ፕሪሚየር ሊጉ ዘጠነኛ ሳምንት ቅድመ ጨዋታ ዘገባ
ታህሳስ 17, 2007


የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነገና እሁድ በአራት የተለያዩ ከተሞች ይካሄዳል። ሊጉ ነገ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘውን ሃዋሳ ከነማን በአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናግዳል። በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከሚጠበቁ አብይ ክስተቶች መካከል በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ ከሚወደዱ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ የቀድሞ ክለቡን በተቃራኒነት የሚፋለም መሆኑ ነው። “ልቤ ያለው ከቡና ጋር ነው” እያለ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚናገረው ግብ አነፍናፊው ታፈሰ ተስፋዬ በአሁኑ ሰዓት ለደቡብ ክልሉ ክለብ የፊት መስመሩን እየመራ ይገኛል። በነገው ጨዋታም ልምዱንና ያለውን የኳስ ችሎታ ተጠቅሞ ለቡና ተከላካዮች ራስ ምታት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ጨዋታ ሌላው የሚጠበቀው የአሁኑ የቡናዎቹ አምበል ዳዊት እስጢፋኖስ ከጉዳት አገግሞ የሚሰለፍ መሆኑ ነው። 

የሳምንቱ ሁለተኛ ጨዋታ የሚካሄደው ደግሞ ከአመሻሹ 11፡30 ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና አዳማ ከነማ የሚያካሂዱት ጨዋታ ነው። ባለፈው ሳምንት ሁለቱም ክለቦች ከተጋጣሚዎቻቸው አንድ አንድ ነጥብ ብቻ ያስመዘገቡ መሆናቸው የነገውን ጨዋታ በአሸናፊነት ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል። በተለይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተደጋጋሚ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ በደጋፊዎች ቅሬታ እየቀረበበት ያለ ክለብ ነው። የአዳማ ከነማው ወጣቱ አጥቂ ታከለ አለማየሁ ባለፈው ሳምንት ክለቡ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወት በደረሰበት ጉዳት በነገው ጨዋታ መሰለፉ አጠራጣሪ ሆኗል። 

የዓመቱን የመጀመሪያ የሽንፈት ጽዋ ባለፈው ሳምንት ቦዲቲ ላይ የተጎነጨው መከላከያ በተቃራኒው የመጀመሪያ ሙሉ ሶስት ነጥብ ባለፈው ሳምንት ያገኘውን ወልድያን ከነገ በስቲያ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይገጥማል። ሁለቱ ክለቦች ያላቸው የነጥብ ልዩነት ሰፊ ቢሆንም ወልድያ ባለፈው ሳምንት ቀምሶ ያጣጣመውን ሙሉ ሶስት ነጥብ በአንድ ሳምንት ላለማጣት መከላከያ ደግሞ በተደጋጋሚ ላለመሸነፍ ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ። በመከላከያ በኩል ጠንካራ ተከላካይና ኮከብ ግብ ጠባቂ ሲኖረው የአጥቂው መስመርም የሚደርሱትን ውስን ኳሶች ከተጋጣሚ መረብ ላይ ለመዶል ወደ ኋላ እንደማይል በተደጋጋሚ አሳይቷል። 

ፈረሰኞቹ እሁድ ከአመሻሹ 11፡30 ላይ መብራት ሀይልንኤሌክትሪክ ክለብን ይገጥማሉ። ቡልጋሪያዊውን አሰልጣኝ ዮርዳን ስታንኮቪችን አሰናብቶ በምትኩ አጥናፉ ዓለሙን ከቀጠረ በኋላ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን የቻለው ኤሌክትሪክ በዚህ ዓመት አንድም ጊዜ አልተሸነፈም። በዚያ ላይ ከውጭ ያዘዋወሩት አጥቂው ፒተር ፕሪሚየር ሊጉን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመላመዱ ክለቡን አንድ ደረጃ ለማሳደግ እየጣረ ሲሆን “የግቡን መስመር ጠንቅቆ ያውቃል” የሚባለው ዮርዳኖስ አባይም ከ11 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግቦችን ማስቆጠር ጀምሯል። 

በፈረሰኞቹ በኩል ደግሞ አዲሱን የውድድር ዓመት ከአዲስ አሰልጣኝና አዲስ ቡድን ጋር የጀመሩ በመሆናቸው አጀማመራቸው የታሰበውን ያህል አልሆነም ነበር። በተለይ ያለፈው ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢና ኮከብ ተጫዋች ኡመድ ኡክሪን እና ኮከቡን ተከላካዩን አበባው ቡጣቆን መሸጡ በቡድኑ ላይ መሳሳት አሳይቷል እየተባለ ሲተች ቆይቶ ነበር። ባለፈው ሳምንት ሙገር ሲሚንቶን ከጨዋታ ብልጫ ጋር በማሸነፉ መነቃቃት አሳይቷል። በእሁዱ ጨዋታም ለመብራት ሀይል ከባድ ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። 

የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በሜዳው ወላይታ ድቻን ያስተናግዳል። በደቡብ ደርቢው ፍልሚያ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት ሲሆን ባለፈው ዓመት ተፈጥሮ የነበረው የደጋፊዎች አምባጓሮ በእሁዱ ጨዋታ እንዳይደገም ትኩረት ሊደረግበት ይገባል። 

አጀማመሩ ያላማረው ሙገር ሲሚንቶ አሰላ ላይ ደደቢትን ያስተናግዳል። በኢንስትራክተር ዮሀንስ ሳህሌ የሚሰለጥኑት ሰማያዊዮቹ በዚህ ዓመት ያካሄዷቸውን ሰባት ጨዋታዎች በሙሉ ያደረጉት በሜዳቸው ነው። እሁድ በአሰላ የሚያካሂዱት ጨዋታም በዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጭ የሚያደርጉት ጨዋታ ይሆናል። የመጀመሪያዎቹን ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች አሸንፎ አጀማመሩን አሳምሮ የነበረው ደደቢት በተከታታይ ሶስት ጨዋታዎችን በመሸነፉ “ለዋንጫ አይፋለምም” ተብሎ እንዱተች አድርጎታል። ሆኖም ባለፈው ሳምንት ከሶስት ጨዋታ ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መረቡን ሳያስደፍር አንድ ነጥብ በማግኘቱ ጥሩ መነሳሳት እያሳየ ይገኛል። 

የጎንደሩ ፋሲለደስ ስታዲየም እሁድ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ የዳሽን ቢራንና የአርባ ምንጭ ከነማን ፍልሚያ ያስተናግዳል። ዳሽን ከተከታታይ ሽንፈቱ ለማገገም አርባ ምንጭ ደግሞ ተከታታይ ድሉን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ፍልሚያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዳሽን ቢራ ከስምንት ጨዋታ ዘጠኝ ነጥብ የያዘ ሲሆን አርባ ምንጭ በበኩሉ በተመሳሳይ ጨዋታ 10 ነጥብ በመያዝ በአንድ ነጥብ ከተጋጣሚው ልቆ ይገኛል። 

ፕሪሚየር ሊጉን 14 ነጥብ የሰበሰበው ሲዳማ ቡና አናት ላይ ሲቀመጥበት አምስት ነጥብ የያዙ ሶስት ክለቦች ወልድያ፣ ሙገርና ሀዋሳ ከነማ ደግሞ ግርጌው ላይ ተኝተውበታል። ሶስት ክለቦች ኤሌክትሪክ፣ ቡናና መከላከያ ደግሞ ተመሳሳይ 13 ነጥብ ሲይዙ ስድስት ክለቦች ዳሽን ቢራ፣ አርባ ምንጭ ከነማ፣ ደደቢት፣ አዳማ ከነማ፣ ወላይታ ድቻና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዘጠኝ እስከ 12 ነጥብ በመሰብሰብ ተቀራራቢ ነጥብ ያላቸው ክለቦች ናቸው። ንግድ ባንክ ደግሞ ሰባት ነጥብ በመያዝ 11ኛ ደረጃን በብቸኝነት ይዞታል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብ ጠባቂ ችግር አለበት እየተባለ የሚተች ቢሆንም ደካማ እየተባሉ በሚተቹት ግብ ጠባቂዎች ላይ እስካሁን በርካታ ግብ ማስቆጠር የቻሉት ሁለት አጥቂዎች ብቻ ናቸው ኢትዮጵያዊው የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ ቢኒያም አሠፋና ናይጄሪያዊው የደደቢት አጥቂ ሳሙኤል ሳኖሜ። ሁለቱም እኩል ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ፍሊፕ ዳውዝ ደግሞ አራት ግቦችን አስቆጥሮ ይከተላቸዋል።  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ በአንድ የውድድር ዓመት በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ዮርዳኖስ አባይ ብቸኛ ነው በ24 ግቦች። ዮርዳኖስ በዚህ የውድድር ዓመትም ካካሄዳቸው ሁለት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን በማስቆጠር “መጣሁ” እያለ ይገኛል። 

ይርጋ አበበ 
ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!