የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር መዝጊያ ጨዋታዎች
ጥር 15, 2007

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2007 ዓ.ም መርሃ ግብር የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ነገና እሁድ በተለያዩ ከተሞች ይካሄዳሉ። የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ይጫወታል። ሁለቱ ክለቦች ያለፉትን ተከታታይ ጨዋታዎቻቸውን በድል የተወጡ በመሆናቸው በነገው ጨዋታም ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላው የደቡብ ኢትዮጵያ ክለብ ወላይታ ድቻ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች በሽንፈት ያጠናቀቀውን ኤሌክትሪክን በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይገጥማል። ሁለቱ ቡድኖች ያለፈውን ወር በተለያየ ደረጃ ያሳለፉ ሲሆን በዛሬው ጨዋታም ኤሌክትሪክ ከተደጋጋሚ ሽንፈቱ ለማገገም ድቻ ደግሞ ተከታታይ ድሉን ለማስጠበቅና ከመሪዎች ጋር ያለውን ልዩነት አስጠብቆ ለመጓዝ ጨዋታውን በከፍተኛ ሞራል የሚያካሂዱ ይሆናል። ሁለቱ ቡድኖ አንድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀራቸዋል።

አርባምንጭ ከነማ በሜዳው አዳማ ከነማን የሚያስተናግድበት መርሃ ግብርም ተጠባቂ ነው። ሁለቱ ክለቦች ተመሳሳይ ነጥብ ይዘው የግብ ክፍያቸው ብቻ በመበላለጡ ደረጃቸው የተለያየ በመሆኑ በዚህ ጨዋታ አሸናፊ የሚሆነው ነጥቡን ከፍ አድርጎ በበላይነት ለመቆየት ስለሚያስችለው ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል። በሜዳቸው ተሸንፈው የማያውቁት አርባምንጮች የአዳማን ተከታታይ የድል ጉዞ መግታት ይችሉ ወይስ አዳማ ተካታታይ ድሉን አስጠብቆ ይጓዛል የሚለውን ከጨዋታው በኋላ የምናየው ይሆናል።

አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋን አሰናብቶ አዲሴ ካሳን በጊዜያዊነት የቀጠረውና ባለፈው ሳምንት የዓመቱን ሁለተኛ ድሉን ያስመዘገበው ሃዋሳ ከነማ ወደ ጎንደር ተጉዞ ከዳሽን ቢራ ጋር ይፋለማል። ሁለቱ ቡድኖች ለዚህ ጨዋታ የደረሱት ዳሽን ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከነማ ተሸንፎ ሃዋሳ ደግሞ ኤሌክትሪክን አሸንፎ ነው። ሃዋሳ ከነማ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ነጥቡን አስር አድርሶ ከዳሽን ቢራ በሶስት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ያለፉትን ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሽንፈት ያጠናቀቀው የአሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌው መከላከያ ወደ አሰላ ተጉዞ የውጤት ቀውስ ውስጥ ያለውን ሙገር ሲሚንቶን ይገጥማል።

የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የሚካሄደው ነገ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና ከወልድያ ከነማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያካሂዱት ጨዋታ ነው። ባለፈው ሳምንት የሽንፈት ጽዋን ተጎንጭተው ለዛሬው ጨዋታ የደረሱት ሁለቱ ቡድኖች የዛሬውን ጨዋታ ልዩ ትኩረት ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ ወልድያ ከነማ ከ12 ጨዋታዎች ማግኘት ከነበረበት 36 ነጥብ 31ን ጥሎ አምስት ነጥብ ብቻ በመያዝ የደረጃው ግርጌ ላይ የተቀመጠ በመሆኑ ከነገው ጨዋታ ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዞ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ባለፈው ሳምንት በቡና ደርቢ በሲዳማ ቡና የተሸነፉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ወልድያን የግድ ማሸነፍ ስለሚኖርባቸው ለጨዋታው ልዩ ትኩረት ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ቡና እንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀራቸው ሲሆን አሁን የያዙት ነጥብ ደግሞ 18 ነው።

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታና ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጨዋታ የሚካሄደው በሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስና በጥሎ ማለፉ አሸናፊ ደደቢት መካከል የሚካሄደው ጨዋታ ነው። ሁለቱ ቡድኖች ያለፈውን ዓመት የፕሪሚየር ሊጉና የጥሎ ማለፉን ዋንጫ በማንሳት ያጠናቀቁ ሲሆን በዘንድሮው የውድድር ዓመትም የፕሪሚየር ሊጉን ክብር ለመቀዳጀት የተሻለ እድል ካላቸው ክለቦች ቀዳሚዎቹ ናቸው። በተለይ ፈረሰኞቹ ባለፈው ሳምንት ወደ ወሎ ተጉዘው ወልድያ ከነማን ሶስት ለባዶ አሸንፈው የተመለሱበት ውጤት ለእሁዱ ጨዋታ ከፍተኛ የሞራል ስንቅ ይሆናቸዋል ተብሏል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀራቸው ነጥባቸውን 21 ያደረሱት ፈረሰኞቹ ከመሪው ሲዳማ ቡና ያለቸው ልዩነት አምስት ብቻ ነው። ሰማያዊዮቹም ቢሆኑ ከአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ስንብት በኋላ መነቃቃት እያሳዩ ሲሆን በተለይ በእሁዱ ጨዋታ ቅጣት ላይ የነበረው ሸይቩ ጅብሪል ወደ ጨዋታ ስለሚመለስ ተጠናክረው እንደሚገቡ ተነግሯል።
ፕሪሚየር ሊጉን ሲዳማ ቡና በ26 ነጥብ ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 21 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በተመሳሳይ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ወላይታ ድቻ በ20 ነጥብ ሶስተኛ ሲሆን የወራጅ ቀጠናውን ሙገር ሲሚንቶና ወልድያ ከነማ በብቸኝነት ተቆጣጥረውታል።

ስምንት ግቦችን ያስቆጠረው ቢኒያም አሰፋ የሊጉን ከፍተኛ ግ አግቢዎች ደረጃ ሲመራ የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኖሜ ይከተለዋል። ሳሙኤል ሳኖሜ ያስቆጠራቸው ግቦች ሰባት መሆናቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጨዋታዎችን ስታትስቲክስ በሚመዘግበው “ኮሚኒኬ” የገለጸ ቢሆንም በርካታ መገናኛ ብዙሃን ግን የግቦቹን ብዛት ስምንት አድርሰው ሲዘግቡ ይሰማል።


ethioootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!