የተጫዋቾች ዝውውር ለክለቦች ወይስ ለተጫዋቾች ጥቅም?
ታህሳስ 08, 2007

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዙሪያ ቅርበት አለን የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች በተደጋጋሚ የሚናገሩት አንድ የጋራ አስተያየት አለ “ለእግር ኳሱ እድገት ማነቆ የሆነው የተጫዋቾች የዝውውር ፖሊሲ ነው” የሚል። 

ለዚህ አስተያየታቸው የሚያቀርቡት አመክንዮ ደግሞ የሚከተለው ነው።ክለቦች በርካታ ገንዘቦችን አውጥተው ተጫዋቾችን ያሳድጋሉ። ተጫዋቾች ደግሞ ለአቅመ ክፍያና ለስታዲየም ብቁ ሲሆኑ ከአደጉበት ክለብ ማዶ ያለውን ሰፈር መቃኘት ይሻሉ። በዚህ ጊዜ ከዐይን የፈጠኑ ደላሎች “እንትና ለሚባለው ክለብ ከፈረምክ ለፊርማ ብቻ እስከ 800 ሺህ ብር ትዝቃለህ። ግዴለህም እመነኝ ለዚያ ክለብ ለአንተ የሚስማማ አጨዋወትና ምርጥ አሰልጣኝ አለ” እያሉ ተጫዋቾቹ ልባቸው እንዲሸፍት ያደርጓቸዋል። ተጫዋቾቹ የእነደልዬን አንደበት አምነው ለተባለው ክለብ ሲፈርሙ ተጫዋቾቹን ላዘዋወሩበት ሥራቸው መጠኑ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ወደ ኪሳቸው ያስገባሉ።

ተጫዋቾችን ከክለብ ክለብ በደላላነት በማዘዋወር ሂደት ውስጥ ጋዜጠኞች፣ አሠልጣኞችና የክለብ ሥራ አስኪያጆች እጃቸውን ያስገባሉ። እንደዚህ ባለው የጥቅማ ጥቅም ገመድ የታሰረ ግንኙነት እግር ኳሱን እሾህ ላይ የተዘራ ሰብል እንዲሆን አድርጎታል ተብሎ ይታማል። “በዝውውሩ ጉዳይ እግር ኳሱ በሁለት መንገድ ይጎዳል” የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች በአንድ በኩል ክለቦች ተጫዋቾችን አሳድገው ቤሳቢስቲን ሳያገኙ ለሌላ ተቀናቃኝ ክለብ ማቅረባቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ተጫዋቾች የፊርማ ክፍያ ከተከፈላቸው በኋላ የሚኖራቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑ ናቸው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው ቅዳሜ አራተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ባደረገበት ወቅት ከጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የሆነውም ይህ ጉዳይ ነበር። በወቅቱ ሃሳቡን በአጀንዳ እንዲያዝ አስተያየት ያቀረቡት የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የቦርድ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ “የክለቦች ራስ ምታት የሆነው የተጫዋቾች ዝውውር ጉዳይ በፌዴሬሽኑ ትኩረት እንዲሰጠው ክለባችን ጥያቄ ያቀርባል” ብለው ነበር። 

ሰሞኑን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ፌዴሬሽኑ የተጫዋቾች ዝውውር መመሪያ ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ መመሪያውን ሲያዘጋጅ የተጫዋቾችንና የክለቦችን ጥቅም ታሳቢ አድርጎ መሆን እንዳለበት ለእግር ኳስ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ይናገራሉ።

ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም “ክለቦች ብዙ ገንዘብ ከፍለው ከተጫዋቾቹ የሚፈልጉትን ያህል አገልግሎት አለማግኘታቸው በመጠኑም ቢሆን ይቀረፍላቸዋል ነገር ግን ተጫዋቾችስ ዝውውሩ ከተፈጸመ በኋላ የጤና እክል ቢገጥማቸው፣ ቅጣትና ጉዳት ቢያስተናግዱ ዋስትናቸው ምን ሊሆን ይችላል?” ሲሉ ይጠይቃሉ። 

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን አካላት አነጋግሮ በቀጣዮቹ ቀናት ሰፋ ያለ መረጃ ይዞ ይመለሳል።  

ዘጋቢ፦ ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!