የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ 47 ሚሊዮን ብር ባጀት በማጽደቅ ተጠናቀቀ
ታህሳስ 06, 2014

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከትናንት በስቲያ ታህሳስ 4/2007 ዓ.ም አራተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በአዲስ አበባ ሐርመኒ ሆቴል አካሂዷል። በጠቅላላ ጉባኤው በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ለውውይት የቀረቡ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችም ከሰብሳቢዎች መልስ ተሰጥቷቸዋል። 

የፌዴሬሽኑ የ2006 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በፌዴሬሽኑ ዋና ፀሃፊ አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት በሙሉ ድምጽ ጸድቋል። አቶ ዘሪሁን ፌዴሬሽኑን በዘመናዊ አደረጃጀት ለማዋቀር እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸው የአምስት ዓመት የሥራ እቅድ ፕላን ተሰርቶ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል። የክለቦችን አደረጃጀት በተመለከተም ከካፍ በተወሰደ የክለቦች ስታንዳርድ መሠረት የክለቦችን ደረጃ የማውጣት ሥራ ተሰርቶ በዚህ ዓመት በአህጉራዊ ውድድር የሚሳተፉት ቅዱስ ጊዮርጊስና ደደቢት የመጀመሪያዎቹ የካፍን ስታንዳርድ የያዙ ክለቦች ሆነው ተመዝግበዋል ሲሉ በሪፖርታቸው ገልጸዋል። 

 የፌዴሬሽኑ ያለፈው በጀት ዓመት የፋይናንስ ሪፖርት በውጭ ኦዲተርና በፌዴሬሽኑ የፋይናንስ ኦዲተር የቀረበ ሲሆን ፌዴሬሽኑም የገቢ አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት ተገልጿል። በውጭ ኦዲተር የቀረበው የፋይናንስ ሪፖርት እንደሚገልጸው ፌዴሬሽኑ ባለፈው የውድድር ዓመት 54 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ይገልጻል። ነገር ግን ወጭው ከገቢው የበለጠ ሲሆን ለዚህም የቀረበው ምክንያት ፌዴሬሽኑ የገቢ ማሳደጊያ ሥራዎችን በስፋት ባለመስራቱ እና በርካታ የውድድር ፎርማቶችን ቀርጾ በውድድር በርካታ ገንዘብ ማውጣቱ ናቸው። በተለይም ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተዋቅሮ ለውድድር መቅረቡ የፌዴሬሽኑን ውድድሮችን የማስፋት ሥራ መስራቱን ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም የዋናው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ወርሃዊ ደመወዝም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወጪ እንዲጨምር ምክንያት ተደርጎ ቀርቧል። 

በርካታ ክለቦች “ዓመቱን ሙሉ ስንወዳደር ከርመን ከስታዲየም መግቢያ ቲኬት የምናገኘው ገቢ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም” እያሉ ቅሬታ የሚያሰሙበት የስታዲየም ገቢ ለፌዴሬሽኑ ግን ጠንካራ የፋይናንስ ምጭ ሆኖ በሪፖርቱ ቀርቧል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአዲስ አበባ ስታዲየም ከሚካሄዱ ጨዋታዎች ከሚገኝ የስታዲየም ገቢ ውስጥ 32 ከመቶ ብቻ የሚቆርጥ ቢሆንም በኦዲት ሪፖርቱ የቀረበው ግን በዓመት ውስጥ ከስታዲየም መግቢያ ቲኬት ሽያጭ ያገኘው ገንዘብ ብዛት 13.5 ሚሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከናይጀሪያ ጋር ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እና ከሩዋንዳ ጋር ደግሞ ለቻን ዋንጫ ማጣሪያ ሲጫወት ያገኘው ገቢ ሙሉ በሙሉ የግሉ መሆኑ ገቢውን ከፍ እንዳደረገለት ይታሰባል። 

ከዚህ በተጨማሪ የፌዴሬሽኑ የገቢ ምንጮች ሆነው የተገለጹት ከበደሌ ቢራ ጋር ባለው የስፖንሰር ስምምነት የሚገኘው 10.5 ሚሊዮን ብር፣ ከካፍ በእርዳታ የተገኘ 14.6 ሚሊዮን ብር እና ከፊፋ በድጋፍ የተገኘው 4.8 ሚሊዮን ብር ዋናዋናዎቹ ሲሆኑ በፌዴሬሽኑ ማርኬቲንግ ዲፓርትመንት የተገኘው ግን 4.6 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው። 

ከጠቅላላ ጉባኤው ተካፋዮች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበው መልስ ተሰጥቶባቸዋል። በተለይ ፌዴሬሽኑ የአደረጃጀት ችግር አለበት፣ የክለቦችና የብሔራዊ ቡድን የስነ ምግባር መከታተያ ደንብ የለውም እና የአምቦ ፊፋ ጎል ፕሮጀክት ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል የሚሉ ይገኙበታል። ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ የሰጡት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ ፌዴሬሽኑ ያለበትን የአደረጃጀት ችግር ለመቅረፍ ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው የተጫዋቾች ስነ ምግባር መከታተያ ደንብ ለመቅረጽ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል። የአምቦ ፊፋ ጎል ፕሮጀክት ያለበትን ደረጃም አሁን በሥራ ላይ መሆኑን ተናግረዋል። 

ከዚህ በተጨማሪም የዋናው ብሔራዊ ቡድን መጠሪያ ቅጽል ስሙ “ዋልያ” ሲሆን ይህንን ስም በንግድ ምልክትነት የሚጠቀመው ዋልያ ቢራ ከፌዴሬሽኑ ጋር ምን አይነት ስምምነት ተደርሶ ነው የብሔራዊ ቡድኑን ስያሜ የሚጠቀመው ይህ ስህተት አይደለም ወይ ሲሉ የቀድሞው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሣህሉ ገብረወልድ ጠይቀው ነበር። ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጡት የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተክለወይን “ፌዴሬሽኑ የምስል ባለቤትነት ማረጋገጫ የለውም ይህ በመሆኑ ማንንም መክሰስና የባለቤትነት ጥያቄ ማቅረብ አንችልም። ይህ ደግሞ አሁን ብቻ ሳይሆን ከዓመታት በፊትም በርካታ የብሔራዊ ቡድን ማሊያ ሲሸጥ ፌዴሬሽኑ ምንም ገቢ ያላገኘው የባለቤትነት ማረጋገጫ ስላልነበረው ነው። ወደ ፊት ግን ስያሜውን በብቸኛ ባለቤትነት ለመጠቀም ምዝገባ ለማድረግ ጥያቄ አቅርበናል” ብለዋል። 

አቶ ሣህሉ ገብረወልድ የዋልያ ቢራን አነሱ እንጅ እሳቸው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ሉሲ ኢንሹራንስ የሴቶችን ብሔራዊ ቡድን ስያሜ ሲጠቀም እንዲሁም ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፉ የተነቃቃው የአገሪቱ ህዝብ በርካታ የብሔራዊ ቡድን ማሊያዎችን ሲገበያይ ጥያቄ አላነሱም ነበር። 
በመጨረሻም ለ2007 ዓ.ም 47 ሚሊዮን ብር በማጽደቅ ጉባኤው ፍጻሜ አግኝቷል። 

ዘጋቢ፦ ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
SHAMBEL [1163 days ago.]
 YISHASHAL

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!