19፣19፣19፤ ፈረሰኞቹ የኮረንቲዎችን አለመሸነፍ ገቱ
ታህሳስ 20, 2007

  • - ብቸኛ የፈረሰኞቹ የማሸነፊያ ጐል፤ በ19ጠነኛው ደቂቃ በ19ጠነኛው ቀንና በ19ጠኝ ቁጥሩ አዳነ ግርማ መቆጠርዋ አስደናቂ ክስተት የነበረበት ጨዋታ።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ፈረሰኞቹን ወደ መሪዎቹ ሲያስጠጋ ደደቢትን ደግሞ ወደ ታች ገፍቷል። ትናንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያና ወልድያ ያደረጉትን ጨዋታ መከላከያ ሁለት ለባዶ አሸንፏል። ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠሩት ተከላካዩ ተስፋዬ በቀለ እና አጥቂው መሃመድ ናስር ናቸው። መሃመድ ናስር ትናንት ያስቆጠራት ጎል በዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት አራት አድርሳለታለች። 
Defence Vs Woldya


መከላከያ በዚህ ዓመት ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎችም ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ጐል በላይ ያስቆጠረበት ጨዋታ ሆኗል። ሁለቱም ቡድኖች ለተመልካች ማራኪ ጨዋታ ያሳዩ ሲሆን በተለይ ከእረፍት በፊት መከላከያ ከእረፍት መልስ ደግሞ ወልድያዎች በኳስ ቁጥጥርና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመቅረብ የበላይነቱን ወስደዋል። ውጤቱን ተከትሎም መከላከያ ነጥቡን 16 በማድረስ ከመሪው ሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አስችሎታል። 
Dedebit Vs Weldya

ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጠኞች አስተያየት የሰጡት የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች በዳኝነት ላይ ቅሬታ እንደሌላቸው ገልጸዋል። የመከላከያው ገብረመድህን ሀይሌ “ከእረፍት በፊት የነበረንን የጨዋታ የበላይነት አስጠብቀን መጓዝ ባለመቻላችን በሁለተኛው ክፍለ ጊዜ የበላይነቱ ተወስዶብን ታይቷል። እንደ ፍሬው ሰለሞን አይነት ተጫዋቾቻችን በጉዳት ባለመሰለፋቸው ቡድናችን የተወሰነ ክፍተት ታይቶበት ነበር” ብሏል። የወልድያ አቻቸው አቶ ሚሊዮን ታዬ በበኩላቸው “ቡድናችን ከጨዋታው አንድ ነጥብ ማግኘት ነበረበት። በተደጋጋሚ የሰራናቸው ስህተቶቻችን ዋጋ አስከፍለውናል።” ብለዋል። 

ከአመሻሹ 11፡30 ላይ የተገናኙት ደግሞ ፈረሰኞቹ ከኮረንቲዎቹ ነበር። ኤሌክትሪክ ክለብ በዚህ ዓመት ካካሄዳቸው ሰባት ጨዋታዎች አንዱንም ሳይሸነፍ የቆየ በመሆኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከመሪዎቹ ያለው ርቀት እንዳይሰፋበት ከፍተኛ ጥረት አድርጎ የሚገባ በመሆኑ ጨዋታው ተጠብቆ ነበር። አዝናኝ የኳስ ቅብብልና ጠንካራ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ አዳነ ግርማ የጨዋታውን ልዩነት የፈጠረች ጎል በ19ነኛው ደቂቃ ላይ እራሱ ባስገኘው የፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ጐል ክለቡ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሎታል ።አዳነ በ19ነኛው ደቂቃ ላይ ጐሏን ካስቆረ በኋላ የማሊያውን ቁጥር 19 ለተመልካቹ እየደነሰ አሳይቷል ቀኑም የአመቱ  ገብርኤል 19 በመሆኑ  ተገጣጥሞለታል።  ፈረሰኞቹ ያገኙት ፍጹም ቅጣት ምት ተገቢ አይደለም ብሎ የተከራከረው የመብራት ሀይሉ አምበል   የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል። 

Stgeorge Vs EEPCO


ከእረፍት በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተጋጣሚው በተሻለ የግብ ማግባት ሙከራ ያደረገ ቢሆንም በአጥቂዎቹ ጎል አምካኝነት ከመረብ ማሳረፍ ሳይችል ቀርቷል። የኤሌክትሪኩ ናይጄሪያዊ አጥቂ ፒተር በተደጋጋሚ የፈረሰኞቹን ተከላካይ ክፍል ሲረብሽ አምሽቷል። ከእረፍት መልስ ግን ፈረሰኞቹ የግብ ክልላቸውን በጋራ ሲጠብቁ በማምሸታቸው ለኤሌክትሪክ አጥቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ተዳርገዋል።

በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ፕሮፌሽናሉ ፒተር በ54ኛውና በ90ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጋቸው የጐል ሙከራዎች ለፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ፈታኝ የሆኑ ሙከራዎች ነበሩ። ከፒተር በተጨማሪም አንጋፋው አጥቂ ዮርዳኖስ አባይና ወንድሜነህ ዘሪሁን በ62ኛውና በ73ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች የኳሷን ማረፊያ መረብ ስተው የጐሉን አናት ታከው ወጡ እንጂ አስደናቂ ኳሶች ነበሩ።
EEPCO VS StGeoge

ጊዮርጊሶች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በትላንቱ ጨዋታ ተጠናክረው ወጥ የሆነ አጨዋወት ባይጫወቱ ኖሮ የመብራቶች የመጨረሻ ደቂቃዎች ጥቃት መከላከል ይከብዳቸው ነበር።  በተለይ አሉላ ግርማ ተቀይሮ ወደሜዳ ከገባ በሇላ ኳስ ባበደችበት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጊዮርጊሶች  በብቃት የመብራቶችን ጥቃት በመቆጣጠር መብራቶች በፕሪሚየር ሊጉ ይዘውት የነበረውን  ያለመሸነፍ ሪከርድ ገድበውታል።  ውጤቱን ተከትሎም ፈረሰኞቹ የነጥብ ድምራቸውን 15 በማድረስ ከሲዳማ ቡና እና ከመከላከያ ዝቅ ብለው ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። 
Stgeorge Vs EEPCO

ክልል ላይ በተካሄዱ ሶስት ጨዋታዎች ደደቢት አሁንም ለማሸነፍ ሳይታደል ባዶ እጁን ከአሰላ ተመልሷል። ሙገር ሲሚንቶ ደደቢትን አስተናግዶ ሁለት ለአንድ ባሸነፈበት ጨዋታ ለደደቢት ሄኖክ ኢሳያስ ሲያስቆጥር ለባለሜዳዎቹ ደግሞ ኤፍሬም  እና   ጌዲዮን አስቆጥረዋል። ሙገር ደደቢትን በማሸነፉ ነጥቡን ስምንት አድርሶ ከነበረበት 13ኛ ደረጃ ወደ 12 ከፍ እንዲል አስችሎታል። ደደቢት በበኩሉ የያዘውን አስር ነጥብ እንደያዘ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የፕሪሚየር ሊጉን የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች በተከታታይ አሸንፎ የነበረው ደደቢት በውድድር ዓመቱ አጋማሽ ላይ የወረደ አቋም ማሳየቱ አስገራሚ ሆኗል። 

ይርጋለም ላይ በሲዳማ ቡና እና በወላይታ ድቻ መካከል የተካሄደውን የደቡብ ደርቢ ባለሜዳው ሲዳማ ቡና በአሸናፊነት አጠናቋል። ሲዳማ በዚህ ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ መጀመሪያ ዙር ከሶስቱም የክልሉ ክለቦች ጋር ካደረጋቸው ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ በማግኘት የክልሉ የባላይነቱን አሳይቷል። በፕሪሚየርት ሊጉም 17 ነጥብ በመያዝ ከታላለቆቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና መብራት ሀይል በልጦ ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ ይገኛል። ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራና አርባ ምንጭ ጨርቃጨርቅ ያደረጉትን ጨዋታ ባለሜዳው ዳሽን ቢራ በሳሙኤል አለባቸው ብቸኛ ግብ አሸንፎ ሸኝቶታል። ዳሽን ቢራ ውጤቱን ተከትሎ ነጥቡን 12 በማድረስ  ላይ ተቀምጧል። አርባ ምንጭ ከነማ ደግሞ ቀድሞ የያዘውን 11 ነጥብ አስጠብቋል። 

ፕሪሚየር ሊጉን ሲዳማ ቡና በ17 ሲመራ ኮከብ ጎል አግቢነቱን ደግሞ ቢኒያም አሰፋ በሰባት ግብ ይመራል። ወራጅ ቀጠናው በወልድያ ከነማና ሀዋሳ ከነማ ቁጥጥር ስር ውሏል። 

ዘገባ፦ በይርጋ አበበና ፈለቀ ደምሴ
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!