በፕሪሚየር ሊጉ ስምንተኛ ሳምንት ሲዳማ ቡና መሪነቱን ሲረከብ ወልዲያ የመጀመሪ ድሉን አጣጣመ ኤልፓም ያለመሸነፍ ሪከርዱን እንደጠበቀ ቀጥሏል
ታህሳስ 13, 2007

  • መከላከያ የዓመቱን የመጀመሪያ ሽንፈት አስተናገደ
  • ወልድያ ከሦስት ነጥብ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኘ
  • ፈረሰኞቹ ወደ አሸናፊነታቸው ተመለሱ
  • አዳማ ከነማ በሜዳው ያለመሸነፍ ሪከርዱን አስጠብቆ ሲወጣ ቡና አንድ      ነጥብና 48 ሺህ ብር ከአዳማ ይዞ ተመልሷል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከተደረጉ ሰባት ጨዋታዎች ሦስቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። 

አደዲስ አበባ ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በቅድሚያ ዘጠኝ ሰአት ላይ የተገናኙት የአምናው ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስና ሙገር ሲሚንቶ ነበሩ። ጊዮርጊሶች አዳነ ግርማን ከፊት ዋና አጥቂ አድርገው ለ90 ደቂቃ ባሰለፉበት ጨዋታ ከመጀመሪያዋ ደቂቃ አንስቶ አጥቅተው ተጫውተዋል። በተደጋጋሚ የሙገርን በር ሲያስጨንቁ የቆዩት ጊዮርጊሶች ከበርካታ የጎል ሙከራዎች በኋላ በጨዋታው የመጀመሪያ ጐላቸውን ማስቆጠር የቻሉት የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 2ት ደቂቃ ሲቀረው በአዳነ ግርማ አማካኝነት ነበር። 
Adnae Attempt on Goalበአብዛኛው በወጣት ተጫዋቾች የተገነባው ሙገር  በሁለተኛው አጋማሽ እስከመጨረሻው ያልዘለቀ ቢሆንም የመከላከል አጨዋወቱን አሻሽሎ ወደ ጐል ለመቅረብ ባደረገው ጥረት ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎችም ቢሆን በሁለቱም በኩል ፉክክር የታየበት እንዲሆን አድርጎት ነበር።  ካለፉት ጨዋታዎቻቸው ውጤት ጥሩ ያለመሆን ብዙ የተማሩ የሚመስሉት ጊዮርጊሶች   የማጥቃት ዘመቻቸውን እስከመጨረሻው አጠናክረው ቀጥለው ምንተስኖት አዳነ በ85ኛው ደቂቃ ላይ በአየር የተሻገረለትን ኳስ በጭንቅላት በመግጨት ካስቆጠራት ሁለተኛዋ ጐል በተጨማሪ ሁለት ጐል ማስቆጠር ችለው ነበር። ሁለቱ ጐሎች በዳኛው ከጫወታ ውጪ በሚል ውሳኔ ተሽረውባቸዋል። 

Stgeorge Vs Muger


የአምና ሻምፒዮኖቹ  ጊዮርጊሶች ደጋፊው በሚጠብቃቸው የበፊት ብቃት ላይ ባይደርሱም በትላንትናው ጨዋታ ከፍተኛ ለውጥና መሻሻልን  በማሳየት በስታዲየሙ የታደሙትን ደጋፊዎቻቸውን አስደስተዋል።

በሁለተኛው ጨዋታ የተገናኙት ደደቢትና ንግድ ባንክ ያደረጉት ጨዋታ ፍጹም ተመጣጣኝ ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ጥሩ የኳስ ፍሰት የታየበትና  በርካታ የግብ ሙከራዎች በሁለቱም ቡድኖች የተደረገበት ጨዋታ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታው በተጀመረ በ21ኛው ደቂቃ ላይ  ደደቢቶች በጥሩ ጨዋታ ጐል ሊሆን የሚችል ኳስ ለግብ አዳኙ ለሳሙኤል ሳኑሚ ቢያመቻቹለትም ኳስ ከመረብ ማገናኘት አቅቶት  ለበረኛው አስታቅፎታል። 31ኛው ደቂቃ ላይ ሌላው የንግድ ባንኩ ግብ አዳኝ ፊሊፕ ዳውዝ ንግድ ባንኮችን ቀዳሚ ልታደርግ የምትችል ጐል አግብቶ ዳኛው ከጨዋታ ውጪ ብለው ሽረውበታል። 

Dedebit vs CBE


ጨዋታው በጥሩ ፉክክር ቀጥሎ በመጨረሻዎቹ 7ት የመጀመሪያው አጋማሽ ቀሪ ደቂቃዎች ውስጥ ከአምስት ያላነሱ የግብ ሙከራዎች በሁለቱም ወገን ተደርጓል። በ38ኛው ደቂቃ ፊለፕ ዳውዝ በግቡ አናት የወጣችበት ኳስ፣ እነዲሁም በ43ኛውና በ45ኛው ደቂቃ ላይ ደደቢቶች ያደረጓቸው ጐል ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ ሙከራዎች የመጀመሪያውን አጋማሽ ጨዋታ የበለጠ አጓጊ እንዲሆን ያደረጉ ክስተቶች  ነበር። 

Dedebit vs CBE


በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው የበለጠ የፈጠነበትና በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተደጋጋሚ የጐል ሙከራ የተደረገበት ነበር።  ባንኮች በ60ኛው ደቂቃ ላይ ከመሃል ኳስ አንድ ሁለት ተቀባብለው ወደ ጐል በቀጥታ የተመታች ኳስ የደደቢቱ በረኛ ተወርውሮ  ወደ ጐሉ አናት ባያወጣት ኖሮ ምን አልባት የፕሪሚየር ሊጉ ድንቅ  ጐል ሆና ልትመዘገብ ትችል ነበር።  በ62ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ደደቢቶች  በድንባር በመግጨት ወደ ጐል የሞከሩት ኳስ  በበረኛው ተመልሶባቸዋል። ጨዋታው ተጋግሎ በቆየበት ሁኔታ በ78ኛው ደቂቃ ላይ የባንኩ ኤፍሬም አሻሞ በክንፍ በኩል ወደ ጐል አንድ ተጫዋች አታሎ ቢገባም ወደ ጐል የመታት ኳስ በደደቢት ተከላካዮች ብሎክ ተደርጐበታል። ጨዋታው 0ለ0 ያለ ግብ ከመጠናቀቁ በፊት ደደቢቶች በ83ኛውና በ85ኛው እንዲሁም ንግድ ባንኮች በ86ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ጥሩ የጐል ሙከራዎችን አድርገው ነበር። 

ንግድ ባንክና ሦስት ነጥብ ከተራራቁ ስምንተኛ ሳምንታቸውን ይዘዋል። ባንክ ለመጨረሻ ጊዜ ሙሉ ሶስት ነጥብ ያገኘው በፕሪሚየር ሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ሁለት ለባዶ ሲያሸንፍ ነው። ከዚያ ጨዋታ በኋላ ያደረጋቸውን ሰባት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲሸነፍ በአምስቱ ደግሞ አቻ ወጥቷል። ደደቢት በበኩሉ ከተከታታይ ሦስት ጨዋታ ሽንፈት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ነጥብ ይዞ የወጣው ከንግድ ባንክ ሆኗል። 

ክልል ላይ ከተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች አስገራሚ ውጤት የተመዘገበው ወልድያ ላይ ነው። ወልድያ “ማሸነፍ የተሳነው” እየተባለ እየተተቸ ባለበት ሰዓት በሜዳው ዳሽን ቢራን አስተናግዶ አንድ ለባዶ በማሸነፍ ከሰባት ጨዋታ በኋላ የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ችሏል።  አርባምንጭ ላይ ኤሌክትሪክ ክለብ በዮርዳኖስ አባይ ግብ አንድ ነጥብ ይዞ ተመልሷል። ኤሌክትሪክ በሰባት ጨዋታ ሳይሸነፍ በመጓዝ ብቸኛው ክለብ ሲሆን የኤሌክትሪክን ታሪክ ይጋራ የነበረው መከላከያ በወላይታ ድቻ ተሸንፎ ተመልስል። መከላከያ በመሸነፉ ደረጃውን ወደ አራተኛ ዝቅ አድርጓል። 

ሲዳማ ቡና የዘወትር ተቀናቃኙን ሃዋሳ ከነማን ሁለት ለአንድ አሸንፏል። ሃዋሳ በሜዳውና በበርካታ ደጋፊው ፊት መሸነፉ ደጋፊዎችን ያስቆጣ ሆኗል። 
እጅግ በርካታ ደጋፊ የተከታተለውና ስድስት ግብ የተቆጠረበት የአዳማ ከነማና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ሦስት እኩል በሆነ ውጤት ተጠናቋል። አዳማ ከአዲስ አበባ ያላት ርቀት 99 ኪሎ ሜትር ብቻ መሆኑነ ተከትሎ በርካታ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ቡድናቸውን ሊያበረታቱ ወደ ስፍራው መጓዛቸውና አዳማ ከነማም ባለፈው ሳምንት ሲዳማ ቡናን በማሸነፉ የተነቃቁት የክለቡ ደጋፊዎች ስታዲየሙን ሞልተውት ነበር። የአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከአፍ እስከ ገደፉ በተመልካች ተጨናንቆ ዛፎችና ግንባታዎች ለተመልካች መቀመጫ ሆነው ባመሹበት ጨዋታ አዳማ ከነማ በሜዳው ያለመሸነፍ ሪከርዱን አስጠብቆ መውጣት ችሏል።

ወጣቱ ታከለ አለማየሁ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ያስቆጠራት የመጀመሪያ ግብ አዳማዎችን ስታነቃቃ ቡናዎችን ደግሞ አስደንግጣለች። ከታከለ ግብ ሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ አንጋፋው በረከት አዲሱ የቡና ተከላካዮችና ግብ ጠባቂ የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ቡድኑን ሁለት ለባዶ መሪ እንዲሆን አስቻለ። ከዚህች ግብ በኋላም አዳማ ከነማዎች በበረከት አዲሱና ታከለ አለማየሁ ሁለት ጊዜ ለግብ የቀረቡ እድሎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። በአጭር ደቂቃዎች ልዩነት ተከታታይ ግብ ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና እስከ 27ኛው ደቂቃ የሚይዘው የሚጨብጠው ጠፍቶት ነበር የታየው። በ27ኛው ደቂቃ ኤሊያስ ማሞ ለቡድኑ ተስፋ የሰጠች ግብ አስቆጥሮ ክለቡን ማረጋጋት ችሏል። ከኤሊያስ ግብ በኋላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለግብ የቀረቡ እድሎች የተፈጠሩ ቢሆንም ከመረብ ማሳረፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። ለኤሊያስ ማሞ ግብ የዴቪድ በሻህ የተስተካከከ ክሮስ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ቢሆንም የአዳማ ከነማው ግብ ጠባቂ የሰራው ስህተት ግን ጉልህ ድርሻ ይኖራታል። 

ከእረፍት መልስ ተደጋጋሚ ስህተት ሲሰራ የነበረውን ተከላካዩን ዴቪድ በሻህን በሮቤል ግርማ ቀይሮ የገባው ኢትዮጵያ ቡና በመስመር አጥቂው አስቻለው ግርማ አማካኝነት አቻ መሆን ቻለ። አስቻለው ግርማ ከእረፍት በፊት ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን ፈጥሮ የነበረ ሲሆን ከእረፍት መልስ ደግሞ ያለው ተፈጥሯዊ ፍጥነት ለአዳማ ተከላካዮች ራስ ምታት ሆኖ ነበር። ያስቆጠራት ግብም የግል ፍጥነቱን ተጠቅሞ እና በእለቱ ለኢትዮጵያ ቡና ባለ ውለታ ሆኖ ያመሸውን የአዳማ ከነማውን ግብ ጠባቂ ስህተት ተጠቅሞ ነው። 

ጨዋታው በዚህ ውጤት ሊጠናቀቅ እየተቃረበ ባለበት ሰዓት የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ኔልሰን የግቡን መስመር ለቆ መወጣቱን የተመለከተው የአዳማ ከነማው አጥቂ ከርቀት አክርሮ የመታት ኳስ ማረፊያዋን በቡናዎች መረብ ላይ አደረገች። ውጤት አስጠብቆ ለመውጣት ጉጉት ያደረባቸው የአዳማ ከነማ ተጫዋቾች የሰሩትን ቴክኒካል ስህተት ተጠቅሞ ወደ ግብ ክልል የቀረበው ቢኒያም አሰፋ ቡድኑን ከመሸነፍ የታደገች ግብ አስቆጠረ። የቢኒያም ግብ ኢትዮጵያ ቡናን ስታስደስት አዳማ ከነማዎችን ደግሞ በደስታቸው ላይ ውሃ የቸለሰች ነበረች። 

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ተከላካዮቹ ዴቪድ በሻህና ሚሊዮን ወንድሙ እንዲሁም አማካዮቹ ጋቶች ፓኖምና ደረጀ ሀይሉ የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ ሲመለከቱ በአዳማ ከነማ በኩል አጥቂዎቹን በረከት አዲሱንና ታከለ አለማየሁን ጨምሮ በድምሩ ስምንት ተጫዋቾች የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ የተመለከቱ ተጫዋቾች ሆነዋል። አዳማ ከነማ በአንድ ጨዋታ በርካታ ቢጫ ካርዲችን በማስተናገዱ ከፌዴሬሽኑ የገንዘብ ቅጣት ይጠብቀዋል። በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና አማካዩን ጥላሁን ወልዴን በጉዳት ያጣ በመሆኑ የክለቡን የጉዳተኛ ተጫዋቾች ብዛት ከፍ አድርጎበታል። አዳማ ከነማ በበኩሉ ኮከቡን ወጣት አጥቂውን ታከለ አለማየሁን በጉዳት ሊያጣ ተገድዷል። 

Coffee supporters at Adama


ኢትዮጵያ ቡና አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ካስቻሉት ሦስት ግቦች አንዷን ያስቆጠረው ቢኒያም አሰፋ በስድስት ግብ ከሳሙኤል ሳኑሜ እኩል የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን እንዲመራ አስችሎታል። ቡና ያስቆጠራቸው ሶስቱም ግቦች የአዳማ ከነማው ግብ ጠባቂ ስህተቶች የሰጡት ስጦታዎች ናቸው። በአገሪቱ ውስጥ ጠንካራ ግብ ጠባቂ የለም እየተባለ በሚተችበት በዚህ ወቅት የአዳማ ከነማው ግብ ጠባቂ ለግብ ጠባቂዎች ደረጃ መውረድ አንዱ ማሳያ ሆኗል። 

ከጨዋታው አንድ ነጥብ ያገኘው አዳማ ከነማ ነጥቡን አስር በማድረስ ከደደቢት ጋር እኩል ሲሆን ከዳሽን ቢራ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሀዋሳ ከነማ በላይ መሆን ችሏል። ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ሜዳ ላይ ባገኛት አንድ ነጥብ የነበረበትን ደረጃ ሲያስጠብቅ ከሜዳ ውጭ ደግሞ በከተማው ባዘጋጀው አነስተኛ ባዛር ከቁሳቁስ ሽያጭ 48 ሺህ ብር ማግኘቱን ከክለቡ የደረሰን መረጃ ያመለክታል። 

ክለቦች ራሳቸውን በገቢ ለማሳደግ የክለባቸውን መገለጫ የሆኑ ቁሳቁሶችን በመሸጥ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነገር ቆይቷል። በዚህ በኩል በርካታ ደጋፊ ያላቸው እንደ ኢትዮጵያ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና ወላይታ ድቻ መስራት የሚገባቸውን ያህል ቢሰሩ ኖሮ የክለባቸውን ካዝና በገንዘብ ባጨናነቁት ነበር። ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ላይ ራሱን በከተማው ከሚኖሩ ደጋፊዎች ጋር ካስተዋወቀ በኋላ የአሁኑ የኢትዮጵያ ቡና እንቅስቃሴ በሌሎች ክለቦችም ሊደገም የሚገባው ሆኖ አይተነዋል። ፈረሰኞቹ አዳማ ላይ በቁሳቁስ ሽያጭ ምን ያህል ገቢ እንዳገኙ መረጃው ባይኖረንም ኢትዮጵያ ቡና በሁለት ቀን ባደረገው ሽያጭ 48 ሺህ ብር ማግኘቱ ሌሎቸ ክለቦችም መንገዱን እንዲከተሉት የሚያስገድድ ነው ማለት ይቻላል። 

ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!