ፕሪሚየር ሊጉ በ11ኛ ሳምንት ፈረሰኞቹን ወደ አርባምንጭ፣ ሰማያዊዮቹን ደግሞ ወደ ጎንደር ይልካል
ጥር 01, 2007

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ነገና እሁድ በአዲስ አበባ፣ አርባ ምንጭ፣ አሰላ፣ ጎንደርና ይርጋለም ላይ ቀጥሎ ይውላል። የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ይርጋለም ላይ በተከታታይ ሶስተኛ ጨዋታውን ከሜዳው ውጭ የሚያካሂደውን ወልድያን ያስተናግዳል። ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ አናትና ግርጌ ላይ የተቀመጡ በመሆናቸው ይህን ያህል ጠንካራ ፉክክር ይካሄድበታል ተብሎ ባይጠበቅም በቅርቡ የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረገው ወልድያ በቀጣዩ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ለመቆየት የግድ ከአሁኑ ነጥብ መሸመት ስላለበት ጨዋታው ቀላል ግምት ሊሰጠው አይገባም የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች አሉ። የአሰላው አረንጓዴ ስታዲየም በፕሪሚየር ሊጉ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሙገር ሲሚንቶ የነጥብ ጎረቤቱን ሃዋሳ ከነማን ያስተናግዳል። 

የቱሪስብ መስህቧ የደቡብ ክልሏ አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ፈረሰኞቹን በእንግድነት ትጋብዝና ከከተማዋ ተወካይ አርባ ምንጭ ከነማ ጋር ታጫውታለች። ሁለቱ ክለቦች ያለፈውን ሳምንት በሜዳቸው ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቻቸውን በተመሳሳይ አንድ ለባዶ ያሸነፉ በመሆኑ በነገው ጨዋታ ሁለቱም ጥሩ የራስ መተማመን ላይ ሆነው ይጫወታሉ። 

ከዳሽን ተራራ ግርጌ ላይ የተቆረቆረችውና ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ደግሞ የከተማዋ ተወካይ ዳሽን ቢራ ከጥሎ ማለፉ አሸናፊ ደደቢት ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ በፋሲለደስ ስታዲየም ታካሂዳለች። ዳሽን ቢራ በዓመቱ በሜዳው ካደረጋቸው ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ የተሸነፈ ሲሆን ደደቢት በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ከአዲስ አበባ ውጭ የተጫወተው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ያን ጨዋታም በሽንፈት አጠናቋል። በሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በርካታ የዳሽን ቢራ ተጫዋቾች የቀድሞ ክለባቸውን በተቃራኒነት ይፋለማሉ። ከእነዚህ ተጫዋቾች መካከል አምበሉ አይናለም ሀይሉ አጥቂዎቹ ሚኬኤል ጆርጆና መዳኔ ታደሰ ይገኙበታል። ደደቢት ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ኤሌክትሪክን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ሲመለስ ዳሽን በበኩሉ በቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ለባዶ በመሸነፍ ነበር ወደ 11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የደረሱት። 

በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን የተሸነፈው የአጥናፉ ዓለሙ ኤሌክትሪክ በተከታታይ ሶስት ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ያጠናቀቀውን አዳማ ከነማን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያስተናግዳል። “ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የደረሰብንን ሽንፈት ረስተን በቀጣይ ጨዋታዎቻችን ላይ ትኩረት በማድረግ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን” ሲሉ የኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ለዝግጅት ክፍላችን በስልክ ገልጸዋል። የቀድሞው መብራት ሀይል ወይም የአሁኑ ኤሌክትሪክ ክለብ የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ጊዜ ያነሳ ሲሆን ባለፉት አምስት ዓመታት ግን በቡልጋሪያዊው ዮርዳን ሰታንኮቪች የአሰልጣኝነት ዘመን ላለመውረድ የሚጫወት ክለብ ሆኖ ነበር የቆየው። ክለቡ በዚህ ዓመት በኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች መሰልጠን ከጀመረ ወዲህ ግን በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ቀርቧል። በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚሰለጥነው አዳማ ከነማ በበኩሉ ለአንድ ዓመት በብሔራዊ ሊጉ ሲወዳደር ከርሞ ከተመለሰ በኋላ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኗል። በተለይ በሜዳው ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ያለሽንፈት ነው ያጠናቀቀው። 

በተከታታይ ሶስት ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት በማጠናቀቁ ስድስት ነጥብ ያጣው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ እንደ እሱ ሁሉ በቅርቡ የአቋም መዋዠቅ እያሳየ የመጣውን መከላከያን ይገጥማል። በበርካታ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች የተሞላው መከላከያ ባለፈው ሳምንት በሲዳማ ቡና የደረሰበትን ሽንፈት ለማወራረድ ቡና ደግሞ ከሶስት ጨዋታ በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ በሳምንቱ ትልቅ ግምት የተሰጠው ጨዋታ ሆኗል። ኢትዮጵያ ቡና በ15 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን መከላከያ በበኩሉ ከቡና በአንድ ነጥብ ልቆ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ቡና ጠንካራ አጥቂ ሲኖረው መከላከያ ደግሞ የራሱን የአደጋ ክልል በንቃት የሚጠብቅ የተከላካይ ክፍልና ግብ ጠባቂ አለው። ለዚህም ማረጋገጫው በአስር ጨዋታ መከላከያ የተቆጠረበት ሶስት ግብ ብቻ ሲሆን ያስቆጠረው ደግሞ አምስት ብቻ ነው። የጥላሁን መንገሻ ልጆች በበኩላቸው በስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ጎል ያስቆጠሩ ቢሆንም የተቆጠረባቸው ጎልም በርካታ ነው። ለቡና የአጥቂ መስመር ጥንካሬ የቀድሞዎቹ የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾች አማካዩ ኤሊያስ ማሞና አጥቂው ቢኒያም አሰፋ ሲጠቀሱ፤ ለመከላከያ የተከላካይ መስመር ጥንካሬ ደግሞ የቀድሞዎቹ የቡና ተከላካዮች ተስፋዬ በቀለና ሲሳይ ደምሴ ከቀድሞው የቡና ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው ጋር የፈጠሩት ውህደት ነው።   

በተከታታይ ስምንት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ተስኖት የሰነበተውና በአስረኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር ሃዋሳ ላይ ሃዋሳ ከነማን አሸንፎ የተመለሰው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ወላይታ ድቻን ያስተናግዳል። በተከታታይ ከሁለት የደቡብ ክልል ክለቦች ጋር የተገናኘው ንግድ ባንክ ነገስ በተከታታይ ሁለተኛ ድሉን ያስመዘግባል ወይስ ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርተው የወጡት ወላይታ ድቻዎች ነገም ነጥብ ይዘው ይመለሳሉ? 

ሲዳማ ቡና በአስር ጨዋታ 20 ነጥብ በመሰብሰብ ከደረጃው አናት ላይ ሲቀመጥ ፈረሰኞቹ ደግሞ በዘጠኝ ጨዋታ 18 ነጥብ ሸምተው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በመሪነት ላይ የተቀመጡት ሁለቱ ክለቦች በውድድር ዓመቱ ካካሄዷቸው ጨዋታዎች በየጨዋታው በአማካይ ሁለት ነጥብ መሰብሰብ ችለዋል። ከክለቡ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎችን አድርጎ ሰባት ጎል ያስቆጠረው ቢኒያም አሰፋ የከፍተኛ ጎል አግቢዎችን ደረጃ ይመራል። የፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኖ እየመራ ያለው ቢኒያም አሰፋ ያስቆጠረው የጎል ብዛት መከላከያ ካስቆጠረው በሁለት ይልቃል። 

ዘገባ፦ ይርጋ አበበ
ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!