ክለቦች ትኩረት ሊሰጡት የሚገባው የዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል
ጥር 13, 2007

የኢትዮጵያ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል መካሄድ የጀመረው በንጉሰ ነገሥት ኃይለሥላሴ ዘመን ነው። ነገር ግን ፌስቲቫሉ በተለያዩ ምክንያቶች አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ እያለ ላልተወሰነ ጊዜ መካሄድ አቁሞ ነበር። በ1990ዎቹ አጋማሽ በቀድሞው ዩኒቲ ኮሌጅ የአሁኑ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ አስተባባሪነት የግልና የመንግሥት ከፍተኛ ተቋማት የጋራ የስፖርት ውድድር መካሄድ ጀመረ። ነገር ግን የሁለቱ ተቋማት ማለትም የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ተቋማት መካከል በተጫዋቾች ምርጫ ዙሪያ አለመግባባት በመፈጠሩ ውድድሩ በአንድ ላይ መካሄዱ ቀርቶ ከሁለት ተከፍሎ መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ ስምንተኛ ዓመቱን ይዟል። 

ለመሆኑ የመንግሥት ከፍተኛ ተቋማት የስፖርት ውድድር ዓላማው ምንድን ነው? ከዓላማው አኳያስ ምን ያህሉን ከግብ አድርሷል? ስንል የኢትዮጵያ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አባይ በላይሁንን ጠይቀናቸው ነበር። አቶ አባይ ፌስቲቫሉ ሲካሄድ ዓላማ አድርጎ የተነሳው “ተተኪ ስፖርተኞችን ለአገር ማብቃት፣ በዩኒቨርስቲዎች ቋሚ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋትና በተማሪዎች መካከል መቀራረብን መፍጠር ነው። በዚህ በኩል ካየነው እንደ ፍጹም ገብረማሪያምና እንዳለ ከበደ አይነት ተጫዋቾችን ለታላላቅ ክለቦችና ለብሔራዊ ቡድን ማብቃት ችሏል። በስፖርት መሰረተ ልማት በኩል ካየነው ደግሞ ውድድሩን ያዘጋጁ ዩኒቨርስቲዎች ለውድድሩ ዝግጅት ሲሉ የሚያስገነቧቸው ስታዲየሞችን ጨምሮ ሌሎች የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች ቋሚ ቅርስ ሆነዋል” ሲሉ ለኢትዮፉትቦል ዶት ኮም ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅት የአገራችን ክለቦች ቡድናቸውን የሚያዋቅሩት በወጣቶችና በተተኪዎች ላይ ሳይሆን ከአንድ ክለብ ወደ አንድ ክለብ በሚዘዋወሩ ወይም ሞባይል ተጫዋቾች ነው። እነዚህን ተጫዋቾች ክለቦቹ የሚያስፈርሟቸው ዳጎስ ባለ የፊርማ ገንዘብ ነው። ነገር ግን እንደዚህ አይነት ውድድሮችን ወደ ታች ወረድ ብሎ በመከታተል ተጫዋቾችን ሲመለምሉ አይታይም። የኦሮሚያ ክልሉ ሙገር ሲሚንቶና የደቡቡ ሲዳማ ቡና ፍጹም ገብረማሪያምንና እንዳለ ከበደን የመለመሉበትን መንገድ ሌሎች ክለቦችም ሊከተሉት የሚገባ አካሄድ ነው።  
Fitsume Gebremariam


እንደ አቶ አባይ ገለጻ የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂው ፍጹም ገብረማሪያም እና የሲዳማ ቡናው እንዳለ ከበደ ወደ ታላላቅ ክለቦች የተዘዋወሩትና አገራቸውን የወከሉት በዚሁ ውድድር ባሳዩት ብቃትነው። ከሁለቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ ቁጥራቸው በዛ ያሉ ተጫዋቾች በፕሪሚየር ሊግና በብሔራዊ ሊግ ተወዳዳሪ ክለቦች ውስጥ ተመርጠው መጫወት የቻሉት ከዚሁ ውድድር ነው። አቶ አባይ “ክለቦች ውድድሩን ትኩረት ሰጥተው በመመልከት ክለባቸውን ለማደራጀት ሲንቀሳቀሱ ግን አይታይም። ክለቦቹ ግን ቡድናቸውን ለማደራጀት በርካታ ሚሊዮን ብሮችን እያወጡ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ ይታያሉ። ነገር ግን ወደ ታች ወረድ ብለው ቢመለከቱ በእድሜ ወጣት የሆኑና ታክቲካል ዲሲሊንድ የሆኑ ተጫዋቾችን ማግኘት ይችሉ ነበር” ሲሉ ይናገራሉ። ከእግር ኳስ በተጨማሪ በሌሎች ስፖርቶች ላይም ማለትም በቮሊ ቦል በእጅ ኳስ አትሌቲክስና የመሳሰሉት ስፖርቶች ላይ አገራቸውን የወከሉ ተጫዋቾች ከውድድሩ መገኘታቸውን አቶ አባይ ተናግረዋል። በሌሎች ስፖርቶች ላይ የተገኙ ውጤቶችን ኢትዮጵያን አትሌቲክስ ዶት ኔት ላይ ይዘን እንቀርባለን። 

በዩኒቨርስቲዎች እየተገነቡ ያሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ምን ያህል ጥራታቸውን የጠበቁ ናቸው? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሰጡት አቶ አባይ “ለምሳሌ የዘንድሮውን ውድድር የሚያስተናግደው የአዳማ ዩኒቨርስቲ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም አስገንብቷል። ስታዲየሙ በወንበር ከ20 ሺህ በላይ ተመልካች የሚያስተናገድ ስታዲየም ነው። ያለፈውን ዓመት ያስተናገደውን የሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ስታዲየምምም ቢሆን እጅግ ዘመናዊ ነው” ሲሉ መልሰዋል። የአዳማ ዩኒቨርስቲ አስገንብቶ ለውድድሩ ብቁ ያደረገው ስታዲየም ከ20 ሺህ በላይ ተመልካቾችን ማስተናገድ ይችላል። ይህ ማለት ደግሞ 30ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ እያስተናገዱ ካሉት የኢኳቶሪያል ጊኒ አራት ስታዲየሞች ሶስቱን ይበልጣል ማለት ነው። 

ሌላው በዩኒቨርስቲዎች እየተገነቡ ያሉ ስታዲየሞች በዝናብ ወቅት በውሃ እንዳይበላሽ የሚከላከል ቴክኖሎጅ ተገጥሞላቸው የተገነቡ በመሆናቸው ስታዲየሞቹን ለየት ያደርጋቸዋል። ይህ ደግሞ የስታዲየም ጥራት ችግር ያለባትን አገራችንን በአማራጮች እንድትሞላ ያደርጋታል። በተለይ እንደ አፍሪካ ዋንጫና ሌሎች አህጉራዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ከሚያስመርጡ መስፈርቶች አንዱና ዋናው አገሪቱ ያሏት የመወዳደሪያ ስታዲየሞችና የመለማመጃ ሜዳዎች ጥራትና ብዛት ነው። በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ እየተገነቡ ካሉ ስታዲየሞች በተጨማሪ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስፖርት ውድድር ሲባል በየዩኒቨርስቲዎች የሚገነቡ ስታዲየሞች አገራችንን ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት የማህበሩ ፕሬዚዳንት ያምናሉ። 

 የእንግሊዙ ታላቅ ክለብ አርሴናል በ1999 ኒኮላስ አኔልካን ለሪያል ማድሪድ በ23 ሚሊዮን ፓውንድ ሽጦ የራሱን መለማመጃ ሜዳ ከመገንባቱ በፊት ይጠቀም የነበረው በለንደን የሚገኝ አንድ ዩኒቨርስቲን ሜዳ ነበር። በአገራችን ካሉ ክለቦች መካከል የራሳቸው መለማመጃ ሜዳና ስታዲየም ያላቸው ክለቦች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ናቸው። ለዚህም ልምምዳቸውን የሚሰሩት ተጫዋቾችን ለጉዳት ከሚያጋልጡ ሜዳዎች ላይ ሲሆን እሱንም ቢሆን ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈሉ ነው። ነገር ግን ክለቦች የራሳቸውን ሜዳዎች ገንብተው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ በዩኒቨርስቲዎች ሜዳ ላይ ከልምምድ እስከ ዋናው ጨዋታ መጠቀም የሚያስችላቸውን እድልም ይፈጥርላቸዋል ማለት ነው። 

የፊታችን ጥር 23 በአዳማ ዩኒቨርስቲ የሚጀምረውን የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የስፖርት ውድድር ክለቦችና በቦታው ተገኝተው በመከታተል ለነገ የቡድናቸውና የማህበራቸው ጥንካሬ የሚሆኑ ስፖርተኞችን ቢመለምሉ ይጠቀማሉ!! የዝግጅት ክፍላችን መልዕክት ነው። 

ዘገባ፦ ይርጋ አበበ ከአዳማ

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!