በ12ኛው ሳምንት በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ለውጦች የታዩበት ሆኗል
ጥር 11, 2007

አስራ አራት ክለቦች ለአንድ ዋንጫና ወደ ብሔራዊ ሊጉ ላለመወረድ ትንቅንቅ የሚያደርጉበት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንትና ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀሩታል። ሊጉ ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባው አበበ ቢቂላና በክልል ከተሞች ተካሂዷል። 

የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና መከላከያ ያደረጉት ጨዋታ ነው። ሁለቱ ቡድኖች ካላቸው የቡድን ስብስብና ከአሰልጣኝ ኳሊቲ አኳያ ለዋንጫ ይጫወታሉ ተብለው የታጩ ክለቦች ቢሆንም በተከታታይ በመሸነፋቸው ከደረጃው መሪዎች በብዙ ማይል ርቀው ይገኛሉ።

በቅዳሜ ምሽቱ ጨዋታም ንግድ ባንክ የሚሸነፍ ከሆነ ከመሪዎቹ ይልቅ ወደ ወራጆቹ የመቅረብ እድል የሚኖረው በመሆኑ መከላከያን ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ከሳምንት በፊት ሁለቱም ቡድኖች ተሸንፈው የነበረ ሲሆን የቅዳሜውን ጨዋታ በአሸናፊነት ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት አድርገው ነበር። በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት ቡድኑን እያሳሳበት ያለው መከላከያ የመጀመሪያ ተመራጭ ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው በደረሰበት ጉዳት ምክንያት በቅዳሜው ጨዋታ የተሰለፈው ተቀያሪው ይድነቃቸው ኪዳኔ ነበር። 

ፍሊፕ ዳውዝና ኤፍሬም አሻሞ ወደ ግብ አስቆጣሪነት በተመለሱበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ንግድ ባንክ ሙሉ ሶስት ነጥብ ከሶስት ግቦች ጋር ይዞ መውጣት ችሏል። መከላከያን ከባዶ ከመሸነፍ የታደገችውን ግብ ያስቆጠረው በቅርቡ የተሞሸረው ሙሉዓለም ጥላሁን ነው በፍጹም ቅጣት ምት። 

በእለቱ ሁለተኛው ጨዋታ የነበረው ተደጋጋሚ ሽንፈት እያስተናገደ ያለው ደደቢትና በተቃራኒው በጥሩ አቋም ላይ ያለው አርባምንጭ ከነማ ያደረጉት ጨዋታ ነው። አርባ ምንጭ ባለፈው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን በሜዳው ያሸነፈ ሲሆን ደደቢት በበኩሉ ጎንደር ላይ ከዳሽን ቢራ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ይታወሳል። በቅዳሜው ጨዋታም ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታውን በአሸናፊነት በመጨረስ ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ፉክክር አድርገው ነበር። በመጀመሪያ እንግዳው ቡድን በበረከት ወልደመስቀል ግብ መሪ ሲሆን ደደቢት ደግሞ በሳሙኤል ሳኖሜ ግብ አቻ ሆኖ ጨዋታውን መጨረስ ችሏል። ውጤቱን ተከትሎም አርባ ምንጭ በ18 ነጥብና በአንድ ንጹህ ግብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። 

ትናንት የተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች በሙሉ የተካሄዱት በክልል ስታዲየሞች ነው በተመሳሳይ ዘጠኝ ሰዓት ላይ። ከተካሄዱት አምስት ጨዋታዎች መካለል አራቱን ባለሜዳዎቹ ክለቦች በአሸናፊነት ሲያጠናቅቁ አንድ ጨዋታ ብቻ የእንግዳው ቡድን ማሸነፍ ችሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልድያ ከነማን። 

ባለፈው ሳምንት ወደ አርባ ምንጭ ተጉዞ የሽንፈት ጽዋን ተጎንጭቶ ተመልሶ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ትናንት በጥምቀት ዋዜማ ወደ ወሎ ተጉዞ ወልድያ ከነማን በማሸነፍ ሙሉ ሶስት ነጥብና ንጹህ ሶስት ግብ አስቆጥሮ ተመልሷል። ውጤቱን ተከትሎም ፈረሰኞቹ በ11 ጨዋታ 21 ነጥብና ስምንት ንጹህ የግብ ክፍያ በመያዝ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀራቸው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።  

ይርጋለም ላይ የተካሄደውን የቡና ደርቢ ጨዋታ ሲዳማ ቡና አንድ ለባዶ በማሸነፍ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል። የትናንቱን ጨዋታ ጨምሮ ኢትዮጵያ ቡና በዚህ ዓመት ከአዲስ አበባ ውጭ ያካሄዳቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል። ቡና አራት ጨዋታዎችን ከአዲስ አበባ ውጭ አካሂዶ በሁለቱ ሲሸነፍ ሁለቱን አቻ ወጥቷል። በትናንቱ ጨዋታ በለስ የቀናው ሲዳማ ቡና በ12 ጨዋታ የሰበሰበውን ነጥብ 26 አድርሶ ከሊጉ አናት ላይ በክብር ተሰይሟል። የሽንፈት ጽዋን ተጎንጭቶ ከይርጋለም የተመለሰው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በ11 ጨዋታ 18 ነጥብና ሶስት የግብ ክፍያ በመያዝ እሱም እንደ ፈረሰኞቹ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

በሌላው የሲዳማ ዞን ጨዋታ የቀድሞውን አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋን ያሰናበተው ሃዋሳ ከነማ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተከታታይ ሽንፈት እያስተናገደ የመጣውን ኤሌክትሪክን ሁለት ለአንድ ማሸነፍ ችሏል። ኤሌክትሪክን ያሸነፈው ሃዋሳ ከነማም ከነበረው ሰባት ነጥብ ላይ ሶስት በማከል ነጥቡን አስር አድርሶ ከነበረበት ደረጃ አንድ በማሻሻል 12ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። 

ሌላው የደቡብ ክልል ክለብ የሆነውና በጥንካሬ እየተጓዘ ያለው ወላይታ ድቻ ቦዲቲ ላይ ሙገር ሲሚንቶን ጋብዞ አንድ ለባዶ አሸንፎ ሸኝቶታል። ወላይታ ድቻዎች ከትናንቱ ጨዋታ ሶስት ነጥብ በማግኘታቸው ያላቸውን የነጥብ ድምር 20 በማድረስ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ወላይታ ድቻ ከሰበሰበው ያ ነጥብ በተጨማሪ የክፉ ቀን መጠባበቂያ ሶስት ንጹህ የግብ ክፍያም አለው። ክለቡ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው በመሆኑ ተስተካካይ ጨዋታውን ከሁለት ሳምንት በኋላ ተጫውቶ የሚያሸንፍ ከሆነ ነጥቡን ከዚህም በላይ ከፍ ማድረግ ይችላል። ትናንት በወላይታ ድቻ የተሸነፈው ሙገር ሲሚንቶ በበኩሉ ከነበረበት 12 ደረጃ አንድ በመቀነስ 13ኛ ላይ ተቀምጧል። 

በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየም የተካሄደው የአዳማ ከነማና ዳሽን ቢራ ጨዋታ በባለሜዳው አዳማ ከነማ አንድ ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል። አዳማ ከነማ ያስቆጠራት ግብ የግቡን መስመር ያለፈች ባለመሆኗ ግቧ ልትቆጠርብን አይገባም ሲሉ የዳሽን ቢራ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ከጨዋታው በኋላ የሁለቱም ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የዳሽን ቢራው አሰልጣኝ ሳምሶን    “የዳኝነት ችግር ለእግር ኳሳችን አደጋ ነው። በተለይ ክልል ላይ የሚካሄዱ ጨዋታዎች በካሜራ ስለማይቀረጹ ከፍተኛ የዳኝነት ክፍተት የሚታይባቸው ጨዋታዎች ናቸው። በዛሬው ጨዋታ የሆነውም ከዚህ የተለየ አይደለም” ሲል ተናግሯል። የአዳማ ከነማው አሸናፊ በቀለ በበኩሉ                     ብሏል። ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ዘንድሮ የተመለሰው አዳማ ከነማ በ18 ነጥብና ሶስት ተጨማሪ የግብ ክፍያ ይዞ አምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። 


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!