ፕሪሚየር ሊጉ በሲዳማ ቡና እየተመራ መጓዙን ቀጥሏል
ጥር 04, 2007

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ትናንትና ከትናንት በስቲያ ሰባት ጨዋታዎች ተካሂደዋል። የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የነበረው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ወላይታ ድቻ መካከል በአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታዲየም የተካሄደው ነው። ከብሔራዊ ሊጉ ወራቤ ከነማ ወላይታ ድቻን ከተቀላቀለ በኋላ ወሳኝ ጎሎችን እያስቆጠረ ያለው ባየ ገዛኸኝ እንግዳውን ቡድን አሸናፊ ያደረገች ጎል በማስቆጠር ንግድ ባንክን በሜዳው እንዲሸነፍ አድርጓል። የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድን ወላይታ ድቻ ፕሪሚየር ሊጉን ከተቀላቀሉበት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ሶስት ጊዜ ተገናኝቶ ሁለቱን ሲያሸንፍ በአንዱ ደግሞ አቻ በመውጣት የውጤት የበላይነቱን እንዲያስጠብቅ አስችሎታል። ባየ በንግድ ባንክ መረብ ላይ ያሳረፋት ጎል በዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት አምስት በማድረስ የከፍተኛ ጎል አግቢዎችን ጎራ እንዲቀላቀል አስችሎታል።  
Coffee Vs Defence


ከዚህ ጨዋታ በኋላ የተገናኙት ደግሞ ኤሌክትሪክና አዳማ ከነማ ናቸው። ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ በመሸነፉ ቀውስ ውስጥ ገብቷል የተባለው ኤሌክትሪክ በሜዳው ከአዳማ ከነማ ጋር የሚያደረገውን ጨዋታ በአሸናፊነት ይወጣል ተብሎ ቢጠበቅም ግምቶች የተሳሳቱ ሆነዋል። ተቀይሮ እየገባ ክለቡን የሚታደጉ ወሳኝ ጎሎችን እያስቆጠረ የሚገኘው ቢኒያም አየለ አዳማ ከነማን ሙሉ ሶስት ነጥብ ቋጥሮ ወደ ቤቱ እንዲመለስ ያስቻለችዋን ጎል አስቆጥሯል። ቢኒያም በዓመቱ ለክለቡ አምስት ጎሎችን በማስቆጠር ከፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ጎል አግቢዎች ተርታ ስሙ እንዲሰፍር አስችሎታል። 

ፕሪሚየር ሊጉ ትናንትም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ቀጥሎ የዋለ ሲሆን ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ ሸይቩ ጅብሪልን በቀይ ካርድ በማጣቱ በጎዶሎ ከተጫወተው ደደቢት ጋር አንድ እኩል ተለያይተዋል። የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በበኩሉ በሜዳው ይርጋለም ላይ የፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ግርጌ በብቸኝነት የተቆጣጠረውን ወልድያን አስተናግዶ አንድ ለባዶ በማሸነፍ ሸኝቶታል። ወልድያ ያለፉትን ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ከሜዳው ውጭ አካሂዶ ሶስቱንም ሲሸነፍ ሲዳማ ቡና በበኩሉ ሶስቱን ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። 

አሰላ አረንጓዴው ስታዲየም ጎል ያልተስተናገደበትን የሙገር ሲሚንቶንና የሃዋሳ ከነማን ጨዋታ አካሂዷል። ሁለቱ ክለቦች በደረጃ ሰንጠረዡ 12ኛ እና 13ኛ የተቀመጡ በመሆኑ ሙገር ካሸነፈ ደረጃውን በማሻሻል ወደ 11 ከፍ ይላል ሃዋሳ ካሸነፈ ደግሞ 12ኛ ደረጃን ይይዛል ተብሎ ቢጠበቅም አንዳቸው የሌላቸውን በር መድፈር ሳይችሉ መሳ ለመሳ ተለያይተዋል። ያለፉትን ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፉ ወደ ቀድሞ አስፈሪነቱ ተመልሶ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አርባምንጭ ተጉዞ በለስ ሳይቀናው አንድ ለባዶ ተሸንፎ ተመልሷል። ፈረሰኞቹ በዓመቱ ካደረጓቸው አስር ጨዋታዎችም ጎል ሳያስቆጥሩ የወጡባቸውን ጨዋታዎች ሶስት ሲያደርሱ በሽንፈት ያጠናቀቋቸውን ጨዋታዎች ደግሞ ሁለት አድርሰዋል። 

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የተካሄደው ደግሞ በአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ነው ኢትዮጵያ ቡናና መከላከያ ያደረጉት ጨዋታ። በሳምንቱ መርሃ ግብር ከ6ስቱ የአዲስ አበባ ክለቦች ሙሉ ሶስት ነጥብ በማግኘት ብቸኛው የአዲስ አበባ ክለብ የሆነው ቡና ቢኒያም አሰፋ በፍጹም ቀጣት ምትና አህመድ ረሺድ ሽሪላው በጨዋታ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች አሸንፎ መውጣት ችሏል። ቡና በማሸነፉ ከነበረበት ስድስተኛ ደረጃ ወደ ሶስተኛ ከፍ ሲል መከላከያ በበኩሉ ከነበረበት አምስተኛ ደረጃ ወደ ስድስተኛ ዝቅ ብሏል። የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ በተመለከተ ሰፋ ያለ ዘገባ እናቀርባለን። 
ፕሪሚየር ሊጉን ከሚመራው ሲዳማ ቡና ጨምሮ ሶስት የክልሉ ክለቦች በሊጉ ጠንካራ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ። ሲዳማ ቡና 23 ነጥብ በመያዝ ከታላላቆቹ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ከሃብታሞቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዳሽን ቢራና ደደቢት የተሻለ ነጥብ ሲሰበስብ ጎረቤታማቾቹ አርባ ምንጭ ከነማና ወላይታ ድቻ በበኩላቸው እኩል 17 ነጥብ በመያዝ ከንግድ ባንክ፣ መከላከያ፣ ሃዋሳ ከነማ፣ ኤሌክትሪክና ደደቢት በላይ መቀመጥ ችለዋል። 

በሊጉ ጠንካራ ውድድር እያደረጉ ያሉትን የደቡብ ክልል ክለቦችን በተመለከተ ሰፋ ያለ ዘገባ የምናቀርብ ይሆናል።

ዘጋቢ፦ ይርጋ አበበ 
ኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!