ኢትዮጵያ ቡና ከመከላከያ የዳኝነት ብቃት ጥያቄ ውስጥ የገባበት ጨዋታ
ጥር 04, 2007

እሁድ ጥር 3/2007 ዓ.ም ከቀኑ አስር ሰዓት ላይ ለቀድሞ ጸጥ ረጭ ብሎ ሰላማዊ አየር ይተነፍስ የነበረው የአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታዲየም የቀድሞ ጸጥታውን ገፍፎ በበርካ ሰዎች ጩኸት ተሞልቷል። ከመሃል አዲስ አበባ የራቀ በመሆኑና ስታዲየሙን ባለበሰው ሰው ሰራሽ ሣር የተነሳ አስታዋሽ አጥቶ የቆየው አበበ ቢቂላ ስታዲየም 12ኛውን የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ መካሄዱን ተከትሎ የፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዲካሄዱ በመወሰኑ ሰሞኑን ቀን የወጣለት ይመስላል። በዚህ የተነሳም ባለፉት ሁለት ተከታታይ ሳምንታት ሰባት ጨዋታዎችን በማካሄድ ጦም ያደረውን ያህል በጨዋታ የተደራረበ ፕሮግራም ተጨናንቋል። ትናንት ምሽትም የተካሄደው ይሄው ነው በፕሪሚየር ሊጉ የሳምንቱን ታላቅ ጨዋታ ያስተናገደበት ኢትዮጵያ ቡናን ከመከላከያ። 
Coffee Vs Defence

ቡናዎች አምበላቸውን ዳዊት እስጢፋኖስና ምክትሉን መስዑም መሃመድን በጉዳት አጥቂውን አስቻለው ግርማን ደግሞ በቅጣት እንዲሁም የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ጎል አግቢ ቢኒያም አሰፋን በእረፍት ለአንድ ሳምንት አጥተው የቆዩ ቢሆንም በትናንትናው ጨዋታ ዝግጁ ሆነውላቸዋል። የገብረመድህን ሀይሌ ቡድን በበኩሉ አማካዮቹን ተክለወልድንና ፍሬው ሰለሞንን በጉዳት አጥቶ የቆየ ሲሆን ሁለቱ ከከብ አማካዮች ለትናንትናው ግዳጅ ብቁ ሆነው ቀርበውለታል። በዚህ የተነሳም የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት ተችሮታል። ቀድሞም ቢሆን የክለባቸው ማንኛውም እንቅስቃሴ እንቅልፍ የሚነሳቸው የቡና ደጋፊዎች በትናንቱ ጨዋታም የአበበ ቢቂላን ስታዲየም ሞልተው ቡድናቸውን መደገፍ ጀምረዋል። 

ጨዋታው ተጀመረ። የኢትዮጵያ ቡናው አምበል ዳዊት እስጢፋኖስ እግሩ ስር የገባችውን ኳስ ለቡድን አጋሩ አቀብላለሁ ብሎ በስህተት ለመከላከያው አጥቂ መሃመድ ናስር አቀበለው። ለወትሮው ከግብ አፋፍ ኳስ አግኝቶ የማይምረው መሃመድ ከዳዊት በችሮታ ያገኛትን ኳስ እሱም ለቡናው ግብ ጠባቂ ጌቱ ተስፋዬ በስጦታ ለገሰው። የቡና ደጋፊዎችና ዳዊት እስጢፋኖስ እፎይ ሲሉ ጥቂት የመከላከያ ደጋፊዎችና አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ደግሞ ብስጭት አሉ። ይህ የሆነው ጨዋታው በተጀመረ አንድ ደቂቃ እንኳ ሳይሞላ ነበር። ጨዋታው በመሃል ሜዳ ውበት አልባ እንቅስቃሴ ታጅቦ በቀጠለበት ሰዓት አስቻለው ግርማ ቡናን መሪ ማድረግ የምትችል ኳስ ደረሰው ከቡድን አጋሩ ኤሊያስ ማሞ። አስቻለው ግን ኳሷን ከጀማል ጣሰው ጀርባ ከተወጠረው መረብ ላይ ማሳረፍ ሳይቻለው ቀረ። 
በእለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ካሜሩናዊው የኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ ኦሊቨር የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ አሁንም መሃመድ ናስር ለጎል የቀረበች ኳስ አግኝቶ ነበር እሱም ተሳስቶ ከመረቡ በጥቂት ርቀት ላይ ሰደዳት። ሽመልስ ተገኝ በቡናው አማካይ ኤሊያስ ማሞ ላይ ከባድ ፋኦል ቢሰራበትም ዳኛው በምክር ብቻ አለፉት።  ትንሽ ቆይቶ ደግሞ የቀድሞው የቡና የአሁኑ የመከላከያ ተከላካይ ተስፋዬ በቀለ ጃምቦ የቀድሞ የክለብ አጋሩን አስቻለው ግርማን በጠንካራ ክንዶቹ ደስቆ ለቀቀው። ለዚህ ጥፋት ዳኛው ጃምቦን በምክር ብቻ ማለፍ አልፈለጉም የጨዋታውን የመጀመሪያ ቢጫ ካርድ መዘዙበት እንጅ በ13ኛው ደቂቃ። 

ጨዋታው በተጀመረ 30ኛው ደቂቃ ፈጣኑ የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ አስቻለው ግርማ ከኤሊያስ ማሞ የተሰጠውን ኳስ ይዞ ወደ ጀማል ጣሰው ሲቀርብ የመከላከያው ተከላካይ ዮሃንስ ወይም ኩባ ጥፋት ሰራበት። ዳኛው ጥፋት ለፈጻመው ዮሃንስ ቢጫ ካርድ ሲሰጡት ለተበዳዩ ቡድን ደግሞ ፍጹም ቅጣት ምት ቸሩት። የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ጎል አግቢነት እየመራ ያለው ቢኒያም አሰፋ ፍጹም ቅጣት ምቱን መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ አደረገ። ይህች ጎል ቢኒያም በዓመቱ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ያስቆጠራት ስምንተኛ ጎሉ ነች። ተደጋጋሚ ጉዳቶችን እያስተናገደ በርካታ ጨዋታዎች ስለሚያመልጡት “ጉዳተኛው” እየተባለ ሲተች የነበረውና በዚህ ዓመት ግን እግሮቹ ተስለው የመጣው ቢኒያም አሰፋ ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና ካስቆጠራቸው 14 ጎሎች ስምንቱን በማስቆጠር ባለውለታ ሆኗል። 
በጎሏ የተነቃቁት ቡናዎች በተደጋጋሚ የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል ደጋግመው ቢፈትኑም ኳስና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለይ አማካዩ ኤሊያስ ማሞ የመከላከያው ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው የግብ ክልሉን ለቆ መውጣቱን አይቶ የመታት ኳስ የግቡን አግዳሚ ስትመለስ አስቻለው ግርማ ብቻውን ቢያገኛትም መረቡን ማስነካት አልቻለም። መከላከያዎች የተቆጠረባቸው ጎል ሳይበግራቸው ውጤቱን ለመቀልበስ ተደጋጋሚ የማግባት ሙከራ ቢያደርጉም ለወትሮው በቀላሉ ጎል የሚቆጠርበት የቡና ግብ ክልል ለመከላከያ ፍንክች የሚል አልሆነም። በተለይ ምንይሉ ወንድሙ በግንባሩ ገጭቶ ጎል አስቆጠረ ሲባል የቡናው ግብ ጠባቂ ጌቱ ተስፋዬ ኳሷና መረቡ እንዳይነካኩ አድርጓል። 

ከእረፍት መልስ ገብረመድህን ሀይሌ ምንይሉ መንድሙን አስወጥቶ ሙሉዓለም ጥላሁንን በማስገባት ይበልጥ ተጭኖ ለመጫወት ሞክሮ ነበር። የመሃል ሜዳውን በፍጹም የበላይነት የተቆጣጠሩት መከላከያዎች ለኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ ክፍል ፈታኝ ሆነው ነበር ያመሹት ልፋታቸው በውጤት ባይታጀብም። ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በማድረጋቸው መከላከያዎች ቢያንስ በጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው መውጣት የሚገባቸው ቢሆንም ወጣቱ የቡና ተከላካይ አህመድ ረሽድ ወይም ሽሪላው በጨዋታው መጠናቀቂያ ሰዓት ቡናን ሁለት ለባዶ እንዲያሸንፍ ያቻለች ጎል በማስቆጠር ጨዋታው ተጠናቀቀ። 

በእለቱ ጨዋታውን የመሩ ዳኞች ጨዋታውን በትክክል መምራት ሲሳናቸው የታየ ሲሆን በተለይ ሽሪላው ለቡና ያስቆጠራት ጎል ከጨዋታ ውጭ ብትሆንም ባለማየታቸው ጎሏን አጽድቀዋታል። ከጨዋታው መጀመር ጀምሮ እስከመጠናቀቂያው ሰዓት ድረስ ከፋኦል ጋር ዝምድና እንዳለው ሁሉ የቡና አጥቂዎችን ሲወግር ያመሸው ተስፋዬ በቀለ ጃምቦ በቀይ ካርድ አለመሰናበቱም የዳኛው ስህተት ሆኖ አይተነዋል። ኢትዮጵያ ቡና በ62ኛው ደቂቃ አምበሉ ዳዊት እስጢፋኖስን ቀይሮ ሲያስወጣ ዳዊት ሰዓት ለማባከን ላደረገው ሙከራ ዳኛው ቢጫ ካርድ አለመስጠታቸው ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የጨዋታውን መጠናቀቅ የሚያበስር ፊሽካ ሲነፉ ለያዥ ለገላጋይ አስቸጋሪ የሆነውን ሙሉዓለም ጥላሁንንም ቢሆን ካርድ ሊያሳዩት ይገባ ነበር። 

በአጠቃላይ ግን የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ በመከላከያ የጨዋታ ብልጫና በቡና የጎል ብልጫ የተጠናቀቀ ሲሆን በቡና በኩል ሮቤል ግርማ፣ መስዑድ መሃመድና ቢኒያም አሰፋ በመከላከያ በኩል ደግሞ ተከላካዮቹ ተስፋዬ በቀለ፣ ዮሃንስ ኩባ እና አምበሉ ሚኬኤል ደስታ የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመለከቱ ተጫዋቾች ናቸው።


ይርጋ አበበ

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!