በ10ኛው ሳምንት ሲዳማ ቡና መሪነቱን ሲያጠናክር ቅ.ጊዮርጊስ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አደረገ
ታህሳስ 27, 2007

ቅዳሜ እለት በአበበ በቂላ ስታዲየም በተደረገው የ10ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ ጨዋታ  የተገናኙት የሳምንቱ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና እና ተከታዩ ባለሜዳው  መከላከያ ነበሩ።  ጨዋታውን ሲዳማ ቡና በፍጹም ተፈሪ ጐል 1ለ0 በሆነ ውጤት ለማሸነፍ ችሏል። በውጤቱም ሲዳማ ቡና የሊጉን መሪነት  በማጠናከር  በ20 ነጥብ በሰንጠረዡ አናት ላይ ሲቀመጥ በአሰልጠኝ ገብረመድህን ሃይሌ የሚሰለጥነው መከላከያ ደረጃውን በአንድ ዝቅ አድርጐ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል።
Dedebit Vs EEPCO
ትላንት እሁድ በተደረጉት ቀሪ 6ስት ጨዋታዎች አዲስ አበባ ላይ በአበበ በቂላ ስታዲየም 8ንት ሰአት የተገናኙት ደደቢትና መብራት ሃይል ነበሩ። ሁለቱም ቡድኖች ባለፈው በ9ኛው ሳምንት ሽንፈት የደረሰባቸው እንደመሆኑ ከውድቀት ለማንሰራራት ከፍተኛ የመሸናነፍ ፍትጊያ እንደሚያደርጉ የተጠበቀ ነበር። ደደቢቶች  የተሻለ እንቅስቃሴ ባደረጉበት በመጀመሪያው አጋማሽ  በግብ አዳኙ ሳሙኤል ሳኑሚ አማካኝነት ጐል በማስቆጠር ጨወታውን መምራት ቻሉ።  በሁለተኛው አጋማሽ መብራቶች የጨዋታ የበላይነቱን ቢይዙም ጐል ለማስቆጠር ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ ሁለት ጊዜ በግቡ አግዳሚ ሲመለስ በተቃራኒው በራቸውን ዘግተው ለሳምንታት የራቃቸውን ውጤት አስጠብቀው ለመውጣት ቆርጠው ሲከላከሉ የዋሉት ደደቢቶች በመልሶ ማጥቃት በ84ኛው ደቂቃ ላይ ከረፍት መልስ ተቀይሮ በገባው 9ጠኝ ቁጥሩ በረከት ይሳቅ አማካኝነት ሁለተኛዋንና የጨዋታውን  ማሳረጊያ ጐል ለማስቆጠር ችለዋል። 
Dedebit Vs EEPCO
የጨዋታውን ውጤት ተከትሎ ደደቢት በ13 ነጥብና በ4 የግብ ክፍያ በዘንጠረዡ ወገብ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፤ መብራት በበኩሉ ከደደቢት እኩል 13 ነጥብ ይዞ በባዶ የግብ ክፍያ ወደ 8ኛ ደረጃ እራሱን ዝቅ አድርጓል።
St.George Vs Dashen Beer
በሁለተኛው ጨዋታ 10 ሰአት ላይ የተገናኙት ቅዱስ ጊዮርጊስና ዳሽን ቢራ ያደረጉት ጨዋታ  ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት ሲሆን  በጨዋታው የጐል ሙከራ  በሁለቱም በኩል መደረግ የተጀመረው ገና ጨዋታው በተጀመረ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ነበር። አሉላ ግርማ በ2ተኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጐል የመታትና በረኛው የመለሳት ኳስ እንዲሁም ዳሽኖች በ5ኛው ደቂቃ ላይ የሳቱት ባዶ ጐል ጨዋታው ጥሩ ፉክክር እንደሚታይበት ከመጀመሪያው ያመላከቱ ክስተቶች ነበሩ። ጊዮርጊሶች ጨዋታውን አፍጥነው ጫና በመፍጠር ለመጫወት ያደረጉት ጥረት ውጤት ያስገኘላቸው  በ17ኛው ደቂቃ ላይ በግራ ክንፍ በአየር ወደ ጐል የተሻማን ኳስ ዳዋ ሂንጤሳ በቄንጠኛ አኳኋን በአየር ላይ ኳሷን እንደመጣች በተረከዝ አቅጣጫዋን ወዶ ጐል በማስቀየር የመጀመሪያዋውን  ጐል ካስቆጠረ በኋላ ነበር።
St.George Vs Dashen Beer
ዳሽኖች ጐል ከተቆጠረባቸው በኋላ  አቻ ለመሆን ባደረጉት ጥረት በ37ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ኳስ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ በጊዮርጊስ 1ለ0 መሪነት ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ጊዮርጊሶች  ወደ ጐል ከሞከርዋቸውና በዳሽን ተከላካዮች ብሎክ ከተደረጉ  ኳሶች አንድዋን በእጅ ተነክታለች በሚል  ያቀረቡትን ቅሬታ ዳኛው በዝምታ አልፈውታል። 
St.George Vs Dashen Beer
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በበለጠ ማራኪ ጨዋታ የታየበት ሲሆን  በሁለቱም በኩል  ብዙ የግብ ሙከራዎች ተደርገዋል። በተለይ ጊዮርጊሶች በ57ኛው  ደቂቃ ላይ ዳዋ ሂንጤሳ አሉላ ጨርሶ ያሳለፈለትን ኳስ ወደ ግብ አክርሮ የመታ ቢሆንም በረኛው ተወርውሮ አውጥቶበታል። የዳዋ ኳስ ተመልካችን ያነቃቃች ግሩም ኳስ ነበረች። በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ውስጥ ዳሽኖች በ64ኛው ደቂቃ ላይ  አንድ ሁለት ተቀባብለው ወደ ጐል የሞከሩት ኳስ በጊዮርጊስ ተከላካዮች ተደርባ ወጥታለች።

ጊዮርጊሶች ደጉ ደበበ፣አዳነ ግርማንና ናትናኤል ዘላለምን ባላሰለፉበት በዚህ ጨዋታ በሃይሉ ቱሳ፣ ዳዋ ሂንጤሳ  እና ከረፍት መልስ ጸባዩን አሳምሮ የገባው አሉላ ግርማ ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይተዋል፣ ፍጹም ገብረማርያም በትላንቱ ጨዋታ ጥሩ  አቋም ላይ አልነበረም። አሉላ ግርማ  በ71ኛውና በ80ኛው ደቂቃ ላይ ከበረኛ ጋር ብቻ ለብቻ ተገናኝቶ ወደ ጐል የሞከራቸው ኳሶች  ኮኮብ ሆኖ በዋለው የዳሽኑ በረኛ ሊመለሱበት ችሏል። ጨዋታው በይበልጥ ውበትና ውጥረት እየበዛበት የመጣው በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ላይ ነበር።  በነዚህ የመጨረሻ ደቂቃዎች ሳላዲን በርጊቾ ከኮርና በአየር የተሻገረን ኳስ በግንባር በመግጨጥ ወደ ጐል ለመቀየር ያደረገው ጥረት በዳሽን የግብ አናት ላይ ለጥቂት ከወጣች በኋላ በይበልጥ ዳሽኖች የመጨረሻዋን አምስት ደቂቃ በጨዋታ የበላይነት  ተጭነው ተጫውተዋል፤ ለዳሽኖች ጥሩ መሆን ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ የነበረው አስራት መገርሳ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ወደ ጐል ሲያሻማ በ89ኛውና በ90ኛው ደቂቃ ላይ ያሻማቸው ኳሶች የዳሽን አጥቂዎች መጠቀም አቃታቸው እንጂ ባለቀ ሰአት አቻ ሊሆኑባቸው የሚችሉ አጋጠሚዎች ነበሩ።  
St.George Vs Dashen Beer
በትላንትናው እለት ፈረሰኞቹ  ያገኙት ድል ሶስተኛው ተከታታይ ድላቸው ሲሆን በውጤቱም መሰረት ቅ.ጊዮርጊስ በ9ኝ ጨዋታ  በ18 ነጥብና በ6ት የግብ ክፍያ ከደረጃው ሰንጠረዥ አናት ዝቅ ብሎ በ2ተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ችሏል። ዳሽን ቢራ በ10ር ጨዋታ 12 ነጥብ ይዞ በ11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

 በሌላ በኩል በክልል ከተሞች በተደረጉ የ10ኛ ዙር  የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ቋሚ ተሰላፊዎቹን ሳያስከትል ወደ ወላይታ ያቀናው ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ዲቻ ባዶ ለባዶ ሲለያይ፣ አዳማ ላይ አዳማ ከነማ  ከሙገር ሲሚንቶ 1ለ1 አቻ ተለያይቷል።  ሐዋሳ ላይ ንግድ ባንክን ያስተናገደው ሐዋሳ ከነማ በበኩሉ በሜዳው 2ለ1 ሲሸነፍ ፣ አርባ ምንጭ ወልዲያ ከነማን 1ለ0 ማሸነፍ ችሏል።  

ፕሪሚየር ሊጉን  ሲዳማ ቡና፣ ቅ.ጊዮርጊስ እና መከላከያ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘው ይመሩታል። የኮኮብ ግብ አግቢነቱን  አሁንም የቡናው ቢኒያም አሰፋ በ7ጐል  ሲመራ የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሚ በ6ት ጐል ይከተላል። 

ዘገባ፦ ፈለቀ ደምሴኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!