ፕሪሚየር ሊጉ በ10ኛ ሳምንት መርሃ ግብሩ መሪዎቹን ያገናኛል
ታህሳስ 24, 2007

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ነገና እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳል። በወጣው መርሃ ግብር መሰረትም አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳሽን ቢራን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይገኝበታል። የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ በርካቶች የቢራ ደርቢ እያሉ የሚጠሩት ቢሆንም ፈረሰኞቹ “የቢራ ደርቢ” የሚለውን ስያሜ አትጠቀሙ ብለው መግለጻቸው ይታወሳል። ጨዋታው የሚካሄደው ነገ ከአመሻሹ 11፡30 ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ያለፈውን ሳምንት ውድድራቸውን በድል በመወጣታቸው በነገው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። 
Addis Ababa Stadiumከፈረሰኞቹና ከጎንደሬዎቹ ቀደም ብሎ ባለፈው ሳምንት የሽንፈትን ጽዋ የተጎነጩት ደደቢትና ኤሌክትሪክ ይጫወታሉ። ኤሌክትሪክ ከስምንት ጨዋታ አንድ ጊዜ ብቻ የተሸነፈ ሲሆን በአንጻሩ ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂውን ሲሳይ ባንጫን ያጣው ደደቢት በበኩሉ አራት ጊዜ ተሸንፏል። በዚህ የተነሳም የነገውን ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች ትኩረት ሰጥተው እንደሚገቡ ይገመታል። 

የአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ነገ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዳማ ከነማና ሙገር ሲሚንቶ የኦሮሚያ ደርቢ ይደምቃል። አዳማ ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን ሙገር ሲሚንቶ በበኩሉ አንዱን ተሸንፎ አንዱን ደግሞ አሸንፎ በጥሩ የራስ መተማመን ላይ ይገኛል። 

አርብ ሊካሄዱ ቀደም ብሎ መርሃ ግብር ተይዞላቸው የነበሩት ጨዋታዎች ወደ እሁድ የተቀየሩት አራት ጨዋታዎች በአዲስ አበባና በክልል ይካሄዳሉ። ሶስቱ የደቡብ ክለቦች በሜዳቸው የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ሲሆኑ ቀሪው አንድ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከተከታዩ መከላከያ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ነው። ሶስት የደቡብ ክልል ከተሞች በእግር ኳስ ደምቀው በሚውሉበት የእሁዱ ጨዋታ ቦዲቲ የወላይታ ድቻንና የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ ታስተናግዳለች። በዚህ ጨዋታ ቡናዎች አስቻለው ግርማን በቅጣት ጥላሁን ወልዴን ደግሞ በጉዳት የማያሰልፉ ሲሆን የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ጎል አግቢ ቢኒያም አሰፋንም እረፍት ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል። 

ሶስት ነጥብ ማግኘት የተሳናቸው ሃዋሳ ከነማና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እሁድ ሃዋሳ ላይ ይጫወታሉ። ሁለቱ ክለቦች በውድድር ዓመቱ ካደረጓቸው ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት አንድ አንድ ጨዋታ ብቻ ሲሆን የሰበሰቡት ነጥብም ያስቀመጣቸው 13ኛና 11 ደረጃ ላይ ነው። የእሁዱን ጨዋታ በድል መወጣት የሚኖረውን ጠቀሜታ በደንብ የሚያውቁት የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። 

አርባ ምንጭ ደግሞ የአማራ ክልሉን ተወካይ ወልድያን ያስተናግዳል። ባለፈው ሳምንት ሁለቱም ሽንፈትን ያስተናገዱ ሲሆን በተለይ የሰሜን ኢትዮጵያው ተወካይ በፕሪሚየር ሊጉ ማሸነፍ የቻለው አንድ ጨዋታ ብቻ በመሆኑ የያዘው ነጥብ አምስት ብቻ ነው 12 የጎል እዳም ተሸክሟል። በእሁዱ ጨዋታም ከባለሜዳው አርባ ምንጭ ከነማ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ ይጠበቃል። 

12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የፊታችን የካቲት መጀመሪያ አካባቢ በአዲስ አበባ የሚካሄድ በመሆኑ ከነገ ቅዳሜ ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄዱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚካሄዱ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። 

ይርጋ አበበ 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!