቻለው ግርማ ተጽእኖ ቢኖርበትም የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባንጫ የሰራው ስህተት ግን የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። የግቡን መስመር ቀድሞ ለቆ ባይወጣ ኖሮ አዳሙ ወደራሱ የግብ ክልል የመታትን ኳስ በቀላሉ ግብ እንዳትሆን ማድረግ ይችል ነበር። 
Coffee vs Dedebit in Action

ያለፉትን ሶስት ጨዋታዎች ለክለቡ በጉዳት መሰለፍ ያልቻለው የደደቢቱ ሸይቩ ጅብሪል በትናንቱ ጨዋታ ከጉዳት ተመልሶ ክለቡን ማገልገል ችሎ ነበር። ሆኖም የሸይቩን ያህል ጠንካራ ያልሆኑት የደደቢት ተጫዋቾችና ክለቡም በደንብ የተዋቀረ ባለመሆኑ ከመሸነፍ አልዳነም። 

ከእረፍት መልስ ተሽለው የገቡት ደደቢቶች ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለው የነበረ ቢሆንም አጥቂዎቻቸው የግቡን መስመር ለይተው ባለማግኘታቸው ክለቡን ዋጋ አስከፍለውታል። በተለይ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ዳዊት ፈቃዱን ተጠባባቂ አድርገው የመጀመሪያ ቋሚ ተሰላፊ ያደረጉት የቀድሞው የመብራት ኃይል አጥቂ በረከት ይሳቅ እና ሳሙኤል ሳኖሜ ያባከኗቸው የግብ እድሎች የሚያስቆጩ ናቸው። በረከትን ቀይሮ የገባው ዳዊት ፈቃዱም ቢሆን የበረከትን ሌጋሲ ለማስቀጠል እንጅ የክለቡን የግብ ችግር መቅረፍ ሳይችል ቀርቷል ያገኘውን የግብ እድልም ከግቡ መረብ ላይ ማሳረፍ ተስኖት ታይቷል። ደደቢት ይህን ያህል ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ እያደረገ ባለበትና ኢትዮጵያ ቡና ዳዊት እስጠጀፋኖስን በጉዳት ባጣበት ሰዓት በ67ኛው ደቂቃ ቢኒያም አሰፋ የክለቡን አሸናፊነት ያረጋገጠች ግብ አስቆጠረ። ከዚህች ግብ በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት ቡናዎች ተጨማሪ የግብ እድል ለማግኘት ወደ ደደቢ የግብ ክልል በቀረቡበት ሰዓት አጥቂው አስቻለው ግርማ ተጠልፎ ወድቆ የነበረ ቢሆንም የእለቱ ዳኛ ግን ፍጹም ቅጣት ምት ሳይሰጡ ቀርተዋል። 

 መስዑድ መሃመድን በጉዳት ጥላሁን ወልዴን በቅጣት ማሰለፍ ያልቻለው ኢትዮጵያ ቡና በትናንቱ ጨዋታም ዳዊት እስጢፋኖስን በጉዳት አጥቷል። ቡናማዎቹ በእለቱ ዳዊትን በጉዳት ቢያጡም ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝተው በመውጣታቸው ፕሪሚየር ሊጉን ከመብራት እኩል በግብ ክፍያ ተበልጠው ሁለተኛ ላይ እንዲቀመጡበት አስችሏቸዋል። 

መብራት ሃይል በስድስት ጨዋታ አንድም ጊዜ ያልተሸነፈ ብቸኛው የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በተከታታይ አራት ጨዋታ በማሸነፍ ብቸኛው ክለብ ሆኗል። ደደቢት እስካሁን ያደረጋቸውን ስድስት ጨዋታዎች በሙሉ አዲስ አበባ ላይ ያደረገ በመሆኑ ከቤቱ ያልወጣ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል። የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኖሜ ስድስት ግቦችን አግብቶ ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ሲሆን ቢኒያም አሰፋ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና በአምስት ግቦች ደረስኩብህ እያለው ይገኛል። 

ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬም በአዲስ አበባ ሁለት ጨዋታዎችን በክልል ደግሞ ሶስት ጨዋታዎችን ያካሂዳል። አዲስ አበባ ላይ ከአመሻሹ 11፡30 የሚካሄደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ትኩረት ተሰጥቶታል። ይርጋለም ላይ በሲዳማ ቡና እና በአዳማ ከነማ መካከል የሚካሄደው ጨዋታም ሲዳማን ወደ መሪነቱ ስለሚመልሰው አዳማን ደግሞ ከአደጋው ክልል ስለሚያወጣው ጨዋታው በጉጉት ይጠበቃል። 

ዘጋቢ፦ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!