ሦስት ደርቢዎችን የሚያስተናግደው ስምንተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ
ታህሳስ 12, 2007

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሰባት ጨዋታዎችን በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ያካሂዳል። የፕሪሚየር ሊጉ መሪ መከላከያ ወደ ደቡብ አቅንቶ በተከታታይ እያሸነፈ የመጣውን ወላይታ ድቻን ይገጥማል። መከላከያ ያለፉትን ሰባት ጨዋታዎች ሳይሸነፍ የተጓዘ ሲሆን ወላይታ ድቻ በበኩሉ በደደቢት ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ የሽንፈትን መራራ ጽዋ አልተጎነጨም። በዚህም ምክንያት የዛሬውን ጨዋታ አጓጊ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።

AA Football Spectators

 
እንደ መከላከያ ሁሉ በዚህ ዓመት አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ የተጓዘው የአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ቡድን መብራት ኃይል ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ተጉዞ አርባምንጭ ከነማን የሚገጥም ይሆናል። ባለፈው ሳምንት መብራት ሀይል በሜዳው ከዳሽን ቢራ ጋር ባደረገው ጨዋታ ነጥብ ተጋርቶ ከመውጣት የታደገው አንጋፋው አጥቂ ዮርዳኖስ አባይ መሆኑ ይታወሳል። አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙም “ዮርዳኖስ ገና ወደ ሙሉ ፊትነሱ ስላልተመለሰ በዛሬው ጨዋታም ተቀያሪ ሆኖ ይጀምራል። ቡድናችን ውስጥ የተጎዳም ሆነ የተቀጣ ተጫዋች ስለሌለ ጨዋታውን በድል ለመወጣት ተዘጋጅተናል።” ሲሉ ለኢትዮ ፉት ቦል ዶት ኮም በስልክ ተናግረዋል። 
በበርካታ የሃዋሳ ከተማና አካባቢ ነዋሪዎች በጉጉት የሚጠበቀው የሃዋሳ ከነማና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ዛሬ በሀዋሳ ስታዲየም ይካሄዳል። ሁለቱ ክለቦች በአንድ ክልልና ዞን የሚገኙ በመሆናቸው ከፍተኛ ፉክክርና የአልሸነፍ ባይነት የሚታይበት ጨዋታ በመሆኑ ጨዋታው አጓጊ ነው። የዘላለም ሽፈራው ሞሪንሆ ቡድን ሲዳማ ቡና 11 ነጥቦችን ሰብስቦ ከመሪው መከላከያ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በታረቀኝ አሠፋ ዳኘ የሚሰለጥነው ሃዋሳ ከነማ በበኩሉ ወልድያን በሶስት ነጥብ ብቻ በልጦ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

አዳማ ላይ አዳማ ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናግዳል። ሁለቱ ክለቦች ተቀራራቢ ነጥብ ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ የቆየ የተፎካካሪነት ታሪካቸው የዛሬውን ጨዋታም በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አምበሉ ዳዊት እስጢፋኖስ በጉዳት እንደማይሰለፍ አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ ለዝግጅት ክፍላችን የገለጸ ሲሆን መስዑድ መሃመድም ተጠባባቂ ሆኖ ጨዋታውን እንደሚጀምር ተናግሯል። በዚህም ምክንያት ክለቡን በአምበልነት እየመራ የሚገባው ወጣቱ አማካይ ጋቶች ፓኖም ይሆናል ሲል ተናግሯል። የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ለመከታተል በርካታ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ወደ ስፍራው አቅንተዋል። የጸጥታ ችግር እንዳይከሰትም ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስተያየት ሰጭዎች ለኢትዮ ፉት ቦል ዶት ኮም ተናግረዋል። 

በሌላ የክልል ጨዋታ ወልድያ ላይ ወልድያና ዳሽን ቢራ የሚያደርጉት የአማራ ደርቢ ይገኝበታል። ወልድያ አጀማመሩን ያላሳመረ ሲሆን ዳሽን ቢራ በበኩሉ ካለፈው ዓመት በተሻለ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ሁለቱ የአማራ ክልል ክለቦች ከዚህ ቀደም ተገናኝተው የማያውቁ ሲሆን የዛሬው ግንኙነታቸውም በታሪካቸው የመጀመሪያ ይሆናል ተብሏል። አጀማመሩን አክፍቶ ራሱን አደጋ ላይ የጣለው ወልድያ አሰልጣኙን አሰናብቷል። 

አዲስ አበባ ላይ ፈረሰኞቹ ሙገር ሲሚነቶን በአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናግዳሉ። በተደጋጋሚ ወሳኝ ነጥቦችን እየጣሉ በመሆናቸው ቁጭት ላይ ያሉት ፈረሰኞቹ በዛሬው ጨዋታ ወደ አሸናፊነት ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሙገር ሲሚንቶ ያለፈውን ሳምንት በሜዳውና በደጋፊው ፊት በአርባ ምንጭ ከነማ አንድ ለባዶ የተሸነፈ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አንድ ለአንድ መለያየቱ ይታወሳል። 

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው በአዲስ አበባ ደርቢ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ደደቢት የሚያደርጉት ጨዋታ ነው። ደደቢት ያለፉትን ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች በመሸነፉ አሰልጣኙን አሰናብቶ አዲስ አሰልጣኝ መቅጠሩ ይታወሳል። አዲሱ የደደቢት አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሣህሌም ዛሬ ከአዲሱ ክለባቸው ጋር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ማለት ነው። የደደቢቱ አሰልጣኝ አጀማመራቸውን ለማሳመር የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ጸጋዬ ኪዳነ ማሪያም ደግሞ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ ጨዋታው በጉጉት ይጠበቃል። በዚያ ሁለቱ ክለቦች ያላቸው የነጥብ ልዩነት ሁለት ብቻ ሲሆን ንግድ ባንክ ደግሞ በዓመቱ ካካሄዳቸው ሰባት ጨዋታዎች ያሸነፈው አንዱን ብቻ በመሆኑ በዛሬው ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ቆርጦ መነሳቱን ለክለቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል።  

ፕሪሚየር ሊጉን መከላከያ በ13 ነጥብ ሲመራ ስሙን ያስቀየረው የድሮው መብራት ሀይል የአሁኑ ኤሌክትሪክ ክለብ በ12 ሁለተኛ ኢትዮጵያ ቡና ከኤሌክትሪክ እኩል 12 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ወልድያ በሁለት ነጠብ፣ እኩል አምስት ነጥብ ያላቸው ሀዋሳ ከነማና ሙገር ሲሚንቶ ከ12 እስከ 14ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ሣሙኤል ሳኑሜ ከደደቢት በስድስት ቢኒያም አሰፋ ከቡና በአምስት ግቦች የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ደረጃ ይዘዋል። የደደቢቱ ንጉሴ ደስታና የወልድያው ንጉሴ ዓለሙ በጊዜ የተሰናበቱ አሰልጣኞች ናቸው።

ደደቢትና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚያካሂዱት ጨዋታ ውጭ ሌሎቹ ጨዋታዎች የሚካሄዱት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ነው። የደደቢትና የባንክ ጨዋታ ግን ከአመሻሹ 11፡30 ላይ ይሆናል። 

ዘጋቢ: ይርጋ አበበ 
ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!