የዘጠነኛ ሳምንት የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ውጤት 1ለ1 ተጠናቀቁ
ታህሳስ 18, 2007

  •  ቢኒያም አሰፋ ኮከብ ግብ አግቢነቱን በብቸኝነት መምራት ጀመረ
  • የዘንድሮው ሊግ ከተጀመረ  ኢትዮጵያ ቡና  በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀመጠ 
  •  ንግድ ባንክ ከሶስት ነጥብ ጋር መገናኘት አልቻለም። እስካሁን ካደረጋቸው   ከ9ኝ ጨዋታዎች 6ቱን አቻ ተለያይቷል።

ትናንት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሁለት ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂደዋል። ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና ከሃዋሳ ከነማ ያደረጉት ጨዋታ በሁለት ግብና በሁለት ቀይ ካርድ ታጅቦ የተጠናቀቀ ጨዋታ ሆኗል። ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም ከጨዋታው በፊት ባወጣው ዜና ቀድሞ እንደገለጸው በሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ታፈሰ ተስፋዬ ለቀድሞ ክለቡ  ተከላካዮች አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጾ ነበር። በእለቱም ገና ጨዋታው በተጀመረ በስድስተኛው ደቂቃ በቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ በማስቆጠር አሁንም ከግብ መስመሩ አለመራቁን አሳይቷል። በጨዋታውም ሙሉ ክፍለ ጊዜ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ታይቷል። 

ኢትዮጵያ ቡና በእንግዳው ቡድን የጨዋታ ብልጫ ተወስዶበት የታየ ሲሆን በተለይ እስከ ሁለተኛው አጋማሽ በነበረው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሃዋሳ ከነማ ሙሉ በሙሉ የጨዋታ የበላይነት ነበረው። ለሃዋሳ ከነማ ሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴና የግብ ብልጫ እንዲወስድ ያስቻለው ሁለቱ ሞክሼዎች ታፈሰ ተስፋዬና ታፈሰ ሰለሞን የነበራቸው ድርሻ ከፍተኛ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ መስዑድ መሃመድን አስወጥተው ጉዳት ላይ የሰነበተውን ዳዊት እስጢፋኖስን ካስገቡ በኋላ የተሻለ መጫወት ችለዋል። በዚህ ክፍለ ጊዜም በተደጋጋሚ የሃዋሳ ከነማን የግብ መስመር መጎብኘት ቢችሉም ያሰቡትን ያህል ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በተለይ አማካዩ ኤሊያስ ማሞ ከ18 ክልል ውጭ አክርሮ የመታትን ኳስ የሃዋሳ ከነማው ግብ ጠባቂ ግብ እንዳትሆን ከፍተኛውን አደራ ተወጥቷል። 

በ86ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዩን ሮቤል ግርማን ተክቶ የገባው ሻኪሩ በሃዋሳ ከነማዎች የግብ ክልል ውስጥ ተጠልፎ በመውደቁ የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት ቢኒያም አሰፋ አስቆጥሮ ቡድኑን ከሽንፈት መታደ ችሏል። ከዚህች ግብ በኋላ ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት ቡናዎች ያገኙትን አንድ የግብ እድል ዳዊት እስጢፋኖስ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጅ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸው ነበር። በሃዋሳ ከነማ በኩልም ታፈሰ ተስፋዬ ንጹህ የግብ እድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ቢኒያም ትናንት ያስቆጠራት ግብ የፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አግቢነቱን በብቸኝነት እንዲመራ አስችላዋለች። ዛሬ የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኖሜ ካስቆጠረ ከቢኒያም ጋር ይጋራል ወይም ይልቃል። ኢትዮጵያ ቡና የሊጉ ጨዋታ ከተጀመረ ለመጀመሪያ ጊዜ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ በ14 ነጥብና በ2 የጎል ክፍያ ለመቀመጥ ችሏል።

በጨዋታው 63ኛ ደቂቃ የሃዋሳ ከነማው አጥቂ ተመስገን ተክሌ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሲሰናበት ከተመስገን መውጣት ሰባት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናው አስቻለው ግርማ ተመሳሳዩን መንገድ ተከትሏል። በተለይ አስቻለው ግርማ በዳኛው ላይ ያሳየው አመል በራሱ ደጋፊዎች ሳይቀር ተቃውሞ ያስነሳበት በመሆኑ ክለቡና አሰልጣኙ ተጫዋቹን ከተመሳሳይ ባህሪው እንዲታቀብ ሊመክሩት ይገባል። የሃዋሳ ከነማው አምበል ግርማ በቀለ በደረሰበት ጉዳት በስትሬቸር ሲወጣ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ያሳዩት ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጭ የሆነ የተቃውሞ ድምጽም ሊታረም የሚገባው ሆኖ አይተነዋል። 

ከዚህ ጨዋታ በኋላ የተገናኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና አዳማ ከነማም ሳይሸናነፉ አንድ እኩል በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን ጨርሰዋል። ከአንድ ጨዋታ ውጭ አሸንፎ የማያውቀው ንግድ ባንክ በትናንቱ ጨዋታ አሸናፊ የሚሆንበትን እድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አማካዩ አብዱልከሪም ሃሰን ባስቆጠራት ግብ እስከ ጨዋታው መጠናቀቂያ የመጨረሻ ደቂቃ ድረስ መምራት ችሎ የነበረው ንግድ ባንክ ተጨማሪ ግብ ከማስቆጠር ይልቅ ከግብ ጠባቂው ጀምሮ ሁሉም ተጫዋቾቹ ሰዓት ለመግደል ባደረጉት ሙከራ ዋጋ ከፍለው እንዲወጡ አድርጓቸዋል። በተለይ ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ በተደጋጋሚ ሰዓት ለመግደል ባደረገው ሙከራ ከዳኛው የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ ተሰጥቶታል። ይህም በተከታታይ ሶስት ጨዋታዎች ሶስተኛ ቢጫ ካርድ በተመሳሳይ ስህተት እንዲያይ አድርጎታል። ንግድ ባንክ በዚህ ዓመት ካስቆጠረው ግብ ይልቅ ግብ ጠባቂው የተመለከተው ቢጫ ከርድ በልጦ ተገኝቷል። 

ለአዳማ ከነማ የአቻነቷን ግብ ያስቆጠረው ቢኒያም አየለ ነው። ቢኒያም አየለ በተከታታይ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሶስተኛ ጐሉን አስቆጥሯል። ውጤቱን ተከትሎም አዳማ ከነማ ከነበረበት አስር ነጥብ አንድ በመጨመር 11 ሲደርስ ንግድ ባንክ ዘጠኝ አድርሷል ነጥቡን። በዘጠኝ ጨዋታ ዘጠኝ ነጥብ የያዘው ንግድ ባንክ 10ኛ ደረጃን በብቸኝነት መቆጣጠርም አስችሎታል። 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!