ሲሳይ ባንጫና ደደቢት ሰማኒያቸውን ለምን ቀደዱ?
ታህሳስ 22, 2007


የዋሊያዎቹንና የደደቢትን የግብ መስመር በመጠበቅ የሚታወቀው ሲሳይ ባንጫ ከክለቡ ደደቢት ጋር ያለውን እህል ውሃ ማቋረጡን ሰሞኑን በስፋት ሲነገር የቆየ ዜና ነው። ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር ያለውን ቆይታ በራሱ ፍላጎት ለማቋረጥ ጥያቄ ማቅረቡንና ክለቡም “ያሰብከው ይሳካልህ በምትሄድበት ሁሉ ይቅናህ” ብሎ መልቀቂያ እንደሰጠው ተነግሯል። ምንም እንኳ ግብ ጠባቂውን በአካልም ሆነ በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም ባለፉት አራት ዓመታት ከደደቢት ጋር ባሳለፈው ጊዜ መደሰቱንና ከክለቡ ጋር በነበረው ቆይታም ደስተኛ እንደነበረ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። 
Sisay Bancha

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2007 ዓ.ም ውድድር ሲጀመር አጀማማሩ መልካም የነበረው ደደቢት እየቆየ የኋላ ማርሽ በማስገባቱ ውጤቱ ያስከፋቸው የክለቡ ሀላፊዎች ቀደም ሲል ለአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የመውጫውን በር መክፈታቸው ይታወሳል። የትናንቱ የሲሳይ ባንጫ “ልቀቁኝ” የሚል ጥያቄ ምክንያቱ ምንድን ነው? ለአራት ዓመታት የዘለቀው የአብሮነት ገመዳቸውስ እንዴት በአንድ ጀምበር ሊበጠስ ቻለ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለማጣራት በቅድሚያ በተጫዋቹ የእጅ ስልክ ደውለን ነበር። ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን በሚደረግለት የስልክ ጥሪ የተሰላቸ የሚመስለው ግብ ጠባቂው ያደረግነውን የስልክ ጥሪ ሊመልስልን ባለመቻሉ በተጫዋቹ በኩል ያለውን ስሜት ማቅረብ አልቻልንም። 

ክለቡ በተጀመረው የውድድር ዓመት እያስመዘገበ ያለው ውጤት ያላማረው ሲሳይ ባንጫ ራሱን በሌሎች ክለቦች ማሊያ ማየት ስለፈለገ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ሲኖሩ በተለይ የአማራ ክልሉ ዳሽን ቢራ የተጫዋቹ ቀጣይ ማረፊያ ሊሆን እንደሚችል የሚናገሩ ወገኖች አሉ። አስተያየት ሰጪዎች ሃሳባቸው ትክክል ነው ቢባል እንኳ የዳሽን ቢራ እና የደደቢት ውጤት ተቀራራቢ ሲሆን በተለይ ደደቢት ለአህጉራዊ ውድድር ተሳታፊ በመሆኑ ከዳሽን የተሻለ እንጅ ያነሰ ደረጃ የለውም ስለዚህ ግብ ጠባቂው ወደ ዳሽን የሚያመራ ከሆነ የተሻለ የዝውውርና የጥቅማጥቅም ጉዳይ አጓጉቶታል ሲሉ ይከራከራሉ። 

በሌላ በኩል ሲሳይ ባንጫ ካለፈው ዓመት የውድድር አጋማሽ በኋላ በተለያየ ምክንያት ከቋሚ አሰላለፍ ውጭ ሲሆን በመታየቱ የልጁ ልብ ከደደቢት ከሸፈተ መቆየቱን ያሳያል የሚሉ አሉ። በተለይ በአንዳንድ ጨዋታዎች የሚያሳየው አቋም ከክለቡ ለመልቀቅ ፍላጎት ስላለው ነው ሲሉ ይከራከራሉ። 

ሲሳይ ባንጫ ከአራት ዓመት በፊት ከደቡቡ ሲዳማ ቡና ወደ ደደቢት የተዘዋወረ ሲሆን ከደደቢት ጋር በቆየባቸው አራት ዓመታት ውስጥም አንድ የፕሪሚየር ሊግና አንድ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ማንሳት ችሏል። ከደደቢት ጋር ባሳየው አቋም የተነሳም የብሔራዊ ቡድኑን የግብ ክልል እንዲጠብቅ ተደጋጋሚ ጥሪ ቀርቦለት አደራውን መወጣት የቻለ ግብ ጠባቂ ነው። 

ዘገባ፦ ይርጋ አበበ 
ማስታወሻ፦ ውድ የኢትዮፉትቦል ዶት ኮም አንባቢያን በሲሳይ ባንጫና በደደቢት ጉዳይ ተጨማሪ መረጃዎችን እንዳገኘን እንደምናቀርብ ለመግለጽ እንወዳለን። 


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!